የቅ/ጊዮርጊስ የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች የሆነው ደስታ ደሙ በዘንድሮው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው ዙሪያና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አጠር ያለ ቆይታን አድርጎ የሰጠው ምላሽ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፤ ተከታተሉት፡፡
ሀትሪክ፡- ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊጉ ፍፃሜ እንዳገኘ የእረፍት ጊዜህን በምን መልኩ እያሳለፍክ ነው….?
ደስታ፡- የክረምት ወራት እንደመሆኑ መጀመሪያ ላይ ወደ ቤተሰቦቹ በማምራት ነበር ጊዜዬን ከእነሱ ጋር ሆኜ በመጫወት ያሳለፍኩት፤ ከዛም ትንሽ አረፍ ካልኩኝ በኋላ በሳምንት ለ3 እና ለ4 ቀን በግል ደግሞ ከልጆች ጋር ኳስን በመጫወት ወቅቱን በጥሩ መልኩ እያሳለፍኩኝ ነው የምገኘው፡፡
ሀትሪክ፡- ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊጉ በአዲሱ የውድድር ዘመን ሲጀመር ከወዲሁ ያቀድከው ነገር አለ…?
- ማሰታውቂያ -
ደስታ፡- እሱማ እንዴት አይኖርም! ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ስመጣ ብዙ ህልሞች ስንቄ ነው ክለቡን የተቀላቀልኩት፤ ቀደም ሲል ተጫውቼ አሳልፌባቸው ከነበሩት የደደቢት እና የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለቦች ጋር ምንም አይነት የሊግ ዋንጫዎችን ያላገኘው ስለነበር ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ከመጣው በኋላም ዓምና በኮቪድ የተቋረጠውን ውድድር ጨምሮ የእዚህ አመትንም የቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ለራሴ ያጣሁበት የውድደር አመታቶችንም ስላሳለፍኩኝ በጣም የቁጭት ስሜት ኖሮኝ ነው የመጪው አመት የሊጉ ተሳትፎ ላይ የተለያዩ ዋንጫዎችን ስለማንሣት ከወዲሁ እያለምኩኝ ያለሁት፡፡
ሀትሪክ፡- በደደቢት ክለብ የተጨዋችነት ቆይታ ምርጥ የውድድር ጊዜን ብታሳልፍም የሊጉን ዋንጫ ከቡድኑ ጋር ለማንሣት አልቻልክም፤ ወቅቱን አስታውሰህ የምትለን ነገር ካለ…?
ደስታ፡- በሁለት አመታት የቡድኑ ቆይታዬ ጥሩ የውድድር ጊዜን ነበር ለማሳለፍ የቻልኩት፤ በተለይ በ2010 ዓ.ም ላይ የአንደኛውን ዙር በቀዳሚነት ሊጉን መርተን ሳለ ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ነጥብ እየጣልን በመምጣታችንና መንሸራተቱም ስለመጣ በዚህ ምክንያት ቡድናችን ውጤት አጣና የሊጉን የሻምፒዮናነትን እድሉን ሳያሳካ ቀረ፡፡
ሀትሪክ፡- በቅ/ጊዮርጊስ ክለብ የተጨዋችነት ቆይታህ ለአንተ ለየት ያለብህ ነገር ምንድን ነው…?
ደስታ፡- ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የቡድኑ አባላቶች ነው ወደዚህ ቡድን ስትመጣ በኳስ ጨዋታ የሚያጋጥም ቢሆንም ሁሌም መሸነፍ አይደለም የአቻ ውጤት ፍፁም ተቀባይነት የሌለ መሆኑን ነው የተመለከትኩት፡፡
ሀትሪክ፡- ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ዘንድሮ ስታጡ በጣም ተከፋህ…?
ደስታ፡- አዎን፣ ዓምና የኮቪድ ወረርሽኙ ሊጉን አቋረጠው እንጂ ዋንጫውን ልንወስድም ላንወስድም እንችላለን በሚል የመንታ ስሜት ውስጥ በመጓዝ ሊጉ ሳያልቅ ቢጠናቀቅም የዘንድሮን ዋንጫ ለማግኘት ግን በቁርጠኝነት ስሜት ነበር ወደ ውድድሩ ልንገባ የቻልነው፤ ያም ሆኖ ግን እንደ ህልማችንና እንደ እቅዳችን ያሰብነው ነገር ስላልተሳካ ሊጉን በ3ኛ ደረጃ ላይ ሆነን ልናጠናቅቀው ችለናል፡፡
ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስን በቤት ኪንግ ዘንድሮ ዋንጫ አሰጥቶታል የምትለው ነገር ምንድን ነው…?
ደስታ፡- በስኳዳችን ከያዝነው ምርጥ ስብስብ አንፃር እንደ ቡድን በሜዳ ላይ ጥሩ አልነበረንም፤ ያም ነው በውድድር አመቱ ተሳትፎአችን ላይ እኛን ቅ/ጊዮርጊሶችን የሚመጥን ውጤት እንዳናስመዘግብ ያደረገን፡፡
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀድሞ ወደሚታወቅበት ስኬታማነት ለመመለስ ምን ማድረግ አለበት ትላለህ…?
ደስታ፡- የውጤት ማጣታችንን ተከትሎ በሁሉም የቡድኑ ተጨዋቾችና መላው የክለቡ አባላት ዘንድ የቁጭት ስሜት አለ፤ መቆጨት ብቻ ግን ጥቅም የለውም፤ ቁጭት የሚያምረው ሰርተህ ስታሳይበት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ ተጫውተህ ያሳለፍክበት የውድድር ዓመታት እንደ ግል ለአንተ የተሳካ ነው ማለት ይቻላል…?
ደስታ፡- ባሳለፍነው አመት ላይ ሊጉ በኮቪድ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ አበረታች እና ጥሩ እንቅስቃሴን ለቡድኔ እያበረከትኩኝ ነበር፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ከፋሲል ከነማ ጋር የነበረንን ጨዋታ ካደረግኩኝ በኋላ ያጋጠመኝ ጉዳት ለቡድኔ ማድረግ ከሚገባኝ ጨዋታዎች ውስጥ ግማሽ የሚደርሱትን ላከናውን ስላልቻልኩ ለቅ/ጊዮርጊስ የሚጠበቅብኝን ያህል ግልጋሎት ልሰጠው አልቻልኩም፡፡
ሀትሪክ፡- የፋሲል ከነማን የቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮናነት እና የኢትዮጵያ ቡናውን የአቡበከር ናስር የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የኮከብ ተጨዋች መሆንን በሚመለከት ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላ ምን አልክ…?
ደስታ፡- ፋሲል ከነማ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊጉን ማሸነፉ ይገባዋል፤ ምክንያቱም ዘንድሮ እነሱ ብቻ ናቸው ወጥ አቋምን አሳይተው ሊጉን ያጠናቀቁት፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ለእያንዳንዱ ጨዋታም እኩል ትኩረትን የሰጡበት ሁኔታም ለስኬታማነት አብቅቷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡናውን አቡበከር ናስር በተመለከተ ደግሞ እኔ ስላልኩ ሳይሆን መላው የስፖርት ቤተሰቡና የእግር ኳስ ባለሙያዎች እንደዚህም ደግሞ አጠቃላይ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ስለ እሱ ብዙ ብለዋል፤ የተለየ የውድድር ዓመትን ነበር ያሳለፈውና ለአቡኪም ሽልማቱ ይገባዋል ነው የምለው፡፡
ሀትሪክ፡- በቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊጋችን በመተላለፉ ዙሪያ የምትለው ነገር አለ….?
ደስታ፡- የጨዋታዎቹ መተላለፍ መቻል እግር ኳሳችን ላይ አንድ የጨመረው እድገት ነገር አለ፡፡ በቀጣይ ጊዜም ከዚህ በተሻለ ለውጥ እንደሚኖረውም እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ያለህ ውል ሰኔ 30 ተጠናቋል…?
ደስታ፡- አዎን፤ ያም ሆኖ ግን አሁንም የቡድኑ ተጨዋች ያህል ሆኖ ነው ጥሩ ስሜት የሚሰማኝ /ያናገርነው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነበር/፡፡ ከዚህ ቡድን ግር ያልጨረስኳቸው ነገሮች አሉና ከእነሱ ጋር ተስማምቼ የምቀጥል ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ሜዳ ላይ ዝምተኛ ነህ አትናገርም ይሉሃል…?
ደስታ፡- አዎን ብዙዎች እንዲህ ቢሉኝም እኔ ግን በመሰለኝ ነገሮች ላይ እናገራለው፡፡
ሀትሪክ፡- በአቋምህ ዙሪያ የምታሻሽለው ነገር ይኖራል…?
ደስታ፡- የእግር ኳስን ስትጫወት ሁሌም ፍፁምነት የለም፤ የሚሻሻሉ ነሮች አሉና እነዚህን ስለማውቃቸው የመጪው አመት ላይ ተሟልተው የሚመጡ ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- የአውሮፓ ዋንጫን ከተመለከትክ እንዴት አገኘኸው…? የማን ደጋፊስ ነበርክ? ማንስ ሻምፒዮና ይሆናል?…
ደስታ፡- ውድድሩን የጠበቅኩት ያህል ጥሩ ፉክክርን የተመለከትኩበት ነው፤ እንደ ዴንማርክን የመሳሰሉ ቡድኖች አራት ውስጥ የገቡበትና ጀርመንና ፈረንሣይን የመሳሰሉ ቡድኖች ደግሞ የወደቁበትም ነበርና ጨዋታዎቹን ተገማች አላደረጋቸውም፤ በውድድሩ ተሳትፎ የእኔ ደጋፊነት ለጣሊያንና ለፖርቹጋል ነበር፤ አንዷ ቡድኔ ብትወድቅም አንዷ የምደግፋት ጣሊያን ለዋንጫ ስላለፈች በጣም ደስ ነው ያለኝ፤ ጣሊያንም ዋንጫውን ታነሳለች፡፡