ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በሻምፒዮናነት ያጠናቀቀው ፋሲል ከነማ ለአዲሱ የውድድር ዘመን ዝግጅቱን አጧጡፎ የቀጠለ ሲሆን በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ተሳትፎው ላይም ከሱዳኑ አል ሂላል ጋር የነበረበትን ጨዋታ በአጠቃላይ ውጤት 3-3 በማጠናቀቅ በሜዳው በተቆጠረበት ግብ ከውድድሩ ሊሰናበት ችሏል፡፡
ፋሲል ከነማ ከቻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ተሳትፎ መልስ በአሁን ሰዓት መደበኛ ልምምዱን በማከናወን ላይ ሲሆን ዛሬ በሚጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫም ላይ ተሳታፊ ይሆናል፤ የመጀመሪያ ግጥሚያውንም ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ሰኞ በ10 ሰዓት ያከናውናል፡፡
የፋሲል ከነማን የፕሪ-ሲዝን ዝግጅት በተመለከተ፣ ስለ ቡድኑ የኢንተርናሽናል ጨዋታ ተሳትፎና ሌሎችን ጥያቄዎች አክለን የቡድኑን ተጨዋች በረከት ደስታን ያናገርነው ሲሆን ተጨዋቹ ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ያደረገው ቆይታም ይህን ይመስላል፤ ተከታተሉት፡፡
ሀትሪክ፡- የፕሪ-ሲዝን ዝግጅታችሁ በምን መልኩ ይገለፃል?
- ማሰታውቂያ -
በረከት፡- በጣም ጥሩ ዝግጅትን ነው ዘንድሮ ያደረግነው፤ አሁንም ልምምዳችንን አጠናክረን ቀጥለንበታል፤ ለእዚህም ጥሩ መዘጋጀታችን ምስክሩ ቡድናችን በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ በነበረው ጨዋታ ምንም እንኳን በሜዳው የተቆጠረበት ግብ ዋጋ አስከፍሎት ከውድድሩ ቢሰናበትም ጥሩ ለመጫወት ችለን ነበር፤ ያ ጥሩነታችንም በመቀጠል ላለብን የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫና ለዋናው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉም የሚረዳን ስለሆነ ዝግጅታችንን በመልካም ሁኔታ ነው የምገልፀው፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማን አዳዲስ ተጨዋቾች ተቀላቅለውታል፤ እንዴት አገኘካቸው? እናንተን እየተላመዱስ ነው?
በረከት፡- ወደ ቡድናችን እኛን ለማጠናከር የመጡት ተጨዋቾች ጥሩ ችሎታ ያላቸውና የቡድናችንን ግንባታም ወደ ላይ ከፍ የሚያደርጉልን ናቸው፤ ቡድኑን ሲቀላቀሉም አዲስ ነገርም አልሆነባቸውም፤ ምክንያቱም ከእነሱ ጋር ከዚህ ቀደም እንተዋወቅም ነበርና፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ በፕሪ-ሲዝኑ ዝግጅቱ ምን ምን ሁኔታዎች ላይ ተንተርሶ ልምምዱን እየሰራ ይገኛል?
በረከት፡- ወደ ዝግጅት ከገባንበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ስንሰራ የቆየነው ልምምድ ከኳስ ጋር የተያያዘው የሜዳ ላይ አጨዋወታችንን በአማከለ መልኩ መሰረቱን ጠብቆ በማጥቃት ላይ ያተኮረ ጨዋታንና ሌላው ደግሞ ጎል እንዳይገባብን ማድረግ ነው፤ እነዚህን ነው እየሰራን የምንገኘው፡፡
ሀትሪክ፡- በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎአችሁ በአጠቃላይ ውጤት 3-3 ብትወጡም በሜዳችሁ የተቆጠረባችሁ ጎል ከውድድሩ አሰናብቷችኋል፤ በቡድናችሁ ላይ ይህ ውጤት ምንድን ነው የፈጠረባችሁ ስሜት?
በረከት፡- በውጤቱ የእውነት ተቆጭተናል፤ በሜዳ ላይ ባሳየነው ጥሩ እንቅስቃሴ ደግሞ ተፅናንተናል፤ ፋሲል ከእዚህ ውድድር መሰናበት አልነበረበትም፤ ያም ሆኖ ግን ፈጣሪ ስላላለው በሜዳችን ላይ የተቆጠረብን ግብ ነው ዋጋ ሊያስከፍለን በመቻሉ ልንወድቅ የቻልነው፡፡
ሀትሪክ፡- ለውጤት መጥፋቱ ዋንኛው ምክንያት ምን ነበር?
በረከት፡- እዚህ የሰራነው ስህተት ነዋ! በሜዳችን ላይ ስንጫወት እድላችንን መጠቀም ነበረብን፤ ግብ ሳይቆጠርብን ማሸነፍ ብንችል የማለፍ እድሉ ይኖረን ነበር፤ የእኛ ሀገርን ቡድኖች ብዙ ጊዜ የሚቸግራቸው የሜዳቸው ላይ አድቫንቴጅን አለመጠቀም ነው፤ ይሄ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የሱዳኑን ክለብ አል ሂላልን በምን መልኩ አገኘካቸው?
በረከት፡- ጥሩ ናቸው፤ እነሱ በቦታ አያያዝና አዘጋግ በታክቲካል ዲስፕሊን ስለበለጡን ነው ወደ ቀጣዩ ዙር ሊያልፉ የቻሉት፤ ከዛ ውጪም ብዙ ጊዜ እኛ ኳስን አንሸራሽሮ መጫወቱ ላይ ብቻ ትኩረትን ስለምናደርግና እነሱ ደግሞ ረጅም ኳስን ሲጫወቱ ጥንቃቄው ላይም ክፍተቱ ስለነበረብን ያ ጎድቶናል፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዓምና አንስቷል፤ ዘንድሮስ?
በረከት፡- እንደ ዓምናው በድጋሚ እናነሳለን ሃ! እኛ ሻምፒዮና ነን፤ ይሄ ድላችንም ይቀጥላል፤ ለዛ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ እንደ ቡድን እንዴት ይገለፃል? ስለ ክለቡ ቆይታህስ ምን አልክ?
በረከት፡- ዘንድሮ በየቦታው ጥሩ ኳሊቲ ያላቸውን ተጨዋቾች ነው የያዝነው፤ ምርጥ አሰልጣኝና የኮቺንግ ስታፍ አባላቶችንም ይዘናል፤ እነዚህ ባለሙያተኞች ኳስን በነፃነት እንድንጫወት እያደረጉንም ይገኛሉና በአጠቃላይ ጥሩ ቡድን ነው ያለን፡፡ በፋሲል ከነማ ስላለኝ ቆይታ እስካሁን ጥሩ ጊዜን ነው እያሰለፍኩ የምገኘው ከሁሉም በላይ ደስተኛ ያደረገኝ ደግሞ አጥብቄ እፈልገው የነበረውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ማንሳቴ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ላይ ትሳተፋላችሁ፤ ከቅ/ጊዮርጊስም ጋር የመጀመሪያውን ጨዋታ ታደርጋላችሁ፤ በዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ?
በረከት፡- የሲቲ ካፑ ውድድር የአቋም መለኪያ ነው፤ ቡድንህን በደንብ አድርገት ትፈትሽበታለህ፤ ከዛ ውጪም ይሄ ጨዋታ በተለይ ለታዳጊና ወጣት ተጨዋቾች ራሳቸውን እንዲያሳዩበትና ለዋናው ውድድርም እንዲበቁበት አቋማቸውን የሚለኩበት ስለሆነ ይበልጥ እነሱ ይጠቀሙበታል፤ በዚህ ውድድር ላይ ፋሲል ከነማ ተጋባዥ ክለብ ሆኖ ቢቀርብም ዋንጫውን ለማንሳት ነው የሚጫወተው፤ የእዚህ ውድድር አሸናፊ መሆን ለዋናው ውድድር መነሳሳትን ይፈጠርልሃል፤ ስለዚህም ከቅ/ጊዮርጊሱ ጨዋታ ጀምሮ አሸናፊ ሆነን ለመጓዝ ነው ለውድድሩ የመጣነው፡፡
ሀትሪክ፡- ስለ ግል ህይወትህ አንድ ነገር በል እስኪ?
በረከት፡- ከስራዬ ውጪ ከባለቤቴ ጋር ጥሩ ጊዜን እያሳለፍኩ ነው የቆየሁት፤ እግር ኳስ ነፃነትን የሚጠይቅ ስፖርት ስለሆነ ባለቤቴ ለስራዬ መቃናት ብዙ ነገሮችን ታደርግልኛለች፤ እሷን ማመስገን እፈልጋለው፤ ልጄም አድጎ ነገሮች በጥሩ ጎኑም እየሄዱልኝ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ….?
በረከት፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ማገልገል የሁልጊዜም ምኞቴ ነው፤ በድጋሚም ስኳዱን መቀላቀል እፈልጋለው፤ ደግሞም ለእዛ የሚያበቃ ብቃትና አቅሙም ስላለኝ ጠንክሬ ሰርቼ የቡድኑ አባል እንደምሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ይህን ካልኩ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የመስቀል በዓል እንዲሆንላችሁ እመኛለው፡፡