በወላይታ ድቻ ክለብ ውስጥ ጥሩ እንቅስቃሴን ከሚያደርጉት ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነው አንተነህ ጉግሳ ስለ ቡድናቸው ስለ ራሱ ስለ ሊጉ ምርጥ ተጨዋች እና ሌሎችን ነገሮች በመጨመር ለሀትሪክ ስፖርት ድረ-ገፅ አስተያየቱን ሰጥቷል።
በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አዲስ አበባ እና ጅማ ላይ ስለነበራቸው የውድድር ተሳትፎ
“በአዲስ አበባ ቆይታችን በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ቡድናችን ጥሩ ሊንቀሳቀስ ቢችልም እንደ ቡድን በመከላከሉ ላይ ክፍተት ስለነበረብን እና በመዘናጋታችን ከአንድ አንድ ጎል ይቆጠርብን ነበር። ይሄ ሊፈጠር የቻለው ተጨዋቾቻችን ወጣቶች ስለሆኑና ጎል ሲቆጠርብንም በፍጥነት ለማንሰራራት ስላልቻሉም ከጨዋታ ሪትም እንወጣ ስለነበርን ነው። ወደ ጅማ ስንሄድ ደግሞ በመከላከሉ ላይ የነበረብንን ችግር ማለትም ሀላፊነቱን ለዛ ስፍራ ላይ ላሉ ተጨዋቾች ብቻ መጣል እንደሌለብን እና ሁላችንም በጋራ እየተከላከልን ማጥቃት እንዳለብን ስላወቅንና ስለተነጋገርንበትም የውጤት ማጣት ችግራችንን በተወሰነ መልኩ ልናስተካክለው ችለናል”።
ወላይታ ዲቻ የክፍተቱን እና ችግሩን ካረመ በቀጣይነት ጥሩ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል
- ማሰታውቂያ -
“ከከዚህ በፊት ጨዋታዎቻችን መካከል አስቆጪ የሚባሉ የውጤት ማጣት ችግሮች ገጥሞናል። በተለይ ደግሞ የምናገኛቸውን የግብ አጋጣሚዎች ካለመጠቀም ጋር። ይሄን ችግር ሙሉ ለሙሉ ከቀረፍን ቡድናችን እግር ኳስን ለመጫወት በጣም በሚያመቸው የባህር ዳር ስታድየም ላይም ሆነ በሌሎች ግጥሚያዎቹ ላይ ጥሩ ውጤት የሚያመጣ ይሆናል”።
ስላለው ወቅታዊ አቋም
“በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እግር ኳስን ገና ተጫወትኩ ብዬ አላስብም። ለቡድኔ ገና ብዙ ነገርንም አላደረግኩም። አሁን ካለኝ ችሎታ በላይም ለክለቤ ጥሩ ነገርን ማድረግ እንደምችልም አውቃለሁና ለዛ በርትቼ እየሰራው ነው”።
ስለ ቡድናቸው ተጨዋቾች
“በወጣት የተገነባ እና ምርጥ የተጨዋቾች ስብስብ ነው ያለን። ሽንፈት ባጋጠመን ወቅት ልጆቻችን ላይ ያላቸውን ችሎታ አውጥተው እንዳይጠቀሙ አድርጓቸው ነበርና በቀጣይ ጊዜ ግን ሁሉም ምርጥነቱን እንደሚያሳይ እተማመናለው”።
ከሶስቱ ወንድማማቾች ማለትም ከአንተ ከቸርነት እና ከሽመክት ምርጡ ተጨዋች
“ወደ እግር ኳሱ ሁለታችንም እሱን አርአያ አድርገን ስለመጣን ምርጡ ተጨዋች ሽመክት ነው”።
ስለ ቸርነት ጉግሳ
“ገና ወጣት እና ጥሩ አቅም ያለው ተጨዋች ነው። በተለይ ክህሎቱና ፍጥነቱ ይገርማል። በደንብ የሚገራው ሰው ካገኘ ደግሞ ከዚህ በላይ መጓዝም ይችላል። እንደ እኔ እይታ ወንድሜ ስለሆነ ሳይሆን ወደ ውጪ ወጥቶም መጫወት ይችላል”።
በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የእሱ ምርጥ ተጨዋች
“የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ነዋ! በጣም አስገራሚ ችሎታ ነው ያለው”።
ከእነሱ ቤተሰብ እና ኳስ ተጨዋቾች ውስጥ ቀልደኛው እና ዝምተኛው
“ቀልደኛው እኔ ነኝ። በባህሪው ደግሞ በዝምታው የሚገዛህ ደግሞ ቸርነት ነው”።
በመጨረሻ
“በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎአችን ከዚህ በኋላም አሁን የያዝነውን የአሸናፊነት መንፈስ እንደምናስቀጥለው እርግጠኛ ነኝ። ከዛ ውጪ ደግሞ ኳሳችን በዲ.ኤስ.ቲቪ መተላለፉ ለእኛ ተጨዋቾች እና ለአሰልጣቾችም ጭምር ጥሩ ነገርን ይዞላቸው ስለመጣ እና ሁሉም ሰው ቤቱ ተቀምጦ ስለሚያየንም ይሄን እድል በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል። በተለይ ደግሞ አሰልጣኞች ከዚህ በኋላ ተጨዋችን ሲያስፈርሙ ሰው ስለጠቆማቸው ሳይሆን በራሳቸው እይታም ጥሩ የሆኑ ልጆችን ስለሚያመጡ ይሄ ለኳሳችን ለውጥ ጥሩ ነገርም ይመስለኛል። በተረፈ አገራችንን ፈጣሪ ሰላም ያድርጋት።