እግር ኳስን መጫወት የጀመረው በክለብ ደረጃ ለአርሲ ነገሌ፣ ለመከላከያ፣ ለመቐለ 70 እንደርታና ለወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ እግር ኳስ ክለቦች ነው። በዘንድሮ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የእግር ኳስ ወድድሩ አሸናፊ በመሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክን ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያልፍ ካስቻሉት ተጨዋቾች መካከል ስሙ ይጠቀሳል።
በቅርብ አመታት በርካታ ሚሊዮን ተከታዮች ባሉት የቻይናው ቲክቶክ የስልክ መተግበሪያ ላይ ብዙ ሺ ተከታዮቹን አፍርቷል ። የዛሬው የሀትሪክ ስፖርት እንግዳችን ግዙፉ ሁለገብ ተጨዋች ካርሎስ ዳምጠው ነው። ከሀትሪክ ስፖርት ድህረገፁ ጋዜጠኛ ኤርሚያስ ምስጋናዉ ጋር በነበረዉ ቆይታ በተለይ ከሰሞኑ ስሙ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ስለመያያዙ ፣ ከሶስት ወራት ቆይታ በኋላ ስለሚጠናቀቀዉ ዉሉ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዝርዝር ሀሳቦችን አካፍሎናል።
ሀትሪክ :- በመጀመሪያ የውድድር አመት ከኤሌክትሪክ ጋር ጊዜው እንዴት አለፈ ?
ካርሎስ :- የውድድር አመቱ እጅግ በጣም ጥሩ ነበር ፤ እንደሚታወቀው እያንዳንዱ ክለብ የራሱ የሆነ ዕቅድ ይኖረዋል ፤ እኛም ኤሌትሪክን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መመለሰ ነበር ዕቅዳችን፤ ያንንም በሚገባ አሳክተነዋል። ዉድድሩን በተመለከተ ሀድያ ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ላይ ቡድናችን እጅግ ጥሩ የነበረና ከሌሎች ክለቦችም የተሻልን መሆናችንን ያሳየንበት በዉጤትም ደረጃ ጥሩ ላይ ነበርን ፤ ባህርዳር ላይ የተደረገዉ ሁለተኛዉ ዙር ግን ትንሽ ከበድ ይል ነበር። ያዉ ታች ያለዉም ላለመዉረድ ከላይ ያለዉም ሻምፒዮን ለመሆን ሌሎቹም መሐል ሰፋሪ ሆነው ለመጨረስ በሚል ፍክክሩ በጣም ያየለበት ጊዜ ነበር። ያም ሆኖ ግን ቡድናችን በወጣቶች እና ልምድ ባላቸዉ ልጆች የተዋቀረ ስለሆነ ሻምፒዮን መሆን ችለናል።ሀትሪክ :- ስለዚህ የካርሎስ ምርጡ አመት ይሄ ነበር ማለት ይቻላል?
- ማሰታውቂያ -
ካርሎስ :- በእስካሁኑ የእግርኳስ ህይወቴ በርካታ ጥሩ የሚባሉ አመታትን አሳልፌያለሁ ብዬ አስባለሁ። በርከት ላሉ አመታት ለተለያዩ ክለቦች መጫወትም ችያለሁ። እንደሚታወቀዉ አምና ከመከላከያ ጋር ሻምፒዮን የሆንበት አመት ጥሩ ነበር ዘንድሮ ደግሞ ታላቁ ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ሊጉ እንዲያድግ የበኩሌን አስተዋጽኦ ተወጥቻለሁ ብየ አስባለሁ ጎሎችንም ማስቆጠር ችያለሁ። ከዚህ በበለጠ ግን ይሄንን ገናና ክለብ ወደ ሚገባዉ ቦታ እንዲመለስ ከክለብ አጋሮቼ ጋር በመሆን የበኩሌን በማድረጌ እና ክለቡን ወደ ሊጉ በማሳደጌ አመቱ ለኔ ልዩ ነበር ማለት እችላለሁ።
ሀትሪክ :- አምና ከመከላከያ ጋር ሻምፒዮን መሆን ችለህ ነበር ነገር ግን በዚያው አመት ክለቡን ለቀህ ወደ ኢትዮ ኤሌትሪክ አምርተሀል ይህ እንዴት ሆነ ? ከመከላከያ ጋርስ ለምን አልቀጠልክም ?
ካርሎስ :- በእርግጥ እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም ተጫዋቾች ነበሩ ዉል እንደሚታደስልን ነበር የምናዉቀዉ ፤ ነገር ግን ነገሮች አሰልጣኙም በፈለገዉ መንገድ ባለመሄዳቸዉ ምክንያት ክለቡን ለመልቀቅ ተገድጃለሁ። በሰዓቱ ከሌሎች ክለቦችም የሚመጡ ጥያቄዎች ነበሩ ነገር ግን ምርጫየን ወደ ኢትዮ ኤሌትሪክ አድርጌ ክለቡን ለመቀላቀል ችያለሁ።ሀትሪክ :- እንደሚታወቀው ፣ ካርሎስ በፕሪሚየር ሊጉ ላይ እንዲሁም በከፍተኛ ሊጉ ላይ በርከት ላሉ አመታት መጫወት ችለሃል። እስኪ የሁለቱን ሊጎች ልዩነት ንገረኝ ?
ካርሎስ :- ልዩነት አለ ይሄ ግልፅ ነዉ። በተለይ አሁን DSTV ከመጣ በኋላ ደግሞ ልዩነቱ ሰፍቷል። ፕሪሚየር ሊጉ ላይ ብዙ አማራጮችን ይዘህ ነዉ የምትጫወተዉ ከሀገር ወጥቶ ለመጫወት ፣ በብሔራዊ ቡድን ዕይታ ዉስጥ ለመግባት ከመሳሰሉት በተጨማሪም የሚሰጠዉ ትኩረት ፣ የሚዳኙህ ዳኞች ጥራት ፣ የሚያሰለጥኑህ አሰልጣኞች ጥራት ወዘተ ከከፍተኛ ሊጉ አንፃር እጅግ የተሻለ ያደርገዋል። ከፍተኛ ሊጉ ላይ ግን አንድ እና አንድ ሻምፒዮን ሁነህ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ ብቻ ነዉ የምትጫወተው። ሊጉ ላይ ያሉ ትኩረቶች በሙሉ የሉም። ከዚህ በተጨማሪም ከላይ የገለፅኳቸዉ አማራጮችንም ማግኘት አትችልም።
ሀትሪክ :- ከፍተኛ ሊጉ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ቀድሞዉ ክለብህ መከላከያ የመዘዋወር ዕድሉን አጊኝተህ ነበር !! ይህ ምን ያህል ዕዉነት ነዉ ? ዕዉነትስ ከሆነ ለምን ዝዉዉሩ ሳይሳካ ቀረ ?
ካርሎስ :- እዉነት ለመናገር ከመከላከያ ብቻ አልነበረም ከሌሎች ክለቦችም ጥያቄዎች መጥተዉልኝ ነበር ፤ ነገር ግን ከኤሌትሪክ ጋር ዉሌ የሚጠናቀቀው ነሐሴ 30 ነዉ። ስለዚህ ከኤሌክትሪክ ጋር ቀሪ ዉል ስላለኝ ወደ ሌላ ክለብ ላመራ አልችልም ኮንትራቴን አከብራለሁ ፤ ምክንያቱ ይሄ ነዉ።ሀትሪክ :- ስለዚህ ነሐሴ 30 ወልህ የሚጠናቀቅ ከሆነ ከነሐሴ በኋላስ የካርሎስ ማረፊያ ወዴት ይሆን ?
ካርሎስ :- እዉነት ነዉ ዉሌ ነሐሴ ይጠናቀቃል። ነገር ግን በዘንድሮው አመት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከካርሎስ ማግኘት ያለበትን ነገር አግኝቷል ብየ ነዉ የማስበዉ ፤ ክለቡ ወደ ሚመጥነዉ ቦታ እንዲመለስ የበኩሌን ተወጥቻለሁ። አሁንም ለዚህ ታላቅ ክለብ ያለኝን መስጠት እፈልጋለሁ። ኤሌክትሪክ ማለት የትኛዉም ተጫዋች ሊጫወትበት የሚፈልገዉ ክለብ ነዉ። እኔም የዚህ ክለብ አካል በመሆኔ ደስተኛ ነኝ ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በቀጣይ አመትም ከኤሌክትሪክ ጋር እቀጥላለሁ ብየ አስባለሁ።
ሀትሪክ :- እንደሚታወቀው አንተ በርካታ ቦታዎች ላይ የመጫወት አቅም አለህ ይህ አቅም ሁለገብ ተጫዋችነትህ ከየት የመጣ ይሆን ?
ካርሎስ :- እኔን እንደ አዲስ አፍርሶ የሰራኝ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ነዉ። ከእርሱ ጋር አራት አመታትን ያህል አሳልፌያለሁ። አሰልጣኝ ዮሐንስ ለእኔ እጅግ በርካታ ነገሮችን ሰጥቶኛል። የቱ ቦታ ምን እንደሚፈልግ በስነስርዓት ነዉ የሚያሳይህ ፤ ያለህን አቅም ማዉጣት እንድትችል ያደርጋል ፣ ኮንፊደንስ እንዲኖርህ ማድረግ ይችልበታል። የትኛዉንም ተጫዋች መስራት ይችልበታል። አሰልጣኝ ዮሐንስ በቃ የተለየ አሰልጣኝ ነዉ። ለሱ የተለየ ክብር ነዉ ያለኝ። በዚህ አጋጣሚ እጅግ በጣም ላመሰግነዉ እወዳለሁ።
ሀትሪክ :- እንደሚታወቀዉ ቀጣይ አመት በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ተሳታፊ ናችሁ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የዘንድሮውን የሊጉን ፉክክር እንዴት ትገልፀዋለህ ?
ካርሎስ :- ዘንድሮ ከትኛውም ጊዜ በበለጠ ጥሩ የፉክክር መንፈስ እየተመለከትን ነዉ። በተለይ የDSTV ወደ ሀገራችን መምጣት ብዙ ነገሮችን ለዉጧል። እኔም ለሊጉ ቅርብ ነኝ ጨዋታዎችን እከታተላለሁ በተለይ አዳማ ላይ በበረዉ ዉድድር አብዝሀኛዎቹን ጨዋታዎች ስታዲየም እየተገኘዉ ተመልክቻለሁ። በጣም የተሻለ የዉድድር አመት እየተመለከትን ነዉ የሚል ዕምነት አለኝ። ከዚህ ጋር ተያይዞም በርከት ያሉ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችንም አሰልጣኞችንም እየተመለከትንበት ያለ አመት ነዉ።ሀትሪክ :- የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ የትኛው ክለብ ሊያነሳ ይችላል የሚል ዕምነት አለህ ?
ካርሎስ :- ከባድ ነዉ ቢሆንም ግን ከሁለቱ ክለቦች ማለትም ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ከፋሲል ከነማ አያልፍም። ፋሲል ከቅርብ አመታት ወዲህ ሀያልነቱን እያስመሰከረ የመጣ ጥሩ ቡድን ነዉ። እንደዉም ፋሲሎች በደጋፊዎቻቸው ፊት መጫወታቸው የበለጠ አድቫንቴጅ እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል ፤ ያም ቢሆን ግን ጊዮርጊስ ጊዮርጊስ ነዉ !! በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ትልቅ ታሪክ ያለዉ ሊጉንም አስራ አራት ጊዜ ማንሳት የቻለ ቡድን ነዉ። እንደዉም እኮ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊጉን አይምራ እንጅ ከመራ ዋንጫውን ያነሳዋል ነዉ የሚባለው።