የዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ንግድ ባንኮች አርባምንጭ ከተማን በጥሩ ብቃት በማሸነፍ ጀምረዋል። አዞዎቹ ከመድን አቻ ከተለያየው ቀዋሚ 11 ሳሙኤል አስፈሪን፣ መሪሁን መስቀለ እና አሸናፊ ተገኝ ወጥተው ስቴፈን አኖርኬ፣ ቻርልስ ሪባኑ እና በፍቅሩ ግዛው ገብተዋል።
ጨዋታውን በፈጣን አጫጭር ቅብብሎች የጀመሩት ንግድ ባንኮች የአርባምንጭን ተከላካይ ክፍል ለመክፈት 2 ደቂቃዎች በቂ ነበሩ። ግራ መስመር ላይ ባሲሩ ኡመር ከአዲስ ግደይ የተቀበለውን ኳስ መሬት ለመሬት ወደ ሳጥኑ ልኮት ኪቲካ ጅማ በቀላሉ ሊየስቆጥረው ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኃላም ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ሻምፒዮኖቹ: በአርባምንጭ ተከላካዮች ስህተት የተገኘውን ኳስ ኪቲካ ጅማ በሚገባ ተጠቅሞ: በ7 ደቂቃ ውስጥ ሁለተኛ ግባቸውን ማግኘት ችለዋል።
ከሁለቱ ግቦች በኃላ ትንሽ መረጋጋት የጀመሩት አርባምንጮች በ16ኛው ደቂቃ ከራሳቸው ሜዳ በረጅሙ የተላከውን ኳስ አህመድ ሁሴን ላይ ደርሶ ኳሱን ወደ ውስጥ ይዘ በመግባት የላከው ኳስ አህብዋ ብሪየን አስቆጥሮ አዞዎቹን ወደ ጨዋታው የመለሰ መስሎ ነበር። የመሀል ሜዳውን ብልጫ ወስደው በአጫጭር ቅብብሎች ጨዋታውን የተቆጣሩት ንግድ ባንኮች የመጀመርያውን 45 በመሪነት ጨርሰዋል።
- ማሰታውቂያ -
ሁለተኛው አጋማሽም እንደ መጀመርያው በንግድ ባንኮች ማራኪ ቅብብሎች የታጀበ ነበር፣ አዚ ላይ የሁለቱ መስመር ተከላካዮች አብዱልከሪም መሐመድ እና ኤፍሬም ታምራት ወደ መሀል እየገቡ ከቢንያም ካሳሁን እና ባሲሩ ኡመር ጋር የነበራቸው መናበብ ለብልጫ መስዳቸው ወሳኝ ሆኖ ታይቷል። ከኃላ መስርተው መጫወታቸውን የቀጠሉት ሻምፒዮኖቹ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ኪቲካ ጅማ፣ አዲስ ግደይ እና ፋዓድ ፈረጃ አካቶ የጀመረው ቅብብል በፋዓድ ፈረጃ ግሩም አጨራረስ ለንግድ ባንክ ሥስተኛ ግብ አስገኝቷል። ሥስተኛዋ ግብ አጋማሽ የአርባምንጭ ወደ ጨዋታው የመመለስ ሞራልን ከጅምሩ የቀጨች ሆናለች።
የበጸሎት ልዑልሰገድ ቡድን የኳስ ቁጥጥር ብልጫን በመውሰድ አርባምንጮች የግብ እድሎችን እንዳይፈጥሩ በሚገባ በመቆጣጠር የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታቸውን በሙሉ ሥስት ነጥብ ጀምረዋል።