የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ አረንጓዴ ጎርፍ አትሌቲክስ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን “የገና በዓልን ከአንጋፋ አትሌቶቻችን ጋር እናሳልፍ፤ ክብር ለሚገባቸው ክብር እንስጥ” በሚል በኢትዮጵያ ሆቴል ያዘጋጁት የእውቅናና የምስጋና ፕሮግራም በልዩ ድምቀት ተጠናቋል፡፡
በዚህ ፕሮግራም ላይ በህይወት ዘመናቸው ለስፖርቱ የላቀ አስተዋፅኦና ድጋፍ ላበረከቱ ኢትዮጵያን ወዳጅ ግለሰቦች የእውቅናና የምስጋና ሠርተፊኬት የተበረከተላቸው ከመሆኑ በተጨማሪ የክብር ካባም ተጠልቆላቸዋል፡፡
የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር የተከበሩ አቶ ዱቤ ጅሎ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በላይ ደጀን፣ የኢትዮጵያ አንጋፋ አትሌቶች ፕሬዚዳንት ኮማንደር ጌጤ ዋሚ በክብር እንግድነት በተገኙበትና ሽልማቱን በሰጡበት ስነ-ሥርዓት ላይ በኢትዮጵያ ስፖርት የማይዘነጋ ውለታን የፈፀሙት የሞሀ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትራ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ጌታቸው ቢርቦ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አያሌው ጥላሁን እንዲህ ረዥሙን ህይወቱን ለኢትዮጵያ ስፖርት በመስጠት ተለይቶ የሚታወቀው አንጋፋው ጋዜጠኛ ሠለሞን ገ/እግዚአብሔር የእውቅናና የምስጋና ሠርተፌኬት የተበረከተላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ለስፖርቱ ላደረጉት አስተዋፅኦም የክብር ካባ ተጠልቆላቸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማህበርን ከምስረታው ጀምሮ አሁን ለደረሰበት የእድገት ደረጃ እንዲበቃ በማድረግ፣ የአዲስ አበባ አትሌቲክስንና በአጠቃላይ የአትሌቲክስ ስፖርትን፣ አትሌቶችን፣ ኪነጥበብንና ሙያተኞችን በማገዝና በመደገፍ እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ፣ የመቆዶኒያ የአረጋዊያን መርጃና መንከባከቢያ ማዕከልን በማገዝ በአጠቃላይ በበርካታ ስፖርታዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍና ማህበረሰቡን ማዕከል ባደረገ በጎ ሥራ ላይ በመሳተፍ የማይሰስተውን እጃቸውን በመዘርጋት ተለይተው የሚታወቁት የሞሐ የለስላሳ መጠጦች ኢንድስትሪ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌታቸው ቢርቦ ለስፖርቱና ለማህበረሰቡ ያበረከቱት መልካም ስራ ተመልካች አግኝቶ ለክብር ካባና ለምስጋና አብቅቷቸዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ለስፖርቱና ለማህበረሰቡ ያደረጉትን አስተዋፅኦ ያህል ያልተነገረላቸውና ያልተዘመረላቸው ነገር ግን በርካታ በጎ ተግባራትን በማከናወን ተለይተው የሚታወቁት አቶ ጌታቸው ቢርቦ በዚህ መልኩ እውቅና ማግኘታቸው መልካም ስራዎቻቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁት ሁሉ ከማስደሰት ባለፈ ሁሉም በአንድ ድምፅ “ይገባቸዋል” ብሎ ምስክርነቱን እንዲሰጥ አድርጓል፡፡
ከአቶ ጌታቸው ቢርቦ ሌላም ሁሌም ከስፖርቱና በተለይ ከአትሌቶች ጎን የማይጠፉት ለአትሌቶች ስኬታማነት የበኩላቸውን ሚና በመጫወት የሚታወቁት የህክምና ባለሙያው ዶክተር አያሌው ጥላሁን ለስፖርቱ እድገት ባበረከተው አስተዋፅኦ እንዲሁም ዛሬ ወደ ሚዲያው ለመጡት ጋዜጠኞች የሙያ አባት የሆነው አንጋፋው ጋዜጠኛ ሠለሞን ገ/እግዚአብሔርም የእውቅናና የምስጋና ሠርተፊኬት የተበረከተላቸው ሲሆን የክብር ካባም ተጠልቆላቸዋል፡፡
ከሽልማቱና በእውቅና ስነ-ሥርዓቱ በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር “መረዳዳት በህይወት” በሚል መሪ ቃል ለሀገራቸው፣ ለህዝቡና ለባንዲራው የላቀ ሚና የተጫወቱ የሀገራችን እንቁዎችን በዚህ ደረጃ እውቅናና ምስጋና ማግኘታቸው ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ በክብር እንግድነት የተገኙት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ በበኩላቸ ፕሮግራሙን ላዘጋጁትና ለዚህ ያበቁትን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ስፖርት ኮሚሽን አመራሮችንና አቶ መልካሙ ተገኘን አመስግነዋል፡፡
ይህንን ቁም ነገር ያለውና ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፉ ፕሮግራምን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን ያዘጋጅው የአረንጓዴ ጎርፍ አትሌቲክስ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ መልካሙ ተገኝ የባህር ዳር ታላቁ ሩጫ ዳይሬክተርና መስራች እንደሁም የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሲሆን በበጎ ሥራው ብዙዎችም “አበጀህ” ብለውታል፡፡
በኢትዮጵያ ሆቴል በተዘጋጀው ስነ ሥርዓት ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ጎርፍ አትሌቲክስ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሁለት አምባሳደሮች የተሰየሙ ሲሆን ከሴቶች አትሌት ቁጥሬ ዱለቻ ከወንዶች ሻምበል እሸቱ ቱራ የእውቅና አምባሳደርነት ሠርተፍኬትም ተሰቷቸዋል፡፡