“ወላይታ ድቻ ደረጃ ውስጥ ገብቶ ሊጉን እንደሚያጠናቅቅ አስባለሁ”
“የቤታችን ምርጡ ተጨዋች እኔ ሳልሆን አይድከሜው ሽመክት ጉግሳ ነው”
ቸርነት ጉግሳ /ወላይታ ድቻ/
ለወላይታ ድቻ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎ ጥሩ እንቅስቃሴን ከሚያሳዩት ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ቸርነት ጉግሳ ስለ ቡድናቸው፣ ስለ ራሱ እና ስለ ቀጣይ የሁለተኛው ዙር ተሳትፎአቸው ይናገራል።
- ማሰታውቂያ -
የወላይታ ድቻው አማካይ ለፋሲል ከነማ እየተጫወተ ያለው የሽመክት ጉግሳ እና ሌላኛው የቡድን አጋሩ አንተነህ ጉግሳ ታናሽ ወንድም ሲሆን ተጨዋቹ ከቤተሰቡ ጋር በተያያዘም በተጨማሪ የሚለው ይኖራል ተከታተሉት።
የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በድል ስለማጠናቀቃቸው እና ግብ ስለማስቆጠሩ
“ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ያደረግነውን ጨዋታ ከግጥሚያው ሶስት ነጥብን ለመውሰድ ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። በሁለታችን ቡድኖች መካከልም ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴም ታይቷል። ያም ሆኖ ግን የኛ ቡድን በጨዋታ ከነሱ በተሻለ መልኩ ጥሩ ስለነበር በመጨረሻ ድል ቀንቶናል። ያገኘነው ውጤትም በጣም አስደስቶናል። ከዛ ውጪ ይሄ ጨዋታ ካራቀኝ ጎል አስቆጣሪነቴም እንድመለስ ስላደረገኝም ለእኔ ድርብ ደስታ ሊሆንልኝም ችሏል”።
ስለ ተጋጣሚያቸው ሀድያ ሆሳህና እና እነሱን ለማሸነፍ ስለቻሉበት መንገድ
“ሀድያዎች ከእኛ ጋር ሲጫወቱ እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነበር ሲሞክሩ የነበሩት። እኛ ያን በማወቃችንና በዛ ላይ ደግሞ የመስመር ላይ እንቅስቃሴያቸውን ልንገድብ ስለቻልን ያ ለስኬት አብቅቶናል”።
ስለ አንደኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታቸው
“ከ ሲዳማ ቡና ጋር ያደረግነውም ያ ጨዋታ የግድ ሶስት ነጥብ በጣም ያስፈልገን ነበር። በጊዜም ነው ግብ አስቆጥረን ግጥሚያውን ልንጨርስ የነበርነው ግን ባልነው መልኩ አልተሳካም። በኋላ ላይ ግን ከባድ በነበረው በዛ ጨዋታ የሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግብ አግብተን ልናሸንፍ ችለናል። ከእነሱ እኛ የተሻልንም ስለነበርን ውጤቱ ይገባናል። ይሄ ጨዋታ ሀድያን ካሸነፍንበት ፍልሚያም ተመሳሳይ ሆኖብኛል”።
ከሲዳማ ቡና ጋር ስላደረጉት የአንደኛው ዙር የመጨረሻ ተጋጣሚያቸው
“የመስመር ጨዋታቸው ጥሩ እንደሚሆን እናውቅ ነበር። ያን የመጫወቻ ቦታም ነበር ያሳጣናቸው። ከዛም ባሻገር ባለፉት ተከታታይ ግጥሚያዎችም ተሸንፈው ስለመጡ በስነ ልቦና ተጎድተው ነበርና ጥሩ ሊጫወቱ አልቻሉም”።
ስለ ሊጉ የመጀመሪያው ዙር ተሳትፎአቸው እና የዘንድሮን ውድድር በምን መልኩ እንደሚያጠናቁ
“በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ ነበርን። ግብ ማስቆጠሩ ላይ ግን የአጨራረስ ችግር ነበረብን። ከዛም ውጪ ከአንድ አንድ ግብ ይቆጠርብን ነበር። ይሄን አሁን ላይ እያሻሻልን በመምጣታችን የአንደኛው ዙር ሲጠናቀቅ በደረጃው ወገብ ላይ ነበር ልንገኝ የቻልነው። አሁን በደረጃው እየተሻሻልን ነው። ባለፉት ሶስት ዓመታት ቡድናችን ወራጅ ቀጠና ላይ ሆኖ ነበር ግጥሚያዎቹን በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ሆኖ ሲያደርግ የነበረው ከዚህ በኋላ ግን ይበልጥ እየተሻሻልን ስለምንመጣ ያ አይደገምም። ብዙም የነጥብ ርቀት በሌለው የዘንድሮ ተሳትፎአችንም የደረጃ ተፎካካሪ ሆነን ማጠናቀቅም ነው ዋንኛ አላማችን”።
ወጣት ተጨዋቾች ቡድናቸው ውስጥ ስለመብዛቱ
“የእውነት ነው። ብዙዎቻችን ከስር ጀምሮ አብረን በማደግ ነው የመጣነው። የዚሁ የስራ ባለቤት ደግሞ ከክለባችን ጋር የተለያየው እና በጥሩ አሰልጣኝነቱ የሚታወቀው እንደ ወንድምም ይቀራረብ የነበረው አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ነበርና በዚሁ አጋጣሚ ላደንቀው እፈልጋለሁ”።
ከቤተሰባቸው ውስጥ ምርጡ ተጨዋች እሱ እንደሆነ
“ምርጡ ተጨዋች ሽመክት ጉግሳ እንጂ እኔ አይደለሁም። እሱ ከእኛ ይለያል። ደከመኝንም አያውቅም”።
አድንቆ ስላደገው ተጨዋች
“ልጅ ሆኜ ጀምሮ ጌታነህ ከበደን እና ወንድሜን ሽመክት ሲጫወቱ የማየት እድሉ ስለነበረኝ እነሱን አድንቄ ነው ያደግኩት”።
ስለ ቡድናቸው ሲኒየር ተጨዋች ደጉ ደበበ
“እሱ ልምዱን እያካፈለን ነው። በግልም ይመክረናል። አብረነው በመጫወታችንም ለኛ ኩራት ነው”።
ማሻሻል የሚፈልገው
“ለወላይታ ድቻ ከስር ጀምሮ ስጫወት ጎል አገባ ነበር። የመጀመሪያ ግቤንም ሶዶ ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስንጫወት ያስቆጠርኳት ናት። ዘንድሮ ደግሞ ከሀድያ ጋር በመክፈቻው ጨዋታ ላይ ስንጫወት ያቺ ግብ በስሜ የተመዘገቡትን ግቦች 7 አድርሶልኝ የነበረ ቢሆንም በድጋሚ አሁንም ከሀድያ ጋር ስንጫወትና ግብን እስካስቆጥር ድረስ ሌላ ግብ አልነበረኝምና ከግብ የምርቅበትን ይህን ችግሬን ማሻሻል እፈልጋለሁ”።
ስለ ወደፊት ምኞቱ
“የእግር ኳስ ጉዞዬ በሀገር ውስጥ ደረጃ ብቻ እንዲገደብ አልፈልግም። ለብሄራዊ ቡድንና ውጪ ሀገር ወጥቼም መጫወትን ነው የምፈልገው”።
በመጨረሻ
“ቤተሰቦቼ በኳሱ እዚህ እንድደርስ ያደረጉልኝ አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ነው። እነሱ በክብር ይመስግኑልኝ። ከዛ ውጪ ሌላ ማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር ቡድናችንን በሀላፊነት የተረከበው አዲሱ አሰልጣኛችን ዘላለም ሽፈራው በየጨዋታው ጠንክረን በመቅረብ ሜዳ ላይ በአካል ብቃቱም ሆነ በስነ ልቦናው ረገድ የሚያደርግልን ድጋፍ ከፍ ያለ ስለሆነ በእሱ ታግዘን ጥሩ ውጤት እንደምናመጣ አምናለሁ”።