“ጉዳቱ ሲደርስብኝ በደመነፍስ ውስጥ ስለነበርኩ ምንም ነገርን አላስታውስም፤ አሁን ወደ ጤንነቴ ተመልሻለሁ”
“ሙሉ የኢትዮጵያ ህዝብን የቡድኔን ጓደኞች እና ቤተሰቦቼን ከጎኔ ስለነበሩ አመሰግናችኋለሁ”
ታሪክ ጌትነት /አዳማ ከተማ/
በመሸሻ ወልዴ
- ማሰታውቂያ -
የአዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለብን በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ለማገልገል ቡድኑን የተቀላቀለው የቀድሞው የደደቢት፣ የወላይታ ዲቻ፣ የሀዲያ ሆሳዕናና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት ባሳለፍነው እሁድ ቡድኑ ከወላይታ ድቻ ጋር ባደረገው ጨዋታ ከራሱ ቡድን ተጨዋች ከአሚን ነስሩ ጋር ጭንቅላት ለጭንቅላት በመጋጨታቸው የታሪክ ምላስ ወደ ውስጥ ታጥፎ የመተንፈሻ አካሉን በመዝጋት ላይ ባለበት ሰዓትና መተንፈስም እያቃተው በሚገኝበት ሰዓት በቅርቡ ከሚገኙት የቡድኑ ተጨዋቾች መካከል በላይ እና ደሳለኝ ደበሽ ደርሰው የተጨዋቹን ህይወት የታጠፈውን ምላሱን በእጅ በማውጣት እና የተጨዋቹን ህይወት የታደጉት ሲሆን ታሪክ በአሁን ሰዓት ላይ አስፈላጊውን ህክምና በማድረግ ወደ መልካም ጤንነቱ እየተመለሰ መሆኑን በመናገር ላይ ይገኛል።
የአዳማው ግብ ጠባቂ ከወላይታ ድቻ ጋር ሲጫወቱ ደርሶበት ስለነበረው ከፍተኛ ጉዳትና ራሱን ስለመሳቱም ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ
“ያን ዕለት ደርሶብኝ ስለነበረው ጉዳት ፈፅሞ ራሴን ካለማወቄ እና በደመነፍስ ውስጥም ስለነበርኩ ወደ ኋላ መለስ ብዬ ምንም ነገርን አላስታውስም። እኔ የማስታውሰው መስመሩ ላይ ቅጣት ምት መሰጠቱን ብቻ ነው። በኋላ ላይ ግን ስለ ደረሰብኝ ጉዳት ሁሉንም ነገር ላውቅ የቻልኩት ወደ መልበሻ ክፍል ከተወሰድኩ በኋላ እኔን ልታይ የተጠራች ነፍሰ ጡር የሆነች ሴት ዶክተር ነበረችና እሷ ካየችኝ በኋላ የቡድኔ ተጨዋቾች የሆኑት በላይ እና ደሳለኝ ናቸው ስለ ሁኔታው የነገሩኝ። በላይ ስለ ሁኔታው ሲያስረዳኝም ከአፍህ ላይ እንደምራቅ ነገር አይቼ ነው የመጣሁት። በኋላ ላይ ምላስህ ታጥፎ እና መተንፈስ ሲያቅትህ ስናይ እኛ ነን ደርሰንልህ ነፍስ እንድትዘራ ያደረግንህ ሲሉኝ ያኔ ነው ሁሉን ነገር ያወቅኩት ብሎናል”።
የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት ጉዳትን ካስተናገደበት እና የመጀመሪያን እርዳታንም ካገኘበት ከባህርዳር ስታድየም በኋላ በቀጥታ ከከተማዋ 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ጥበበ ጊዮን ሪፈራል ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን ወደዛም ሲያመራ ስለ ነበረው ሂደት እና ስለ ጉዳቱም ይህን ብሏል።
“መጀመሪያ እንደተኛው ወደ ሆስፒታሉ ነበር ያመራሁት። ከዛም ኤክስሬይ ተነሳው። የኤክስሬይ ውጤቱም በነጋታው ይታወቅ ነበርና ድንገት መተንፈስ እንኳን ቢያቅትህ በሚል እዛ ማደር እንዳለብኝ ቢነገረኝም እኛ ጋር የክለባችን ዶክተር ስለነበር ሳላድር ቀረውና በነጋታው ውጤቱ ሲታይ ቅጥቅጥ ነው ተባለና አሁን ያን አውቄ ነው ጭንቅላቴ አካባቢ ቁስለት ስለነበር በክለባችን ዶክተር አማካኝነት ከሰኞ ዕለት አንስቶ በቀን ሁለት ጊዜ በክንዴ ላይ መርፌ እየተወጋውና መድሀኒት በመውሰድ ከፍተኛ መሻሻልን እያሳየው ያለሁት” ብሏል።
ታሪክ አሁን ላይ ስለሚገኝበት ሁኔታ እና ወደ ሜዳም መቼ እንደሚመለስም ተጠይቆ ሲገልፅ
“ከዚህ ቀደም ስለ እንደዚህ አይነት ጉዳቶች አውቃለው። ለደደቢት ስጫወትም በብርሃኑ ቦጋለ /ፋዲጋ/ ላይም ይሄ አጋጥሞት ነበር። አሁን እኔ በተወሰነ መልኩ የስነ-ልቦናው ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር የዛን ዕለት ሂደቱን ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ አድርጌ ነው እየቆጠርኩት ያለሁት። በጥሩ ጤንነት ላይም ነው የምገኘው። ኳስን በሚያጫውተኝ ሁኔታም ላይ ነኝ” ብሏል።
ከደረሰበት ጉዳት በኋላ ስለ እነማን ምን ማለትን እንደሚፈልግም ታሪክን ጠይቀነው
“በቅድሚያ ሁለቱ የቡድኔ ተጨዋቾች በላይ እና ደሳለኝ በፍጥነት ስለደረሱልኝ እና ወደ ህይወትም ከፈጣሪ እገዛ ጋር ስለመለሱኝ ለእነሱ ላቅ ያለ ምስጋና አለኝ። ሙሉ የኢትዮጵያ ህዝብም ጉዳቱን ካስተናገድኩበት ጊዜ ጀምሮ በፀሎት እና በመጠየቅ እኔ ወደ መልካም ጤንነት እንድመለስ ከጎኔ ሆኗልና ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው የቡድኔ አባላቶች እንደዚሁም ከእኔ ጋር በጭንቅላቱ የተጋጨው የቡድናችን ተጨዋች አሚንም በእኔ ጉዳት ደንግጦ እና እኔንም የተጋጨሁበት እያመመኝ ነውም ብሎ ጠይቆኛልና እሱም ሊመሰገን ይገባዋል”።
የአዳማው ታሪክ ከባለቤቱ ሰናይት ታግሎ ጋር በመሰረተው ትዳር በግንቦት ወር ላይ 6ኛ ዓመትን የምትይዝ የአብሳላት እና በመጋቢት ወር ላይ 1ኛ ዓመትን የምትይዝ የማኬልዳ አባት ሲሆን ጉዳቱን ካስተናገደ በኋላ ባለቤቱ ጋር ስለነበረው ስሜትም ይናገራል።
“ባለቤቴ ሰናይት እንደ አጋጣሚ ያን ዕለት ኳሱን እያየች ነበር። ልክ ጉዳቱ እንደደረሰብኝም በጣም ተደናግጣ ስልክ ያልደወለችበት ቦታ የለም። ለእናቴ እና ለወንድሜ ሁሉ ደውላለች። በመጨረሻም በዛን ዕለት ጨዋታ ደስታ ደሙ በቀይ ካርድ ወጥቶ ስለነበር ነው ከእሱ ጋር አውርታ ነው ስላለሁበት ሁኔታ በማወቅ ልትረጋጋና ለሌሎቹም ልታሳውቅ የቻለችውና ውዷ ባለቤቴ እሷም ሌላዋ ተመስጋኝ ናት”።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ለደደቢት ስትጫወት እስከ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋችነት ድረስ በመመረጥ ስምህ በጉልህ ይጠራ ነበር ያስም አሁን ላይ እንደበፊቱ ካለመጠራት ጋር በተያያዘ የምትለው ይኖር ይሆን
“አዎን! በእግር ኳስ መውጣት እና መውረድ ያለና የሚኖር ነው። እኔንም ይሄ የመጫወት እድሎችን ከማግኘት እና አለማግኘት ጋር በተያያዘ አጋጥሞኛል። በዚህ ብዙም አልቆጭም። በፊት ከፍተኛ ስም ያለኝ ተጨዋች ነበርኩ። አሁንም ያን የመጫወት ዕድልን በተደጋጋሚ ግዜ ሳገኝ ሁሉ ነገር ይስተካከላል። እስከዛም ከፈጣሪ እርዳታም ጋር ጠንክሮ መስራትም ግዴታዬም ነው”።