የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት መደረግ ጀምረዋል።
ከቀን 10:00 ጀምሮ በተደረገው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኅን ከግብ ጋር ታርቆ ወልዋሎ አዲግራትን ረቷል።
በጨዋታው አብዲሳ ጀማል ለአሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌው ቡድን በ81ኛው ደቂቃ ላይ የማሸነፊያውን ግብ ያስቆጠረው ተጫዋች ነው።
ይህ ግብ ለኢትዮጵያ መድኅን የውድድር ዓመቱ ቀዳሚ እንዲሁም በአጠቃላይ በሊጉ ከ531 ደቂቃዎች በኋላ የተገኘ ግብ ነው።
- ማሰታውቂያ -
ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ መድኅን ነጥቡን 6 በማድረስ ወደ 13ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።
በጨዋታው የተረታው የአሸናፊ በቀለው ወልዋሎ አዲግራት በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው ሁሉም(ስድስት) ጨዋታዎች ሁሉንም ተሸንፏል።
በዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ቀናት ላይ በርካታ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ቡድኑ ያለ ምንም ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን ግርጌ ይዞ ይገኛል።
በሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድኅን ከመቀሌ 70 እንደርታ እንዲሁም ወልዋሎ አዲግራት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይጫወታሉ።
ምሽት 1:00 ጀምሮ በተደረገው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ከ37 የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከታታይ ጨዋታዎችን አሸንፏል።
በተመሳሳይ በ1 – 0 ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ አበበ ጥላሁን አዞዎቹን ሶስት ነጥብ ያስገኘውን ብቸኛ ግብ በአምስተኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።
በሊጉ የመጀመሪያ ሶስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው አርባምንጭ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት ባህርዳር ከተማን በመርታት የዓመቱን ቀዳሚ ድል ማስመዝገቡ ይታወሳል።
ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ዳግም በ2009 ከተመለሰ በኋላ ጠንካራ ተፎካካሪ የሆነው ፋሲል ከነማ የዓመቱ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ከማስተናገዱ ባለፈ ከመጀመሪያ ስድስት ጨዋታዎች በታሪኩ ዝቅተኛውን ነጥብ አስመዝግቧል።
ቡድኑ በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከረታ በኋላ ያደረጋቸውን ያለፉትን አራት ተከታታይ ጨዋታዎች በሙሉ በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ ይታወቃል።
በቀጣይ ሳምንት ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ፋሲል ከነማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ይጫወታሉ።