በሐረር ህፃናት ማሳደጊያ ነው ያደገው፤ ከልጅነት ዕድሜው አንስቶም እዛ በሚገኘው የእግር ኳስ ሜዳ ላይም ነው ኳሱን በማንከባለል ጀምሮ ዛሬ ላይ የሀገሪቱ ጠንካራ ለሆነው የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን በመጫወትም ላይ የሚገኘው፤ በሐረር ከተማ የተወለደው ሳሙኤል ዩሃንስ ወደ ፋሲል ከነማ ክለብ ከመግባቱ በፊት እግር ኳስን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተስፋ ቡድንና የዋናው ቡድን ጀምሮ ለአማራ ውሃ ስራ፣ ለድሬዳዋ ከተማ፣ ለወልዋሎ በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን በቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ደግሞ ለአሁኑ ክለቡ ፋሲል ከነማ በግራ መስመር ተከላካይም ሆነ በአማካይ ስፍራው ላይ በመጫወት ጥሩ እንቅስቃሴን በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡
የፋሲል ከነማ ክለብን በእነዚህ ሁለት የመጫወቻ ስፍራዎች ላይ ቡድኑን እየጠቀመ የሚገኘውን ይኸውን ተጨዋች ሲዳማ ቡናን ድል ካደረጉበት ጨዋታ በኋላ በአጠቃላይ የሊጉ ጉዞዋቸው ዙሪያ እና ስለ ራሱ እንደዚሁም ደግሞ ሌሎችን ተያያዥ ጉዳዮችን ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ለተጨዋቹ አንስቶለት ምላሾቹን ሰጥቶበታል፡፡
ሀትሪክ፡- በቤት ኪንጉ የአዲስ አበባ ስታድየም የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ፋሲል ከነማ ሲዳማን ቡናን ማሸነፍ ችሏል፤ የሁለታችሁ ጨዋታ ምን መልክ ነበረው? እንዴትስ ለድል በቃችሁ?
ሳሙኤል፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሲዳማ ቡናን ለማሸነፍ የቻልነው ከእዚህ በፊት በነበሩን ችግሮች እና ክፍተቶቻችንን ላይ ተነጋግረንበት እና ሰርተንበት ስለመጣን ነው፤ ወደ ጨዋታው ሳመራ እኛ ወደ ሜዳው የገባነው ከባህር ዳር ጋር በነበረን ጨዋታ ላይ ነጥብ ጥለን ስለነበር ከእዚህ ጨዋታ የግድ ሶስት ነጥብን ይዘን መውጣት አለብን ብለን ወደ ሜዳ ስለገባን ነው፤ በእዛ መልኩ ለጨዋታው ብንገባም መጀመሪያ ላይ በጣም ተቀዛቅዘን ነበር፤ ከዛ በኋላ ግን የመጫወት ፍላጎታችን ከደቂቃ ወደ ደቂቃ እየጨመረ ሲመጣ እና የምናገኛቸውን የግብ አጋጣሚዎችም የግድ መጠቀምም ስለነበርን በመልሶ ማጥቃት አጨዋወትም ነው ጨዋታውን ለማሸነፍ የቻልነው፡፡
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ፡- ለፋሲል ከነማ በግራ መስመርም በአማካይ ስፍራ ላይም ስትጫወት ተመልክተንሃል፤ ወደ ሁለገብ ተጨዋችነት የሚቃረብ ችሎታ አለህ ማለት ነው?
ሳሙኤል፡- በመጀመሪያ በእዚህ መልኩ እንድጫወት ያደረገኝ በወልዋሎ በነበርኩበት ሰዓት አሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ ነበር፤ መጀመሪያ የግራ መስመር ተከላካይ ነበርኩ፤ ከዛ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሞከረኝ ጥሩ ስለሆንኩም አጫወተኝ፤ እግር ኳስ ተጨዋች ስትሆን ሁሌም በየሁሉም ስፍራ ለመጫወት ራስህን ዝግጁ ማድረግ አለብህ እኔም ለሚያሰለጥኑኝ አሰልጣኞች ሁሉ ራሴን በምን መልኩ ዝግጁ አድርጌ መቅረብ እንዳለብኝ በማወቅ ነው ጥሩ በመንቀሳቀስ ላይ ያለሁት፡፡
ሀትሪክ፡- የዘንድሮውን እና የዓምናውን ቡድናችሁን ስታነፃፅረው በምን መልኩ አገኘኸው?
ሳሙኤል፡- ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ቡድናችን ኮቪድ እስከገባበት ጊዜ ድረስ በጥሩ አቋም ላይ ነው ይገኝ የነበረው፤ ውድድሩ ባይቋረጥ ኖሮ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት የሚያስችለንም ምርጥ ቡድን ነበረን፤ ወደ ዘንድሮ ቡድናችን ስመጣ ግን አሁን ላይ የሊጉ ጨዋታዎቹ በየቀናት ልዩነቶች የሚካሄዱ ስለሆኑና ድካምም ስላለ ውድድሩ እየከበደ ነው የመጣው፤ ይሄንንም አሁን ላይ እኛ በደንብ አውቀናል፤ ስለዚህም ከእዚህ በኋላ ለሚኖሩት እያንዳንዱ ጨዋታዎች ጥንቃቄ ያለበትን እንቅስቃሴ በማድረግ እና ከአሰልጣኛችን የሚሰጠንን ታክቲክም በደንብ አድርገንም በሜዳ ላይ ለመተግበር በመሞከር የአምናው አይነት ቡድናችንን ለመመለስ ጥረትን እያደረግን እንገኛለን፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማን በቤት ኪንጉ ፕሪምየር ሊግ የት ድረስ ይጓዛል ብለን እንጠብቀው?
ሳሙኤል፡- የሊጉን ዋንጫ እስከመውሰድ ነዋ! ዋንጫውን ማንሳታችን ደግሞ አይቀርም፤ የከዚህ በፊት ቁጭቶች አሉብን፤ ለዛም በእያንዳንዱ ጨዋታዎች ላይም ከዚህ በኋላ አንድ ነጥብን ላለመጣልም በሚገባ ተዘጋጅተናል፡፡
ሀትሪክ፡- ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያደረጋችሁት እና አቻ የተለያያችሁበት ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር የተደረገበት ነበር፤ 2 የእነሱ ተጨዋቾች በቀይ ካርድ ወጥተውም ነው ውጤቱ የተመዘገበው፤ ያን ጨዋታ በተመለከተ ያን ዕለት ምን አልክ?
ሳሙኤል፡- የእኛ እና የባህር ዳር ከተማ ጨዋታ ደርቢ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ፍልሚያ ነበር፤ ፋሲል ደግሞ ትልቅ ቡድን ከመሆኑ አኳያ ማንኛውም ቡድን ከኛ ጋር ሊጫወት ሲመጣ ወይ ነጥብ ይዞ ለመውጣት አለያም ደግሞ የአቻነትን ውጤት አስጠብቆ ለመውጣት ስለሆነ ጠበቅ ብሎም ነው የሚመጣው፤ ደርቢ ሲሆን ደግሞ ጨዋታው ምን ሊመስል እንደሚችል የበለጠ አስበው፤ ይህን የደርቢ ጨዋታ ባደረግንበት የእዛን ዕለት እኛ የነበሩብንን ክፍተቶችና ስህተቶች ለመድፈን አልሞከርንም፤ የቁጥር ብልጫውንም መጠቀም አልቻልንም በእዛ ጨዋታ እነዚህ ችግሮቻችን ዋጋ እንድንከፍል ስላደረጉን ግጥሚያውን በአቻ ውጤት አጠናቀናል፤ በውጤቱም ተከፍተናል፡፡
ሀትሪክ፡- በፋሲል ከነማ ተጨዋቾች እና በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ መካከል ልዩነቶች እና ችግሮች አሉ ይባላል..ምን ያህል እውነት ነው?
ሳሙኤል– በአሰልጣኛችን የሚሰጠንን የጨዋታ ታክቲኮችን በሜዳ ላይ ከመተግበርና ካለመተግበር አኳያ ካልሆነ በስተቀር ያንን ያህል የጎላ ችግርንም ሆነ ልዩነትን እስካሁን በቡድናችን ውስጥ አልተመለከትኩም፤ ታክቲኩን ያለመተግበር ችግሩ ደግሞ የእኛ ተጨዋቾች ነው፤ እንዲህ ያሉ ነገሮች ደግሞ በእግር ኳሱ ውስጥ የሚያጋጥሙ ናቸውና በቀጣይነት በሚኖሩት ጨዋታዎች ታክቲኮቹ ሙሉ ለሙሉ መተግበራቸው አይቀሬ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የፋሲል ከነማ የተወሰኑ ደጋፊዎች አሰልጣኝ ስዩም ከበደን ከባህር ዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ሲቃወሙት ተመልክተናል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
ሳሙኤል፡- እንዲህ ያሉ ተቃውሞዎች እግር ኳስ ላይ የሚጠበቁ ናቸው፤ በተለይ ደግሞ ውጤት እምቢ ሲልህ ሊደጋገሙም ይችላሉ፤ አሰልጣኝ ስዩም ላይ ይሄ ተቃውሞ ገና የሊጉ በርካታ ጨዋታዎች ባልተካሄዱበት ሁኔታ ሊነሳ ቢችልም በባለፈው ግጥሚያ ላይ ደግሞ ያገኘነው የድል ውጤት ለዛ ማሳያ ስለሆነ ይሄን አልተመለከትንም፤ በቀጣይ ግጥሚያዎች ላይም እንዲህ ያሉ ተቃውሞችን ማስቆም የምንችለው ደግሞ በተለይ እኛ ተጨዋቾች ስለሆንን ከአሰልጣኙ ጋር የሚኖረንን ግንኙነት የበለጠ እያጠናከርን በማስጓዝ ምርጡን ቡድናችንን በቅርብ ጊዜ ውስጥ በሜዳ ላይ እንደምናስመለከት በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና ከእነሱ አንድ ተጨዋች በቀይ ካርድ ወጥቶ ተሸንፋችሁ ነበር?
ሳሙኤል፡- የእውነት ለመናገር ያን ሽንፈት በፍፁም አልጠበቅነውም ነበር፤ ቡናዎች በጨዋታው ላይ ፈርተውንም ነበር፤ በኋላ ላይ ግን እግር ኳስ 90 ደቂቃ ሙሉ የምታደርገው ፍልሚያና ጥረት ስለሆነ ቡናዎች ያን በመጠቀም ሊያሸንፉን ችለዋል፡፡
ሀትሪክ፡- በፋሲል ከነማ ቆይታህ ቡድንህን የቱን ያህል ደረጃ ልታገለግለው ዝግጁ ነህ? የእግር ኳሱ ግብህና እልምህስ እስከምን ድረስ ነው?
ሳሙኤል፡- ፋሲል ከነማ በመጀመሪያ ደረጃ የሀገሪቷ ትልቅ ቡድን ነው፤ ወደዚህ ቡድን ስመጣም የመጀመሪያ እቅዶቼና እልሞቼ ከዚሁ ቡድን ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት አለብኝ ብዬ ስላሰብኩ ለቡድኑ በሁለገብ የጨዋታ ሚና ተሰልፌ በምጫወትባቸው ግጥሚያዎች ሁሉ ከእኔ የሚጠበቀውን ለማድረግ ራሴን በሚገባ እያዘጋጀው ነው፤ በእዚህ ቡድን ቆይታዬም በአሁን ሰዓት አበረታች የሆነን እንቅስቃሴም እያሳየው ነው፤ ይሄን ብቃቴን የበለጠ አሳድጌው እስከ ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ ተጨዋችነት እና በፕሮፌሽናል ወጥቶ እስከመጫወት ደረጃም ልወስደው እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ….?
ሳሙኤል፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት አሁን ለመጣሁበት መንገድ ላመሰግናቸው የምፈልጋቸው ሰዎች አሉ፤ የመጀመሪያው በሐረር ህፃናት ማሳደጊያ እንደማደጌ እንደ አባት እና እናት ሆኖ ያሳደገኝ አሰግድ በረገግ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፤ ከእሱ በመቀጠል ደግሞ አሰልጣኝ ደግ አረገ በባህር ዳር ከተማ ውስጥ የሚያሰለጥነው ጣና ባህር ዳር የሚባል የፕሮጀክት ቡድን ነበረውና እሱ ጋር በታዳጊነት እድሜዬ ስለሰለጠንኩና ለዛሬም ደረጃ እንድበቃ መሰረትን ስለጣለልኝ እሱን አመሰግነዋለሁ፤ ከእነዚህ ውጪ ደግሞ ችሎታዬን የበለጠ እንዳሳድግ ያደረገኝን አሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌን፣ እንደዚሁም የአሁኑ አሰልጣኝ ስዩም ከበደንና ሙና መሐመድን በጣም ላመሰግናቸው እፈልጋለው፡፡