በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ከቅ/ጊዮርጊስ በመለያየት ፊርማውን ለፋሲል ከነማ ያኖረው አብዱልከሪም መሐመድ በአዲሱ ቡድን ቆይታው በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒየንስ ሊግ ላይ ለሚሳተፈው ክለባቸው ጥሩ ግልጋሎትን በመስጠት ከዚህ ቀደም የአገራችን ቡድኖች በኢንተርናሽናል ጨዋታ ተሳትፎ ካስመዘገቡት ውጤት በሚሻል መልኩ ፋሲል ይህል ክብር እንዲጎናፀፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ዋንኛው ተዋናይ ለመሆን መዘጋጀቱን ገልፆልናል።
በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመን ቆይታው ለደቡብ ፖሊስ፣ ለሲዳማ ቡና፣ ለሐዋሳ ከተማ፣ ለኢትዮጵያ ቡናና ለቅ/ጊዮርጊስ በመጫወት ያሳለፈው አብዱልከሪም መሐመድ በተጨዋችነት ዘመኑ አንድ ጊዜ የፕሪሚየር ሊግ የኮከብ ተጨዋችነትን ክብር በቅ/ጊዮርጊስ ቡድን ውስጥ ሆኖ ማግኘቱ ቢያስደስተውም የሊግ ዋንጫውን ግን እስካሁን በተጫወተባቸው ክለቦች ውስጥ ሊያገኝ አለመቻሉና በተለይም ደግሞ ይህንን ክብር በእርግጠኝነት እጎናፀፍበታለው ብሎ ወዳሰበው ክለብ ቅ/ጊዮርጊስ ካመራበት ጊዜ ጀምሮም ይህን እልሙን ሊያሳካው አለመቻሉ በውስጡ ከፍተኛ የቁጭት ስሜት እንደሚያድርበት ከሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል።
ፋሲል ከነማ የፕሪ ሲዝን ዝግጅቱን በጀመረበት የአሁን ሰዓት ላይ አዲሱ የቡድኑ ፈራሚ ክለቡን የቅድሚያ ምርጫው አድርጎ ስለተቀላቀለበት መንገድ፣ ስላሳለፋቸው የኳስ ህይወቶቹና ስለ ቀጣይ ጊዜ የፋሲል ከነማ ቡድን ቆይታው ጥያቄዎችን አቅርበንለት አጠር ባለ መልኩ ምላሹን ሰጥቶናል።
ከቅ/ጊዮርጊስ ከተለያየ በኋላ ፋሲል ከነማን የቅድሚያ ምርጫው ስለማድረጉ
- ማሰታውቂያ -
“የቅ/ጊዮርጊስ የውል ጊዜዬ እንደተጠናቀቀ ፋሲል ከነማን የመጀመሪያ ምርጫዬ በማድረግ ለክለቡ ፊርማዬን ያኖርኩት አሁን ላይ ካሉት ቡድኖች እሱ የተሻለ ስለሆነና በዚህ ቡድን ቆይታዬም ራሴን በማውጣት ያለኝን ጥሩ አቅም አሳይበታለው ብዬ ስላሰብኩኝ ነው”።
ከሌሎች ክለቦች ጥሪ ቀርቦለት እንደሆነ
” አዎን፤ ከፋሲል ውጪ እኔን ለመውሰድ የጠየቁኝ ቡድኖች ነበሩ፤ ያም ሆኖ ግን ፋሲል ከነማ ከእኔ ጋር ግንኙነትን ጀምሮ የነበረው ወደ ውድድሩ ማጠናቀቂያ አካባቢና ሻምፒዮናነቱንም አረጋግጦ ከሆነም በኋላ ስለነበር እንደዚሁም ደግሞ ይሄ ቡድን ሀገራችንን በመወከልም በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ላይም ስለሚሳተፍ ያንን ታሳቢ በማድረግም ጭምር ነው ለእነሱ ቅድሚያን መስጠት አለብኝ ብዬ ቡድኑን የተቀላቀልኩት”።
ባሳለፋቸው የእግር ኳስ ህይወቱ ደስተኛ እንደሆነ
“ከሞላ ጎደል አዎን በጣም ደስተኛ ነኝ፤ አልተደሰትኩም ብዬ የምናገረውም የሊጉን የኮከብ ተጨዋችነት ክብርን አግኝቼ የሊግ ዋንጫውን ከተጫወትኩባቸው ክለቦች ጋር በተለይም ደግሞ ይህን ክብር በእርግጠኝነት አሳካለው ካልኩበት ቅ/ጊዮርጊስ ጋር ለማግኘት ባለመቻሌ ነውና። ይሄ የቁጭት ስሜት ፈጥሮብኛል”።
በቅ/ጊዮርጊስ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው የሊጉን ዋንጫ ላለማንሳታቸው ስለሚሰጠው ምክንያትና ከክለቡ ጋር ስለመለያየቱ
” የቅ/ጊዮርጊስ ቆይታዬ ላይ ቡድናችን የሊጉን ዋንጫ ያጣባቸው የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ከእነዛ ውስጥ እኔ ልጠቅሰው የምፈልገው የአሰልጣኞች በተለያዩ ጊዜያት መቀያየር መቻላቸው ቡድኑን ባልተረጋጋ መልኩ እንዲጓዝና ውጤትም እንዲያጣ አድርጎታልና ይህ አካሄድ ሊሻሻል ይገባል። ለዚህ ውጤት ማጣት የአሰልጣኝ መለዋወጥ እንዳለ ሆኖ እኛ ተጨዋቾችና ወደ ቡድኑ የሚመጡት አንዳንድ አሰልጣኞችም ባለፉት አራት ዓመታት ለክለቡ የሰራነው ምንም ነገርም አልነበረምና እኛም ለውጤቱ መጥፋት ተጠያቀሚ ነን፤ ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ስለመለያየቴ ደግሞ ለመናገር የምፈለረገው የውል ጊዜዬን ጨርሼ ነበር። ፋሲል ከነማም እንድጫወትለት ጠየቀኝ፤ እኔም ከዚህ ቡድን ጋር ዋንጫን ለማንሳት ስለምፈልግ የእነሱን ጥሪ በመቀበል ወደ ቡድናቸው አመራሁኝ”።
በኢትዮጵያ ቡና እና ወደ ቅ/ጊዮርጊስ በገባም የመጀመሪያው ዓመት ላይ የነበረውን ምርጥ ብቃት ዳግም በአዲሱ ክለቡ ያሳይ እንደሆነ
“ያን ዳግም ለማሳየት እንደምችል አልጠራጠርም። በቡና ቆይታዬ እንዳልከው ጥሩ የጨዋታ ጊዜ ነበረኝ። ቅዱስ ጊዮርጊስ በገባሁበት የመጀመሪያ ዓመት ላይሞ ኮከብ ተጨዋች እስከመባል ደርሻለው። ከዛ በኋላ ግን የአሰልጣኞች በየጊዜው መቀያየር ብቃቴን ጠብቄ እንዳልሄድ አድርጎኝ ነበርና በአዲሱ ዓመት ላይ በሚኖረኝ የውድድር ቆይታ ምርጥ የተጨዋቾችን ስብስብ በያዘው የፋሲል ከነማ ክለብ ውስጥ ስኬትን ተጎናፅፌ ዳግም እንደማበራ አምናለሁ”።
ፋሲል ከነማ የፕሪ-ሲዝን ልምምዱን ጀምሯል፤ ከቡድኑ ምን ውጤት ይጠበቅ
” ይሄ ቡድን ከዚህ ዓመት መጨረሻ ጀምሮ እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ ቅድሚያ የኢንተርናሽናል በመቀጠል ደግሞ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ስላለበት አሁን ላይ ለብሄራዊ ቡድን የተመረጡትን ተጨዋቾች ሳያካትት ጥሩ የሚባለውን የዝግጅት ወቅቱን ጀምሯል። በዚሁ ተሳትፎውም ክለባችን በሁለቱም ውድድሮቹ በሀገር ውስጥ የያዘውን አሸናፊነት ለማስቀጠል በኢንተርናሽናሉ ደግሞ የከዚህ በፊቱን የአገራችን ክለቦች ያመጡትን የውጤት ሪከረድ ለመስበር ተዘጋጅተናልና በዚህ መልኩ ነው ወደ ውድድሩ የምንገባው”።
ስለ ፋሲል ከነማ ሻምፒዮናነትና ስለ አቡበከር ኮከብ
ተጨዋችነት ምን አልክ….
“ፋሲሎች በውድድር ዘመኑ በሁሉም መልኩ ጥሩ ጊዜን ነበር ያሳለፉት፤ ሻምፒዮንነቱም የሚገባቸው ነው። ወደ አቡኪ ስመጣ ስለ እሱ ምንም ጥያቄ የለም። በውድድር ዘመኑ ምርጥ ነበር። ለቡና ስኬታማነትም ትልቁን ድርሻ ይወስዳልና ኮከብነቱ የሚያንሰው እንጂ የሚበዛበት አይደለም”።