በአስራ አራተኛዉ ሳምንት ሶስተኛ ዕለት የመጀመሪያ ጨዋታ የአሰልጣኝ ዉበቱ አባተ ቡድን ፋሲል ከነማ እና አዳማ ከተማ መርሐግብራቸዉን አንድ አቻ በሆነ ዉጤት አገባደዋል ።
በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ከነበረባቸው የጎል ድርቅ በመላቀቅ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ከሀዋሳ ከተማ እና ባህርዳር ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ አምስት ጎሎችን ማስቆጠር የቻሉት አዳማዎች በዛሬዉ ወሳኝ መርሐግብር ገና በጨዋታው መባቻ በመስመር አጥቂዉ ዮሴፍ ታረቀኝ አማካኝነት ድንቅ የግብሙከራ ካደረጉ በኋላ በስምንተኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ከአማካዩ መስዑድ መሐመድ የተሻገረለትን ኳስ ለቦና አሊ አቀብሎት የመስመር አጥቂዉ አስደናቂ ግብ አስቆጥሮ አዳማዎች መምራት ጀምረዋል።
በተቃራኒው በመጨረሻዎቹ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻል ጋር ባደረጓቸዉ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዉ ወደ ዛሬዉ ጨዋታ የቀረቡት አፄዎቹ ፤በጨዋታዉ የመጀመሪያ የግብ ሙከራቸዉን በአስራ አምስተኛዉ ደቂቃ ላይ አማካዩ ይሁን እንደሻዉ ከሳጥን ዉጭ ወደ ግብ በላከዉ ኳስ ማድረግ የቻሉት ፋሲሎች በድጋሚ ከማዕዘን ምት በአማኑኤል አማካኝነት ድንቅ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም በግብ ዘቡ ሰኢድ አማካኝነት ከሽፍባቸዋል።
- ማሰታውቂያ -
አጠቃላይ በጨዋታዉ እንቅስቃሴ ረገድ የአፄዎቹን የበላይነት ባስመለከተዉ የመጀመሪያዉ አጋማሽ መጠናቀቂያ በጭማሪ ደቂቃ ወቅት አንጋፋዉ አጥቂ ጌታነህ ከበደ ከግራ መስመር በኩል ከናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ አቻ መሆን ችሏል።
ከዕረፍት መልስ የመጀመሪያውን አጋማሽ ያህል የጨዋታ እንቅስቃሴ መመልከት ያልተቻለ ሲሆን በተለይ በሙከራ ረገድ በ55ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጣሪዉ ቦና አሊ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ድንቅ ሙከራ ማድረግ ሲችል በተቃራኒው ቀስ በቀስ ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ የጨዋታዉን ብልጫ ዳግም መዉሰድ የቻሉት አፄዎቹ ደግሞ ምንም እንኳን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ይቻሉ እንጅ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታዉ አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ወራጅ ቀጠናዉ ላይ የሚገኘዉ ሻሸመኔ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።
ከአምስት ተከታታይ ሽንፈት አልባ ጉዞ በኋላ በ13ተኛዉ ሳምንት በፋሲል ከነማ ሽንፈት ገጥሟቸዉ የነበሩት ሻሸመኔዎች በዛሬዉ ተጠባቂ መርሐግብር ላይ በብዛት በራሳቸዉ ሜዳ ጊዜን በማሳለፍ እና ለተጋጣሚ ቡድን ክፍተቶችን ባለመስጠት ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ የተስተዋለ ሲሆን ፤ በተጨማሪም ከተከላካይ ክፍሉ ረጃጅም ኳሶችን ለአጥቂ ተጫዋቾች በመጣል የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል።
በተቃራኒው በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ምንም እንኳን አስደንጋጭ የሚባል ሙከራን ማድረግ አይቻሉ እንጅ በተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን በዳግማዊ አባይ ፣ ኤፍሬም አሻሞ እና ሄኖክ አንጃዉ አማካኝነት መፍጠር ችለዋል ።
እምብዛም አስደንጋጭ የሚባል ተጠቃሽ ሙከራ ያልተመለከትንበት የመጀመሪያዉ አጋማሽ ያለ ግብ በአቻ ዉጤት ሲጠናቀቅ ፤ ከዕረፍት መልስ ግን በ50ኛዉ ደቂቃ ላይ አብዱለጢፍ ከቀኝ መስመር ያሻገረዉን ኳስ ሱራፌል ጌታቸው ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በመጠኑም ቢሆን ወደ ጨዋታዉ ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ሻሸመኔዎች ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ በ54ተኛዉ ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል ። በዚህም የድሬዳዋዉ ግብ ጠባቂ አጥቂዉ ጌትነት ተስፋየ ላይ የሰራዉን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት አለን ካይዋ ከመረብ አሳርፎ ጨዋታዉ በአቻ ዉጤት ተጠናቋል።