በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች መካከል ተጠባቂ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ የ3 – 2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ምሽት 1:00 ጀምሮ በተደረገው እና በከፍተኛ ትኩረት የተጠበቀው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በርካታ ክስተቶችን አስተናግዶ እና 5 ግቦች ተቆጥርውበት ተጠናቋል።
በጨዋታው አስቀድመው በግብ መሪ የሆኑት ፈረሰኞቹ ሲሆኑ ተገኑ ተሾመ በ25ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተነሳውን ኳስ ተጠቅሞ ቡድኑን መሪ አድርጓል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ተቃርቦ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ሳለ ግን የአምና ሻምፒዮኖቹ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ አስቆጥረዋል። ግቡን ያስቆጠረው የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች አዲስ ግደይ ነው።
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው አጋማሽ የአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ቡድን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ መሪነት የመጣበትን ግብ በ54ኛ ደቂቃ ላይ አግኝቷል።
ንግድ ባንኮች የቅዱስ ጊዮርጊስ የጨዋታ እንቅስቃሴ በማቋረጥ ያገኙትን ኳስ በፈጣን ቅብብል ያገኘው ኪቲካ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።
የንግድ ባንክ መሪነት ግን ከሶስት ደቂቃዎች በላይ መዝለቅ የቻለ አልነበረም። በ57ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ኤርቦ ከፍፁም ጥላሁን የደረሰውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን በማለፍ ጭምር ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ስምንት ያህል ደቂቃዎች በቀሩበት ጊዜ ፈረሰኞቹ ዳግም መሪ እንዲሁም አሸናፊ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል። በፈጣን መልሶ ማጥቃት ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ተነስተው በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል የገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በፍፁም ጥላሁን አማካኝነት የጨዋታውን 3ኛ ግብ ከመረብ አሳርፈዋል።
በርካታ ጉሽሚያዎች ከታዩበት የመጨረሻ ደቂቃዎች በኋላም ቅዱስ ጊዮርጊስ በ3 – 2 ውጤት ሶስት ነጥቡን ወስዷል።
በቀጣይ ሳምንት መርሐግብር በመጪው ጥቅምት 14 ሀሙስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፋሲል ከነማ እንዲሁም ጥቅምት 16 ቅዳሜ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ መድኅን ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ከቀን 10:00 ጀምሮ የተደረገው የስሁል ሽረ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ባለመሸናነፍ ተጠናቋል።
በ1 – 1 ውጤት ፍፃሜውን ባገኘው ጨዋታ ቻርለስ ሙሴጌ በ21ኛው ደቂቃ ላይ የይታገሱ እንዳለውን ቡድን መሪ አድርጓል።
ቻርለስ ሙሴጌ ግቡንም ተከትሎ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛቶች አራት ማድረስ ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሸ 54ኛ ደቂቃ ላይ ደግሞ የስሁል ሽረው ብርሀኑ አዳሙ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ከጨዋታው አንድ ነጥብ እንዲያሳካ አስችሏል።
በአምስተኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ጥቅምት 14 ሀሙስ ድሬዳዋ ከተማ ከመቀሌ 70 እንደርታ እንዲሁም ጥቅምት 17 እሁድ ስሁል ሽረ ከወላይታ ድቻ ያገናኛሉ።
የሊጉ መርሐግብር በነገው ዕለትም ሲቀጥል 10:00 ላይ ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ምሽት 1:00 ላይ አዳማ ከተማ ከፋሲል ከነማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።