በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23ተኛ ሳምንት መርሐግብር መቻል በምንይሉ ወንድሙ ሀትሪክ ወልቂጤ ከተማን ሶስት ለአንድ አሸንፏል ።
ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲል በጀመረዉ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች በተመጣጠነ የጨዋታ እንቅስቃሴያቸዉን ከጀመሩ በኋላ በመጀመሪያዉ ተጠቃሽ ሙከራ መቻሎች በ13ተኛዉ ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል ። በዚህም በዚሁ ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የተገኘዉን ኳስ ከንዓን ማርክነህ በፍጥነት ለምንይሉ ወንድሙ አቀብሎት ተጫዋቹ ደግሞ በቀጥታ ወደ ግብነት በመቀየር መቻልን መሪ ማድረግ ችሏል።
እንደከዚህ ከደቀሙ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸዉ እየተዳከመ የቀጠሉት ወልቂጤ ከተማዎች ይባስኑ በ24ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግዷል ። በዚህም ከግራ መስመር በኩል ዳዊት ማሞ ያቀበለዉን ኳስ አምበሉ ምንይሉ ወንድሙ በድጋሚ ወደ ግብነት በመቀየር የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ለዜሮ ከፍ ማድረግ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ገና በጊዜ ሁለት ግብ የተቆጠረባቸዉ ወሎቂጤዎች በ33ተኛዉ ደቂቃ ላይ ወደ ጨዋታዉ የሚመልሳቸዉን ለማግኘት ተቃርበዉ ነበር ፤ በዚህም ተመስገን በጅሮንድ ኳስ በዕጅ መነካቱን ተከትሎ የተገኘዉን የቅጣት ምት ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ግን ለጥቂት ወጥታለች። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ ላይም በ43ተኛዉ ደቂቃ ምንይሉ ወንድሙ ሶስተኛ ግብ ለራሱ እና ለክለቡ አስቆጥሮ አጋማሹ በመቻል ሶስት ለዜሮ መሪነት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መንቀሳቀስ የጀመሩት ወልቂጤዎች ምንም እንኳን በአንድ ሁለት አጋጣሚ ወደ ሶስተኛዉ የሚዳ ክፍል ቢገቡም ነገር ግን ዕድሎችን ከመጠቀም እንፃር ደካማ ሆነዉ ተስተዉሏል። በ68ተኛዉ ደቂቃ ላይም መድን ተክሉ በክትፎዎቹ በኩል ድንቅ ሙከራ ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ ኳሷን አዉጥቷት በ76ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግን ጋዲሳ መብራቴ ከቅጣት ምት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው ሶስት ለአንድ በሆነ ዉጤት በመቻል አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሀዋሳ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለት ለአንድ በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል ።
በፈረሰኞቹ የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አመሻሽ 12:00 ሰዓት ሲል በጀመረዉ ጨዋታ በ10ኛዉ ደቂቃ ላይ አጥቂዉ አማኑኤል ኤረቦ ወደ ግራ ካደላ ቦታ ከሳጥን ዉጭ ድንቅ ሙከራ ማድረግ ቢችልም ግብ ጠባቂዉ ቻርልስ ግን በደረቱ መልሶበታል። በዚህ ሂደት በጀመረዉ ጨዋታም በ14ተኛዉ ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ ግብ አግኝተዋል ከኋላ መስመር ዳዊት ተፈራ የሰነጠቀለትን ኳስ አማኑኤል አረቦ በፍጥነት ተቆጣጥሮ ቺፕ አድርጎ በማስቆጠር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር ከአምስት ያህል ደቂቃዎች በኋላ ሀዋሳ ከተማ ድንቅ ሙከራ አድርገዋል ፤ በዚህም እንየዉ ካሳሁን ከቅጣት ምት ያሻማዉን ኳስ በረከት በግንባሩ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ግብ ጠባቂዉ ባህሩ ነጋሽ ኳሷን ተቆጣጥሯል። በ33ተኛዉ ደቂቃ ላይም አሊ ሱለይማን ከሳጥን ዉጭ ድንቅ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ በ43ተኛዉ ደቂቃ ላይ አማኑኤል አረቦ አስቆጪ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂዉ ቻርልስ እንደምንም አዉጥቶበት ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛዉ አጋማሽ ተጋግለዉ የተመለሱት ሀይቆቹ በአጥቂዎቹ አሊ ሱለይማን እና እስራኤል እሸቱ አማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላ በ68ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ችለዋል ። በዚህም ከተከላካይ ክፍል የተሻገረለትን ኳስ አሊ ሱለይማን በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን አቻ አድርጓል። ከመጀመሪያዉ አጋማሽ በተቃራኒዉ ተቀዛቅዘዉ የተመለሱት ፈረሰኞቹ በ84ተኛዉ ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። በዚህም ሄኖክ አዱኛ በመከላከል እንቅስቃሴ ለመመለስ የገጨዉን ኳስ አጠገቡ የነበረዉ አማኑኤል ጎበና አግኝቶት ወደ ግብነት በመየቀር ክለቡን ከመመራት ወደ መሪነት አሸጋግሮ ፤ ጨዋታዉም በሀዋሳ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።