” ዘንድሮ እኔን እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ወደ ሚገባን ሊግ ማሳደግ ነው ዕቅዴ “
” ወደ ሜዳ ከገባው በኋላ ወንድሜ ነው ብዬ ዝም አላልኩትም “
” ለኔ አርአያዎቼ ወንድሞቼ ናቸው ” ፀጋ ደርቤ /ኢትዮ-ኤሌክትሪክ /
የ2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር የመጀመሪያ ዙር ውድድር መጠናቀቁ ይታወቃል ። በመጀመሪያው ዙር ውድድር ላይ ድንቅ ብቃታቸውን ያስመለከቱትን ወጣት ተጫዋቾችን ከየምድብ የመረጥን ሲሆን በምርጫው ላይ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ተሳትፈውበታል ። በተከታታይ ሶስት ክፍልም ከሶስቱም ምድቦች ምርጥ ተጫዋቾች ጋር ያደረግነውን ቃለ-መጠየቅ ወደ እናንተ እናደርሳለን ።
- ማሰታውቂያ -
በሰበታ ከተማ በተካሄደው የምድብ 1 የመጀመሪያ ዙር ውድድር ላይ ኢትዮ ኤልክትሪክ የምድቡ መሪ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ለቡድኑ ውጤት ጉልህ ሚና ተጫውቷል ። ትውልዱ ከሀላባ የሆነው በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ20 ዓመት በታች ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ መጫወት የቻለው ከክለብ ባለፈም በ2010 ዓ.ም በተመስገን ዳን እየተመራ ለነበረው ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንም ተመርጦ ሀገሩን ወክሎ የተጫወተው ፀጋ ደርቤ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንም ጥሪ ደርሶት ሳይጫወት የቀረበትን ምክንያት እና ከወንድሙ ጋር በተቃራኒ የተጫወተበትን አጋጣሚ እና ሌሎች ከእግር ኳስ ህይወቱ ጋር በተያያዘ ከሀትሪክ ስፖርት ድህረ-ገፅ ጋር ያደረገው ቆይታ እንዲህ ቀርቧል ።
ሀትሪክ :- በመጀመሪያ ራስህን ለሀትሪክ ቤተሰቦች አስተዋውቅልን ?
ፀጋ :- ፀጋ ደርቤ እባላለው ተወልጄ ያደኩት ሀላባ ከተማ ማዶ የሚባል ሰፈር ነው ለቤተሰቦቼ የመጨረሻ ልጅ ነኝ ።
ሀትሪክ :- ስለ አስተዳደግህ እና እግር ኳስን የጀመርክበትን አጋጣሚ አጫውተን ?
ፀጋ :- ያው እንደ ማንኛውም ኢትዮጲያዊ ሰፈር ውስጥ በጨርቅ ኳስ እየተጫወትኩ ነው ያደኩት እግር ኳስ የጀመርኩት ደግሞ ጊቢያችን ውስጥ ነው ጊቢያችን ሰፊ ስለነበር ወንድሞቼም አብረውኝ ስለሚጫወቱ እነሱን አይቼ ነው ወደ ኳሱ የገባውት ።
ሀትሪክ :- በግቢያቹ እግር ኳስን መጫወት ከጀመርክ በኋላ ወዴት አመራህ ?
ፀጋ :- ድንገት በራችን ላይ ስጫወት በረከት ሉሉ(ጫላ) የሚባል የሰፈራችን ሰው ጁቬንቱስ ወደሚባል የካቶሊክ ከ13 አመት በታች ቡድን አሰገባኝ ። ቡድናችንም በሀላባ የክረምት ውድድር ተሳታፊ ነበር ። በውድድሩ ላይ ጥሩ ስለነበርን ሀላባን ወክለን ከ15 ዓመት በታች ኮካኮላ ውድድር ሀዋሳ ሄድን ። የኮካ ኮላ ውድድር ላይ ባሳየሁት እንቅስቃሴ የደቡብ ምርጥን ወክዬ አዳማ ላይ በተዘጋጀው ሀገር አቀፍ ውድድር ላይ ተመረጥኩኝ ። አሁንም በሀገር አቀፍ ውድድር ላይ ባሳየሁት ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ለአካዳሚ ለመመረጥ በቅቻለው ።
ሀትሪክ :- እስቲ የአካዳሚ ቆይታህን ንገረኝ ?
ፀጋ :- በአካዳሚ ቆይታዬ በጣም ብዙ ነገርን አግኝቻለው ብዙ ክህሎቶችን አዳብሬያለው ። በ2010 በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የተመራውን ከ17 አመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመመረጥም ችያለው ። ከአካዳሚ ሳልወጣ በ 2011 በምልመላ ወደ ኢትዮ ኤሌትሪክ ከ20 አመት በታች ቡድን ተቀላቅያለው ።
ሀትሪክ :- በ2010 ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባል ነበርክ ። ምን ያህል ጨዋታዎችን አደረክ ? የነበረህስ ጊዜ እንዴት ነበር ?
ፀጋ :- የነበረኝም ቆይታ በጣም አሪፍ ነበር የምድቡን ሶስቱንም ጨዎታዎች ተጫውቻለው ። ከምድብ ግን ማለፍ አልቻልንም ነበር ። ውድድሩ ብሩንዲ ላይ ነበር ።
ሀትሪክ :- በውድድሩ ላይ ግብ አስቆጥረኻል? ለጓደኞችህስ ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችተህ አቀብለኻል?
ፀጋ :- በውድድሩ ላይ ግብ ማስቆጠር አልቻልኩም ነበር ። ነገር ግን በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ ነበር ያደረኩት ያንንም አሰልጣኜ በተደጋጋሚ ይነግረኝ ነበር ።
ሀትሪክ :- ለብሔራዊ ቡድን ከ17 ዓመት በታች ብቻ ነው የተመረጥከው ?
ፀጋ :- አዎ ምክንያቱ ደግም የሰውነት አቋሜ ነው ። 2012 ላይ ከ 20 አመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጠርቼ ነበር ነገር ግን ባለኝ ደቃቃ ተክለሰውነት ምክንያት ልቀነስ ችያለው ።
ሀትሪክ :- በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ20 ዓመት በታች ምን ያህል ጊዜ ቆየህ ?
ፀጋ :- ሁለት አመት ነው የቆየሁት ነገር ግን ሁለተኛውን አመት ዋናው ቡድን ሆኜ ከ20 አመት በታች ውድድር ላይ እየወረድኩ ነበር የተጫወትኩት ።
ሀትሪክ :- በስንት ዓ.ም ነው ወደ ዋናው ቡድን ያደከው?
ፀጋ :- 2012 ነበር ያደኩት ነገር ግን በጊዜው የነበረው አሰልጣኝ አልተጠቀመብኝም ነበር በትክክል አደኩ ብዬ ማስበው በ2013 ነው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ወደ ክለባችን ከመጣ በኋላ ማለት ነው።
ሀትሪክ :- በ2013 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ድንቅ ብቃትህን አሳይተኻል ይሄ ከምን የተነሳ ነው?
ፀጋ :- ከ20 አመት በታች ውድድር ነው ቀጥታ ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመጫወት የመጣሁት እና ለውድድሩ አሰልጣኜ ከሚሰጠኝ የተለያዩ ስልጠናዎች በተጨማሪ በግሌ እሰራ ነበር ። በግል መስራቴም ውድድሩ ላይ በሚገባ ጠቅሞኛል ።
ሀትሪክ :- ምን ያህል ጎሎችን አስቆጠርክ? ለጓደኞችህስ ምን ያህል ኳስ አመቻችተህ አቀበልክ?
ፀጋ :- በውድድሩ አምስት ጎሎችን ማስቆጠር ችያለሁ ሰባት የሚሆኑ ኳሶችን ደግሞ ለጓደኞቼ ማቀበል ችያለሁ ።
ሀትሪክ :- የትግራይ ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ አለመሳተፋቸውን ተከትሎ ሀዋሳ ላይ በተደረገው ውድድር በድጋሚ ድንቅ እንቅስቃሴ አድርገኻል ። ለጨዋታዎቹ የተለየ ዝግጅት አድርገህ ነበር ?
ፀጋ :- አዎ ምክንያቱም ክለባችንን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ የተገኘ ትልቅ አጋጣሚ ነበር። አሰልጣኜም ለውድድሩ በአግባቡ እንድዘጋጅም ያግዘኝ ነበር ። በዚህ ምክንያት ነው ጥሩ መንቀሳቀስ የቻልኩት ።
ሀትሪክ :- የ2013 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድባቹ ኮከብ ተጫዋች ተብለህ ተመርጠኻል ። ኮከብ ተጫዋች መባልህ የፈጠረብህ ስሜት እንዴት ነበር?
ፀጋ :- በጣም ነው ደስ ያለኝ ምክንያቱም ለውድድሩ አዲስ ነኝ ከ20 አመት በታች ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ገና ማደጌም ነበር። በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ለዚህ አይነት ክብር በመብቃቴ ደስ ብሎኛል ። የተሻለ ስራ እንደሰራም ነው ያነሳሳኝ ።
ሀትሪክ :- ጠንክሬ መስራቴ ለዚህ ስኬት አብቅቶኛል ትላለህ ?
ፀጋ :- በሚገባ እንጂ ማንም ሰው ሳይሰራ ያገኛል የሚል እምነት የለኝም ። ጠንክሬ በመስራቴ ነው ያገኘሁት።
ሀትሪክ :- የ2014 ዓ.ም ውድድርን እንዴት አገኘኸው ?
ፀጋ :- በጣም አሪፍ ነው ጫና ቢኖረውም ።
ሀትሪክ :- ምን አይነት ጫና ?
ፀጋ :- በእኛ ምድብ ያሉ አብዛኛው ክለቦች ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ ነው የሚጫወቱት። እኛም ካለን አላማ ጋ ተጨምሮ ሀሳብ ይሆናል ።
ሀትሪክ :- ምን ያህል ጨዋታዎችን አደረክ ? ምን ያህል ጎሎችንስ አስቆጠርክ ?
ፀጋ :- አንደኛውን ዙር ዘጠኙንም ጨዋታዎች የመጀመሪያ ተሰላፊ ሆኜ ተጫውቻለው ሁለት ጎሎችን አግብቻለው አንድ ደግሞ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቼ አቀብያለሁ ።
ሀትሪክ :- የወደፊት እቅድህ ምንድነው ?
ፀጋ :- እንግዲህ ወደፊት በሀገራችን ትልቁ ሊግ ላይ መጫወት ነው ከዛም አልፎ በትላልቅ የውድድር መድረኮች ላይ የመጫወት እቅድ አለኝ ግን ዘንድሮ እኔንና ኢትዮ ኤልክትሪክንን ወደ ሚገባን ሊግ ማሳደግ ነው እቅዴ ።
ሀትሪክ :- በእግር ኳስ ህይወትህ አርአያዬ ነው የምትለው ተጫዋች ማነው ?
ፀጋ :- ለኔ አርአያዎቼ ወንድሞቼ ናቸው ተጫዋቾች ናቸው በጣም ነው ምወዳቸው ።
ሀትሪክ:- የት ነው የሚጫወቱት ? ስማቸውስ ? እናም ትንሽ ስለ እነሱም አጫውተን?
ፀጋ :- ታላቃችን ተመስጌን ደርቤ ይባላል ሀላባ ሻሸመኔ ተጫውቷል አሁን ግን በከባድ የጉልበት ጉዳት ምክንያት እግር ኳስ መጫወት አቁሟል ። የኔ ታላቅ አቡሽ ደርቤ ይባላል ሀላባ ከተማ እየተጫወተ ይገኛል እንደውም ዘንድሮ ተቃራኒ ሆነን ተገናኝተናል ።
ሀትሪክ :- እርግጠኛ ነኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ወንድምህን በተቃራኒተት የገጠምከው ። ምን አይነት ስሜት ፈጠረብህ ?
ፀጋ :- አዎ ለመጀመርያ ጊዜ ነው በታሪክ ከስንት አንዴ የሚገኝ ነገር ነው በጣም ነበር ደስ ያለኝ ።
ሀትሪክ :- ከወንድምህ ጋር ከኳስ ጋር የመገናኘት አጋጣሚ ነበር?
ፀጋ :- (ረጅም ሳቅ እየሳቀ) አዎ ነበር
ሀትሪክ :- ምን ተፈጠረ ?
ፀጋ :- (አሁንም እየሳቀ) ያው ሜዳ ውስጥ ስትሆን ሁሉን ነገር ትረሳለክ ። ሜዳ ላይ የተገናኘነው ለማሸነፍ ነው ስለዚህ ወደ ሜዳ ከገባው በኋላ ወንድሜ ነው ብዬ ዝም አላልኩትም የሆነ ሰዓት ላይ ጫን ብዬ ኳስ ነጥቄዋለው ።
ሀትሪክ :- ከሀገር ውጪ የምታደንቀው ተጫዋች ማነው ?
ፀጋ:- ክርስቲያኖ ሮናልዶ
ሀትሪክ :- ትርፍ ጊዜህን በምንድነው የምታሳልፈው ?
ፀጋ :- የተለያዩ የእግር ኳስ ቪዲዮዎችን አያለሁ በልምምድ ሰዓትም እሞክራቸዋለው ። በተጨማሪ እና የፕሌይስቴሽን ጌም በመጫወት ነው የማሳልፈው ።
ሀትሪክ :- ከጨዋታ በፊት የምታደርገው ልምድ አለ?
ፀጋ:- አዎ ለጨዋታ ከመውጣታችን በፊት ፀሎት አደርጋለሁ ።
ሀትሪክ :- በመጨረሻ ማመስገን የምትፈልጋቸውን ሰዎች ማመስገን ትችላለህ
ፀጋ :- በመጀመሪያ ለዚህ ሁሉ ክብር ያበቃኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ ። በመቀጠል ቤተሰቦቼን በጣም ማመስገን እፈልጋለው ።በተጨማሪ ከሰፈር ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያሰሩኝን አሰልጣኞቼን ማመስገን ፈልጋለው ። እናንተም አክብራችሁኝ እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።