የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች በኋላ በዛሬው ዕለት በአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲመለስ ፤ ሀዋሳ ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን 2 – 1 የረታ ሲሆን መቀሌ 70 እንደርታ ከመቻል ነጥብ ተጋርተዋል።
ከቀን 10:00 ጀምሮ በተደረገው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ የዘርዓይ ሙሉው ሀዋሳ ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን 2 – 1 አሸንፏል።
በጨዋታው ሀዋሳ ከተማ ገና በ8ኛው ደቂቃ ላይ በአቤኔዘር ዮሐንስ በተቆጠረ ግብ መሪ ሆኗል። አቤኔዘር ዮሐንስ ከሳጥኑ የቅርብ ርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት በአስገራሚ ሁኔታ በቀጥታ ግብ አድርጎታል።
ሀይቆቹ መሪነታቸውን ከፍ ለማድረግ አራት ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጁባቸው። ኤርትራዊው አጥቂ ዓሊ ሱሌማን በ12ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ከተማን መሪነት ወደ 2 – 0 አሳድጓል።
- ማሰታውቂያ -
አጥቂው ከታፈሰ ሰለሞን በግሩም እይታ የደረሰውን ኳስ በተፈጥሯዊ ጠንካራ እግሩ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ 51ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋአብ ግዛው ሀድያ ሆሳዕና ወደ ጨዋታው መመለስ የምትችል ግብ አስቆጥሯል። ከቅጣት ምት ወደ ግብ የተሻገረውን ኳስ የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች በአግባቡ ለማራቅ በተቸገሩበት ወቅት ፀጋአብ ኳስና መረብን አገናኝቷል።
በመጨረሻም ሀዋሳ ከተማ 2 – 1 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ድል ሲያሰመዘግብ ሀድያ ሆሳዕና ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገደበት ሆኗል።
በአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው አርብ ጥቅምት 15 ሀዋሳ ከተማ አዳማ ከተማን ሲገጥም ፤ ሀድያ ሆሳዕና በበኩሉ ከሁለት ቀናት በኀላ ጥቅምት 17 ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ይጫወታል።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ከምሽት 1:00 ጀምሮ ጨዋታቸውን ያደረጉት መቀሌ 70 እንደርታና መቻል 1 – 1 በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል።
በጨዋታው 37ኛ ደቂቃ ላይ የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሀኑ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገ ግብ አስመዝግቧል።
ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ በሌላኛው የቡድን አጋሩ ተገጭቶ ያገኘው ያሬድ ብርሀኑ በግንባር በመግጨት ግቡን አስቆጥሯል።
በሁለተኛው አጋማሽ 51ኛ ደቂቃ ላይ መቻል አቻ የሆነበት ግብ ተመዝግቧል። የመቀሌ 70 እንደርታው ዘረሰናይ ብርሀኑ ከመቻል ተጫዋች በረጅሙ ወደ መቀሌ 70 እንደርታ የግብ ክልል የተሻገረውን ኳስ ለማውጣት ሲጥር ተጨርፎበት በራሱ መረብ ላይ አሳርፎታል።
በመጨረሻም ጨዋታው በ1 – 1 ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።
በአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሀሙስ ጥቅምት 14 መቀሌ 70 እንደርታ ከድሬዳዋ ከተማ ሲጫወት ፤ በተከታዩ ቀን ጥቅምት 15 መቻል ከወልዋሎ አዲግራት ጋር ይገናኛል።
የሊጉ መርሐግብር በነገው ዕለትም ሲቀጥል ቀን 10:00 ጀምሮ ስሁል ሽረ ከድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም ከምሽት 1:00 ጀምሮ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።