“አዳማ ከተማን በሰፊ ግብ ያሸነፍነው ከእረፍት በኋላ ተረጋግተን በመጫወታችን ነው”
“አሁንም ተደጋጋሚ የግብ እድልን መፍጠር ከቻልን እኛን የሚያቆመን ማንም የለም”
ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን /ችምስ/
/ኢትዮጵያ ቡና/
በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ቡና አዳማ ከተማን በአቡበከር ናስር ሶስት እና በታፈሰ ሰለሞን አንድ ግቦች 4-1 ያሸነፈ ሲሆን ቡድኑ ከመሪው ፋሲል ከነማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነትም ፋሲል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እያለሁ በ4 ነጥብ ሊያጠብ ችሏል። ለአዳማ ከተማ ደግሞ አብዲሳ ጀማል ብቸኛውን ግብ አስቆጥሯል።
- ማሰታውቂያ -
የኢትዮጵያ ቡናን ድል አስመልክቶና ከቡድኑ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ እንደዚሁም ስለ ራሱ የሀሰላ ከተማ ተወላጅ ከሆነው የአማካይ ስፍራ ተጨዋቹ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን /ችምስ/ ጋር የሀትሪክ ስፖርት ድረ-ገፅ ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ አናግሮት ተጨዋቹ ምላሹን እንደሚከተለው ሰጥቷል።
ኢትዮጵያ ቡና ባለድል ስለሆነበት የዛሬው ጨዋታ እና በድሉ ስለተሰማው ስሜት
“ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ የተጎናፀፈው የድል ውጤት በጣም አስፈላጊያችን ስለነበር እና ጣፋጭም ስለሆነ ደስ የሚል ስሜት ነው የተሰማኝ። ወደ ጨዋታው ሳመራ በመጀመሪያው አጋማሽ ቶሎ ቶሎ በመፍጠን ወደ እነሱ የግብ ክልል እንደርስ ነበር። ግብ በማስቆጠር ጨዋታውን በዚሁ ክፍለ ጊዜ ውስጥ ለመጨረስም ፈልገን ነበር። ያም ሆኖ ግን አልተሳካልንም። ጭራሽ እንደውም ፈፅሞ ባላሰብንበት መንገድ እነሱ ግብ አስቆጠሩብን። በእረፍት ሰዓት ላይ ግን ባለብን ችግር ዙሪያ ከአሰልጣኛችን ጋር ለመነጋገር በመቻላችን እና አዳማሞ በደረጃው ሰንጠረዥ እታች ከመሆኑ አንፃር ሊያስቸግሩን እንደሚችሉም ስለገመትን በእንቅስቃሴ ደረጃ ተረጋግተን መጫወት እንዳለብን በማወቅ ከመመራት ተነስተን አራት ግቦችን አስቆጥረን ግጥሚያውን በድል ልንወጣው ችለናል”።
ስለተጋጣሚያቸው
“አዳማ አሪፍ ቡድን ነው። እንዲህ አልጠበቅናቸውም ነበር። በተለይ እስከረፍት ሰዓት ጥሩ ነበሩ። ጠንክረውብንም ነው የመጡት”።
ድሉ ይቀጥል እንደሆነ
“ብዙ ቡድኖች ከቡና ጋር ሲጫወቱ በራቸውን ከርችመው ነው እየመጡ ያሉት እንደ አዳማ ከተማ ቀን ክፍት የሆነ ጨዋታን ካገኘን ግን አሸናፊነታችን የሚቀጥል ነው የሚሆነው”።
ለኢትዮጵያ ቡና ከቆይታ በኋላ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ስለመግባቱ
“ልክ ነህ፤ ከዚህ ቀደም ጉዳትን አስተናግጄ ስለነበር ከቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ወጥቼ ነበር። በአሁኑ ጨዋታ ግን የመጀመሪያ ተሰላፊ ሆንኩ ይህ መሰለፌ ምንአልባት እንደ አሰልጣኙ ውሳኔ ሊቀጥልም ላይቀጥልም ይችላል። ግን ሌላ ጉዳት ካላጋጠመኝ ልሰለፍ የምችልበት እድል ይኖረኛል”።
ስለ ጥንካሬያቸው
“እኛ ያለን ጠንካራ ጎን ኳስን ፖሰስ አድርገን መጫወት መቻላችን ነው። በዚህ ከሁሉም ቡድንም እንሻላለንና እንቅስቃሴያችን ቀጣይነት አለው”።
በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለኢትዮጵያ ቡና ከወዲሁ ሶስት ጊዜ ሀትሪክ ስለሰራው እና የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት እየመራ ስላለው አቡበከር ናስር
“ስለ እሱ ምንም ማለት አልችልም። የተለየ በጣም ክስተት የሆነና በጣም ደግሞ ታምረኛ የሆነም ተጨዋች ነው። በዚህ የወጣትነት እድሜው እንዲህ ነግሶ መውጣቱ እድለኛም ተጨዋች ያደርገዋል። ይሄን ብቃቱን እንዲያስቀጥልም ነው የምመክረው”።
ሊያሻሽሉት ስለሚፈልጉት ነገር
“ባለፈው ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ስንጫወት አዳማ ከተማን እንዳሸነፍንበት ግጥሚያችን ተደጋጋሚ የጎል እድሎችን አልፈጠርንም ነበር። አሁን ግን ፈጠርን። በዛም በርካታ ግቦችን አስቆጠርን። በራቸውን ዘግተው ለሚመጡብን ለእንደነዚህ ያሉ ቡድኖች አሁንም ተደጋጋሚ የግብ እድልን መፍጠር መቻል አለብን። ይሄን ችግር ልንቀርፍም ይገባናል። ያን ካደረግን እኛን የሚያቆመን የለም”።
ስለሚቆጩበት ነገር
“በአንድአንድ ጨዋታዎቻችን ላይ በጣልናቸው ነጥቦች ነው። ያን ድል አሳክተን ቢኖር ኖሮ በደረጃው ሰንጠረዥ ከፋሲል ከነማ በላይ በመቀመጥ ሊጉን እንመራው ነበር”።
ስለ ዘንድሮ ግባቸው
“በውድድሩ ላይ ያለን እልምና ግብ ዋንጫውን ለማንሳት ነው። በራሳችንም እድል ነው ልንወሰን የሚገባን። ለዛ ሁሉንም ጨዋታ ማሸነፍ ይኖርብናል። ደግሞም ቡድናችን በሁለተኛው ዙር ጨዋታው በተለየ መልኩ እንቅስቃሴውን አሳድጎ ስለሚመጣና የበለጠም መዋሀዱ ስለሚኖር ሻምፒዮና የመሆን እድሉ አለን”።
ስለ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ
“በጣም የተረጋጋ እና ጥሩ የሆነ አሰልጣኝ ነው። ቡድኑ ጥሩ እግር ኳስን እንዲጫወት የሚፈልግበት እሳቤውም ይገርመኛል። ቡድኑን ሲመራ እንደ ብዙ አሰልጣኞች ክፍተት በሚፈጠር ሰዓት አይቆጣህም፤ አይጮህብህም። ያም እሱን ልዩ ያደርገዋል”።
በቅርቡ ስለፈፀመው ጋብቻ እና ስለ ባለቤቱ
“ጋብቻዬ በጣም አሪፍ ነበር። እንግዲህ የትዳር ህይወትን በጥሩ መልኩ ጀምረነዋል። ባለቤቴን ረድሄት ተሾመን በተመለከተ የደብረዘይት ልጅ ናት አየር ሀይል ስጫወትም ነው የተዋወቅነው። በጣም አሪፍ ልጅ ናት። ፎጋሪም ነች። ደብሮኝ የገባው ቀን ለዛ ባለው ጨዋታዋ ሳቅን ትፈጥርልኛለች”።
በመጨረሻ
“በዘንድሮው የውድድር ዘመን ቡና ጥሩ ጊዜን ከውጤታማነት ጋር እንዲያሳልፍ ምኞቴ ነው። ለዛ በጣም ጠንክረን መስራትም ይኖርብናል። ፈጣሪም ይርዳን”።