ባሳለፍነው አርብ በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ በምድብ ለ ምድቡን በበላይነት በማጠናቀቅ በ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ መሳተፋቸውን ካረጋገጡት ሶስት ክለቦች አንዱ የሆነው እና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ መደጉን ያረጋገጠው የለገጣፎ ለገዳዲ እግር ኳስ ክለብ ወደ ከተማው ሲገባ ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎለታል ።
ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ በመጨረሻው ቀን ባቱ ላይ በተካሄደ ጨዋታ የሰንደፋ በኬን ክለብ 4 ለ 0 በማሸነፍ እና በውድድሩ ላይ በአጠቃላይ 36 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከተከታዩ ቤንቺ ማጂ በሶሰት ነጥብ በመብለጥ ነበር ወደ ሊጉ ማደጉን ያረጋገጠው ።
ቡድኑ ወደ ከተማው ሲገባ በክፍት መኪና በመዘዋወር ከህዝቡ ጋር ደስታውን የገለፀ ሲሆን ከጎዳና ላይ ዝግጅቱ በኋላ በዳሌ ደምበል ሆቴል የአቀባበል ስነ ስርዓት ተካሂዶለታል ። የሆቴሉ ዝግጅት አባ ገዳዎች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የከተማው ከንቲባ እና የክለቡ ደጋፊዎች በተገኙበት የተደረገ ነበር ።
በስነ ስርዓቱ ላይም ለተጫዋቾቹ ለአሰልጣኞች እና ለሌሎች የቡድኑ አባለት የዕውቅና እና ለኮከብ ተጫዋቾች ሽልማት ከተሰጠ በኋላ ድል ያደረጉበትን ዋንጫ ለከተማው ከንቲባ አቶ በሪሶ ተመስገን አስረክበው የአቀባበል ስነ ስርዓቱ ተጠናቋል ።
- ማሰታውቂያ -
ፕሪሚየር ሊጉ ገና የ14 ሳምንታት ቀሪ ጨዋታዎች ያሉት ሲሆን የቀጣይ አመት የውድድር ዘመን እስኪደርስ ተጫዋቾች በምን አይነት መልኩ ቀጣዩን ጊዜ ያሳልፋሉ የሚለው ለብዙዎች ጥያቄ ሲሆን ምናልባትም ከሰሞኑ በተደጋጋሚ እየሰማን እንዳለነው ወደ ሌሎች የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በውሰት በማምራት ሊያሳልፉ እንደሚችሉ ይጠበቃል ። የውድድሩ ገና በዚህ ጊዜ መጠናቀቅ እና ያስነሳቸው ጥያቄዎች በቀጣይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድሩን ፕሮግራሞችን በቀጣይ ሲያወጣ ሊያስተካክለው የሚገባ ተግባር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ።
ሌላው ጉዳይ አንዳንድ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚያድጉ ክለቦች ሲያደርጉ የተመለከትነው እና ክለቦች አድገው ደካማ እንቅስቃሴ ለማሳየታቸው እንደምክንያት የሚነሳው ጉዳይ ያሉትን ተጫዋቾች በሌሎች ተጫዋቾች በመተካት በሊጉ ላይ መሳተፋቸው እንደሆነ ይታወቃል ። በቀጣይስ ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ክለቡን ባሳደጉት ወጣት ተጫዋቾች የ2015 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ያከናውን ይሆን ወይንስ በሌሎች ተጫዋቾች ተክቶ ይሳተፍ ይሆን ? በቀጣይ አመት የምንመለከተው ይሆናል ።