ፋሲል ከነማ ድሬዳዋ ከተማን በበዛብህ መላዮ እና በበረከት ደስታ ሁለት ግቦች 2-0 ካሸነፈ በኋላ የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ መሪነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ፋሲል ከነማ በጅማ በተካሄደው የ11ኛው ሳምንት ጨዋታ ባለድል ሲሆንም ለእዚሁ ቡድን ተጨዋች በረከት ደስታም ያስቆጠራት ግብ ለአዲሱ ክለቡ የመጀመሪያው ሆና ልትመዘገብለትም በቅቷል።
በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድሩን እየመራ ስላለው ፋሲል ከነማ እና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የቀድሞ የአዳማ ከተማ እና በአሁን ሰዓት ደግሞ ለፋሲል ከነማ ቡድን እየተጫወተ ከሚገኘው በረከት ደስታ ጋር ሀትሪክ ስፖርት ድረ-ገፅ አጠር ያለ ቆይታን አድርጋለች።
በአዲስ አበባና በጅማ ከተማ ላይ ስለነበራቸው የውድድር ተሳትፎ
“ይህን በሁለት መልኩ ነው የምመልሰው። ከውጤት አንፃር ከሆነ በጅማ የነበረን ቆይታ በጣም ጥሩ ነበር። አራት ያደረግናቸውን ጨዋታዎች በማሸነፍ በመቶ ፐርሰንት ሪከርድ ውድድራችንን አጠናቀናል። ተከታዮቻችንንም በ5 እና ከዛ በላይ በሆነ የነጥብ ልዩነት እንድንርቃቸው አድርጎናል። ከመጫወቻ ሜዳ አኳያ ከሆነ ግን የአዲስ አበባ ከተማ ቆይታችን የሚሻል ነበር። ምክንያቱም ጅማ ላይ ስንጫወት ሜዳው ለጨዋታ በጣም አስቸጋሪ ስለነበር ነው። ጠዋት ላይ ውሃ ስለሚፈስበት እና ሜዳው አፈርም ስለሆነ ይጨቀይ ነበር። ከሰዓት ላይ ደግሞ ስለሚደርቅ አመቺ ባልሆነ ሁኔታ ነው ስንጫወት የነበረው”።
- ማሰታውቂያ -
በጅማ ቆይታችሁ ስለነበራችሁ ጠንካራና ደካማ ጎን
“ጠንካራው ጎናችን የነበረው የኋላው መስመር ነው። ጎል አልተቆጠረብንም። ድክመታችን የምለው ደግሞ ፊት መስመሩ ላይ ብዙ ኳስ እያገኘን አናገባም ነበር”።
ፋሲል ከነማ በውጤታማነቱ ይቀጥል እንደሆነ
“ለዛ ምንም ጥርጥር የለንም። አሁን የአሸናፊነቱን ሚስጥር እና ቁልፉን ካገኘነው የሳምንታት ዕድሜን እያስቆጠርን ስለሆነና የውጤቱ መምጣት ደግሞ በቡድኑ ተጨዋቾች ላይ ከፍተኛ ተነሳሽነትን ስለፈጠረ እና ሁላችንም ደስተኛ ስለሆንም ጉዞአችን እስከ ዋንጫው ድረስ ነው፤ ካለን ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብ አኳያና ከያዝነውም አጨዋወት አንፃርሞ በመጨረሻ ሻምፒዮና የምንሆነው እኛ ነን”።
በጅማ ከተማ ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአችሁ ለአዲሱ ቡድንህ ፋሲል ከነማ የመጀመሪያ ግብህን ስለማስቆጠርህ
“በጅማ ከተማ ቡድናችን ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች መካከል እኔ የተጫወትኩት በሁለት ጨዋታዎች ላይ ነበር። በአንዱም ላይ ለእኔ የመጀመሪያዋን ግብ ስላስቆጠርኩ በጣም ነው ደስ ያለኝ። በተለይ ደግሞ ይህንን ቡድን በተቀላቀልኩበት የእዚህ ዓመት ቆይታዬ ላይ እስካሁን አንድም ግብም ስላላስቆጠርኩም ነበር ይህን ተከትሎም በደጋፊው አካባቢ ግብ ካለማግባቴ ጋር ተያይዞ ውጥረት እና ጫና ውስጥም ስለነበርኩ ነው ባለፈው ድል ባደረግንበት ጨዋታ ላይ ግብ በማስቆጠሬ የተነሳም ውጥረቱ ስለሚቀንስልኝ ብዬም በጣም ልደሰት የቻልኩት”።
የአዳማ ከተማው እና የፋሲል ከነማው በረከት
“በአዳማ ከተማ ቆይታዬ ምርጥ የሆነን የጨዋታ ጊዜ አሳልፌያለሁ። በአዲሱ ክለብ ፋሲል ከነማ ደግሞ ምንም እንኳን ገና የ10 ሳምንት የጨዋታ ጊዜን ባሳልፍም ተደጋጋሚ ጎል ካለማስቆጠር ጋር በተያያዘ የውጥረት መኖር እኔን የሚገልፅ ነገርን እያየው አይደለሁም። ይሄ በመሆኑም በቀጣይ ጊዜው የባህር ዳር ስታዲየም ጨዋታዎች ላይ ሜዳው ለእንቅስቃሴም ጥሩ ስለሆነ የበፊቱን በረከት ትመለከቱታላችሁ”።
ምርጡ የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተጨዋች
“የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ጎል እያገባም አጨዋወቱም በጣም ደስ ይላልና እሱን ነው የምለው”።
ለፋሲል ከነማ ምርጡ የሊጉ ጨዋታ
“ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያደረግነው ነው። በዛ ጨዋታ ሁለታችንም ጠንካራ ነበርን”።
በመጨረሻ
“ለአዳማ ከተማ ስጫወት ለመጨረሻ ጊዜ ጎል አስቆጥሬ የነበረው ከወልቂጤ ከተማ ጋር በነበረን ጨዋታ ነበር። ለአዲሱ ቡድኔ ደግሞ አሁን የመጀመሪያዬን ግብ ስላስቆጠርኩ የግቧን ማስታወሻነት በጣም ለምወዳት ባለቤት ቤዛዊት ሽመልስ ማድረግ እፈልጋለሁ። ጎሉን እንዳገባ የረዳኝን ፈጣሪዬን ደግሞ ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ”።