በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአስራ ዘጠነኛ ሳምንት የመጨረሻ ዕለት የቀን 10:00 ሰዓት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ጨዋታቸውን በአቻ ዉጤት አጠናቀዋል።
በተመጣጣኝ የሜዳ ላይ የጨዋታ ፉክክር በጀመረዉ የቀኑ መርሐግብር ሁለቱም ክለቦች የጨዋታዉን የበላይነት ለመውሰድ ሲጥሩ የተስተዋለ ቢሆንም ድሬዳዋ ከተማዎች ግን በሙከራ እና ጫና በመፍጠሩ ረገድ በንፅፅር የተሻሉ ሆነዉ ተስተዉለዋል። በዚህ ሂደት በጀመረዉ ጨዋታም ድሬዳዋዎች በ15ተኛዉ ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም ከመስመር በኩል መሐመድ አብዱልለጢፍ ያሻማዉን ኳስ ተከላካዩ ፈቱዱን መቆጣጠር ባለመቻሉ ምክንያት ኳሷን ያገኛት ቻርልስ ሙሰጌ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ገና በጊዜ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ያስቆጠሩት ድሬዎች በድጋሚ መሪነታቸዉን ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ ተቃርበዉ ነበር ፤ በዚህም ግብ ጠባቂዉ ፍሬዉ ጌታሁን መሳሳቱን ተከትሎ የተገኘችዉን ኳስ አሜ መሐመድ ከኤፍሬም አሻሞ ጋር ተቀባብሎ ወደ ግብ ቢሞክርም ኳሷ ወጥታለች።
- ማሰታውቂያ -
እምብዛም ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ባላስመለከተን እና በአብዛኛዉ በሜዳዉ የመሐል ክፍል ላይ ትኩረት ያደረገን የተጨዋታ መንገድ ያስመለክቱን በነበሩት ሁለቱ ክለቦች ድሬዎች መሪ ከሆኑ ከደቂቃዎች በኋላ ዳግም በዘርዓይ ገ/ስላሴ አማካኝነት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበዉ ሳይሳካላቸዉ ቀርቷል።
በአንፃሩ ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ በተጋጣሚያቸው ቡድን ብልጫ የተወሰደባቸዉ ባንኮች በይበልጥ ረዣዥም ኳሶችን ወደ ፊት በመላክ የአቻነት ግብ ፍለጋ ላይ የነበሩ ሲሆን በመጨረሻም አሰልቺ ከነበረዉ ጥረታቸዉ በኋላ በ80ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም ኪቲካ ጀማ ያሻገራት ኳስ በግብ ዘቡ ስትመለስ ያገኛት ሲሞን ፒተር ኳሷን ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን አቻ አድርጎ ጨዋታው አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።
* በአስራ ዘጠነኛዉ ሳምንት የመጨረሻ መርሐግብር ሲዳማ ቡና ከተከታታይ አራት ጨዋታዎች በኋላ ወሳኝ ድል አስመዝግበዋል።
በዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ ፊሽካ ምሽት አንድ ሰዓት ሲል በጀመረዉ ጨዋታ ገና በመባቻዉ በ4ተኛዉ ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች መሪ መሆን ችለዋል። በዚህም ከግራ መስመር በኩል ማይክል ኪፖሩል ያሻማውን ኳስ የሻሸመኔዉ ተከላካይ ገዛኸኝ ደሳለኝ በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሮ ሲዳማዎች ጨዋታውን መምራት ችለዋል።
ገና በጊዜ ግብ የተቆጠረባቸዉ ሻሸመኔ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ በ17ተኛዉ ደቂቃ ላይም አብዱልከሪም ቃሲም ከሳጥኑ ውጭ ድንቅ ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም መክብብ ደገፉ ኳሷን ተቆጣጥሯል። በዚሁ ቅፅበት በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ይዘዉ ሳጥን ዉስጥ የደረሱት ሲዳማዎች በማይክል ኪፕሩል አማካኝነት ድንቅ ሙከራ ቢያደርጉም የግቡ ቋሚ ሙከራቸዉን አክሽፎባቸዋል።
ምንም እንኳን በሙከራ ረገድ ደካማ በነበረዉ ጨዋታ በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሲዳማዎች በመጀመሪያዉ አጋማሽ በአማካዩ በዛብህ መለዮ እና ይስሀቅ አማካኝነት ድንቅ ሙከራዎችን ማድረግ ሲችሉ በአጋማሹ መገባደጃ ወቅትም ሲዳማ ቡና ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበዉ ነበር ፤ በዚህም ሀብታሙ ንጉሴ ይስሀቅ ላይ የሰራዉን ጥፋት ተከትሎ የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ደስታ ደሙ መትቶ የነበረ ቢሆንም ኳሷን የግቡ ቋሚ መልሷታል።
በሙከራ ረገድ ደካማ የሚባል እንቅስቃሴ ካስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ በይበልጥ በሁለተኛዉ አጋማሽ በአጠቃላይ የጨዋታ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞ እና ለዕይታ ደብዝዞ ይህ ነዉ የሚባል ተጠቃሽ ሙከራ ሁለቱም ክለቦች ሳያደርጉ ጨዋታዉ እንድ ለዜሮ በሆነ ዉጤት በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል።