” በህይወቴ ሁሌም ከምኮራባቸው ታሪኮች አንዱ የኢትዮጵያ ቡና ቆይታዬ ነው “
” የፕሮጀክት ቆይታዬ እግር ኳስንም በሚገባ ተረድቼ እንድጫወት አግዞኛል “
” የሁላችንንም ህልም ልናሳካ ከጫፍ ደርሰናል “
” ሁሌም ቢሆን ትናንት ከነበረኝ ደካማ ነገር እየተነሳው ለመሻሻል ነው የምሰራው ” ቢኒያም ካሳሁን /ኢትዮጵያ መድህን /
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ :- በመጀመሪያ ራስህን አስተዋውቀን ?
ቢንያም :- ቢንያም ካሳሁን እባላለሁ የቤተሰባችን የመጀመሪያ ልጅ ነኝ ሁለት እህት እና አንድ ወንድም አለኝ ተወልጄ ያደኩት በ ዳንግላ ከተማ ነው ።
ሀትሪክ :- እግር ኳስ የጀመርክበትን አጋጣሚ ታስታውሳለክ ?
ቢንያም :- አዎ እግር ኳስ የጀመርኩት በዳንግላ 04 ቀበሌ ከ 13 አመት በታች ቡድን በአሰልጣኝ ፀጋዬ አማካኝነት ነው ከዚያ በዳንግላ ከተማ ፕሮጀክት ታቅፌ ለ 3 አመታት በ አሠልጣኝ ታደሰ ጌታነህ ስር መሰልጠን ጀመርኩኝ ።
ሀትሪክ :- በፕሮጀክት የነበረህ ቆይታ እንዴት ነበር ?
ቢንያም :- በጣም ጥሩ ነበር አሠልጣኝ ታደሰ በእድሜያችን ልክ ይሰጠን የነበረው ስልጠና በጣም ትልቅ መሠረት እንድይዝ አድርጎኛል ። የፕሮጀክት ቆይታዬ እግር ኳስንም በሚገባ ተረድቼ እንድጫወት አግዞኛል ።
ሀትሪክ :- ከፕሮጀክት በኋላ ?
ቢንያም :- ከፕሮጀክት በኋላ የመላው አማራ ከ17 አመት በታች ውድድር ላይ ዳንግላን ወክዬ ለውድድር ባህርዳር ሄድኩ እዛ ባሳየሁት አቋም ለአማራ ምርጥ ተመረጥኩና 2008 ክረምት ሀዋሳ ላይ በተደረገው የመላው ኢትዮጵያ ከ 17 አመት በታች ውድድር ላይ ተሳተፍኩኝ ። ውድድሩ ላይ ባሳየሁት ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ በአሰልጣኝ ታዲዮስ ተክሉ ለኢትዮጵያ ቡና 17 አመት በታች መመረጥ ቻልኩኝ ።
ሀትሪክ :- በትንሽ እድሜህ ቤተሰብህን እና ያደክበትን አካባቢ ለቆ መሄድ አልከበደህም ?
ቢንያም :- በጣም ከባድ ነበር ለአማራ ምርጥ ለመመረጥ የወረዳ እና የዞን ውድድሮችን ማለፍ ግድ ነበር በዛ ምክንያት ራሱ ከቤተሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ለወራት እርቄ ነበር ናፍቆቱን አልቻልኩትም ነበር ።
ሀትሪክ :- ቡና ከገባህ በኋላ ከቤተሰብ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ርቀህ ነው የሄድከው ሁኔታው እንዴት ነበር ?
ቢንያም :- እውነት ከባድ ነበር አዲስ አበባን መላመድ ከብዶኝ ነበር የቤተሰብ ናፍቆት ተጨምሮበት ማለት ነው ። ያው ቀስ በቀስ መልመድ ጀመርኩ ።
ሀትሪክ :- አዲስ አበባ እንደገባህ ያገዘህ ሰው አለ ?
ቢንያም :- በአጋጣሚ አዲስ አበባ ውስጥ የማውቀው ሰው አልነበረም የቡድን አጋሮቼ እና አሰልጣኞቼ ቀስ በቀስ እንድለምደው አድርገውኛል ።
ሀትሪክ :- ከቡድን አጋሮችህ በተለየ ሁኔታ ይረዳህ የነበረ ሰው አለ ?
ቢንያም :- በሚገባ በወቅቱ የቡድን አጋሬ እና የቡድናችን አምበል ቅዱስ ተስፋዬ ወዲያው ተግባብቶኝ ብዙ ነገር አቅሎልኛል እሱም እንደኔ ከኦሮሚያ ክልል ተመልምሎ ነበር የመጣው ። በአሁን ሰዓት ለሰንዳፋ በኬ እየተጫወተ ይገኛል ።
ሀትሪክ :- የቡና ቆይታህ እንዴት ነበር ?
ቢንያም :- በእግር ኳስ ህይወቴ ትልቅ ቦታ የምሰጠው እንዲሁም ደስ የሚል ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት ። በህይወቴ ሁሌም ከምኮራባቸው ታሪኮች አንዱ የኢትዮጵያ ቡና ቆይታዬ ነው ።
ሀትሪክ :- ወደ ዋናው ቡድን እንዴት አደክ ?
ቢንያም :- 2010 የነበረው ተስፋ ቡድን ላይ በጣም ጥሩ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት ከዛ ቡድን ውስጥ በአሰልጣኝ ዲድየር ጎሜዝ አማካኝነት የዋናው ቡድን ዝግጅት ላይ ታይተን አራት ልጆች ወደ ዋናው ቡድን አደግን ።
ሀትሪክ :- በዋናው ቡድን ምን ያህል አመት ቆየክ ?
ቢንያም :- አንድ አመት ነው የቆየሁት 2011 ዓመተ ምህረት ።
ሀትሪክ :- የመጫወት እድል አግኝተህ ነበር ?
ቢንያም :- አላገኘሁም ነበር አሰልጣኝ ጎሜዝ ለቀጣይ አመታት በዋናው ቡድን እንድንጫወት በጥሩ ሁኔታ እያዘጋጀን ነበር ። ኮንትራትም ለሶስት አመት ነበር የፈረምነው ። ለኛ ጥሩ ነገር ነበረው ያለንን ነገር እንድናሳድግ ይመክረን ነበር ። በመሀል ግን ከቡና ጋር ተለያየው ።
ሀትሪክ :- የወጣህበት መንገድስ እንዴት ነው ?
ቢንያም :- በ2012 አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ለቀጣይ አመት ዝግጅት ከመጀመሩ በፊት ልጆችን ማየት አለብኝ ብሎ ተጠራን ። በሰዓቱ ብዙ ተጫዋቾች ለመታየት ፍቃደኛ አልነበሩም የመጣነው ልጆች 2 እና 3 ቀን ከሰራን በኋላ እኔ ለምፈልገው አጨዋወት አትሆኑም ተብለን ተቀነስን ።
ሀትሪክ :- ከዛ ወዴት አመራህ ?
ቢንያም :- በሰዓቱ ከባድ ጊዜ ነበር ብዙ ሰዎችንም አላውቅም ነበር መጨረሻ ላይ ወደ ዳንግላ ተመለስኩ ። በጊዜው ከተማችን ላይ ለነበረው ዳንግላ ከነማ መጫወት ጀመርኩ ለ 6 ወር ያክል ።
ሀትሪክ:-ከኮቪድ መልስ ነው የበፀሎትን ገላን ከተማን የተቀላቀልከው
ቢንያም:- አዎ አሰልጣኝ በፀለት ነው ተስፋ ቆርጬ ከተቀመጥኩበት ታች ወርዶ ያመጣኝ ።በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው እፈልጋለው
ሀትሪክ :- አሰልጣኝ በፀሎትን ተከትለህ ወደ ኢትዮጵያ መድን መተኻል እና አመቱ እንዴት ነው ለአንተ ?
ቢንያም :- በጣም ደስ የሚል አመት እያሳለፍኩ ነው ። አሰልጣኝ በፀሎት በብዙ ነገር እያገዘኝ እዚህ አድርሶኛል የተሳካ አመትም እያሳለፍኩ ነው ።
ሀትሪክ :- በግልህ ጥሩ የውድድር አመትን እያሳለፍክ ነው የተለየ ዝግጅት አድርገኻል ?
ቢንያም :- ሁሌም ቢሆን ትናንት ከነበረኝ ደካማ ነገር እየተነሳው ለመሻሻል ነው የምሰራው ። ገላን እያለሁ የነበሩብኝን ክፍተቶች ጠይቄ በድክመቶቼ ላይ በደንብ ሰርቼ ነው በዚ አመት የቀረብኩት በቀጣይም ማሻሻል ያለብኝ ብዙ ነገር አለ ጠንክሬ ሰርቼ አስተካክላለው ።
ሀትሪክ :- በዘንድሮ የውድድር ዓመት ወደ ሀገሪቱ ትልቁ ሊግ ለመካፈል የቀራቹ ሁለት ነጥብ ብቻ ነው ። ውድድር ስትጀምሩ እንገባለን ብላችሁ ነበር ?
ቢንያም :- አዎ ከመጀመሪያው የዝግጅት ቀናችን ጀምሮ ነው ወደ ፕሪምየር ሊግ ስለመግባት ማውራት የጀመርነው ። አሰልጣኛችን በስነ ልቦና እና በልምምድ በደንብ አዘጋጅቶን ነው ወደ ውድድር የገባነው ።
ሀትሪክ :- ነቀምት ከተማ ጠንካራ ተፎካካሪያቹ ነበር ምድቡን መምራት ሲጀምሩ ስጋት ውስጥ አልገባቹም ?
ቢንያም :- በርግጥ ብዙ ሳምንት መርተዋል እኛንም ስጋት ውስጥ ከተውን ነበር ። ነገር ግን በሁለተኛው ዙር እርስ በርስ እንገናኝ ስለነበር እነሱን አሸንፈን መሪ እንደምንሆን እርግጠኞች ነበረን ፈጣሪ ይመሰገን ተሳክቶልናል ።
ሀትሪክ :- የአመት ልፋታችሁን ውጤት ለማየት ሁለት ነጥብ ብቻ ማግኘት ነው የቀራቹ በዚህ ሰዓት የቡድኑ ስሜት ምን ይመስላል ?
ቢንያም :- አሁን ከምነግርህ በላይ ደስ የሚል መንፈስ ነው ቡድናችን ላይ ያለው ። የሁላችንንም ህልም ልናሳካ ጫፍ ደርሰናል ። ያለን ህብረት መዋደድ መተሳሰብና መከባበር በጣም ነው ደስ የሚለው በቀሪ ጨዋታወች ደስታችንን ሙሉ እንደምናደርግ እርግጠኛ ነኝ ።
ሀትሪክ :- አሁን ደግሞ ወደ አንተ እንመለስና በእግር ኳስ ህይወትህ ማንን እያየህ ነው ያደከው ?
ቢንያም :- ልጅ እያለው ዳንግላ ውስጥ ብዙ ባለተሰጥኦ ተጫዋቾችን አይ ነበር ከዛ የውጭ ኳስ ማየት ከጀመርኩ በኋላ ግን በጣም የምወደው ዣቪ ኸርናንዴዝን ነው ። አጨዋወቱ በጣም ነው የሚስበኝ እናም ሁሌ እንደ ዣቪ መጫወትን እያሰብኩ ነው ያደኩት ።
ሀትሪክ :- ቡድናቹ ውስጥ አዝናኙ ተጫዋች ማነው ?
ቢንያም :- ብዙ አሉ ነገር ግን አብዱለጢፍ ይበልጥብኛል ያለሱ ጨዋታ አይደምቅም ። በቃ እሱ ካለ ሁሌም ትስቃለህ ።
ሀትሪክ :- ዘናጩስ ተጫዋች ማነው ?
ቢንያም :- ሁሉም ዘናጮች ናቸው መምረጥ ራሱ ከባድ ነው ምረጥ ካልከኝ ግን ያሬድ ዳርዛ ።
ሀትሪክ :- በመጨረሻ የምትለው ነገር ካለ ?
ቢንያም :- ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን እኛ የሚያምርብን ተዋደን ተፋቅረን ተከባብረን ስንኖር ነው ። እግዚአብሔር ለሀገራችን ሰላም ይስጣት እላለው ።
ሀትሪክ :- ማመስገን የምትፈልገው ካለ ?ቢንያም :- በመጀመሪያ ፈጣሪን እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ በመቀጠል በብዙ ነገር የሚደግፉኝን ቤተሰቦቼን አመሰግናለሁ ። የኢትዮጵያ መድኅን የቡድን አባላት ተጫዋቾች የአሰልጣኞች ስታፍ እንዲሁም በእግር ኳስ ህይወቴ እዚህ እንድደርስ ድጋፍ ያደረጉልኝን በሙሉ አመሰግናለሁ ። በተለይ
የኢትዮጵያ መድኅን የቡድን አጋሮቼን አመት ሙሉ ያደረግነውን ተጋድሎ ፍሬ ለማየት ከጫፍ ስለደረስን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እወዳለሁ ። በጣም ነው የማመሰግናችሁ እወዳችኋለሁ ማለትም እፈልጋለሁ ። እናንተም አክብራችሁኝ እንግዳ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ ።