የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ሲደረጉ ወላይታ ድቻ ኢትዮጵያ ቡናን ከመመራት ተነስቶ አሸንፏል።
ከቀን 10:00 ጀምሮ በተደረገው ጨዋታ በግብ ቀዳሚ የነበሩት ቡናማዎቹ ነበሩ። ጨዋታው በተጀመረ 4ኛው ደቂቃ ላይ አንተነህ ተፈራ በኮንኮኒ ሀፍዛ የተሞከረው ኳስ ሲመለስ አግኝቶ ግቡን አስቆጥሯል።
አስቀድመው መሪ የሆኑት ቡናማዎቹ የመጀመሪያውን አጋማሽ በመሪነት ቢያጠናቅቁም ሁለተኛው አጋማሽ ግን ከነርሱ በተቃራኒ ነበር።
በ48ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳሬዛ ከቡድን አጋሩ የተቀበለውን ኳስ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ይዞ በመግባት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።
- ማሰታውቂያ -
ይህ ግብ ከተቆጠረ 18 ደቂቃዎች በኋላ ያሬድ ዳርዛ የጦና ንቦቹን ከመመራት ወደ መሪነት የቀየረ ግብ አስቆጥሯል።
በመጨረሻም በወላይታ ድቻ የ2 – 1 አሸናፊነት ጨዋታው ተጠናቋል።
በአምስተኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ቅዳሜ ጥቅምት 16 ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና ሲጫወቱ በተከታዩ ቀን ጥቅምት 17 ወላይታ ድቻ ከስሁል ሽረ ጨዋታቸው ያደርጋሉ።
ምሽት 1:00 ጀምሮ የተደረገው የአዳማ ከተማ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ በ1 – 1 ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።
በጨዋታው 63ኛ ደቂቃ ላይ ቢንያም አይተን አዳማ ከተማን ቀዳሚ ያደረገ ግብ ከመረብ አሳርፏል። ቢንያም ረጅም ሜትሮችን እየገፋ በመሄድ ግቡን አስቆጥሯል።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሶስት ያህል ደቂቃዎች በቀሩበት ጊዜ በረከት ግዛው ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።
በመጨረሻም ውጤቱ በ1 – 1 ተጠናቋል። በአምስተኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሀሙስ ጥቅምት 14 ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ጥቅምት 15 አዳማ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ ይገናኛሉ።
የሊጉ መርሐግብሮች በነገው ዕለትም ሲቀጥሉ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከባህርዳር ከተማ እንዲሁም ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ መድኅን ይጫወታሉ።