የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ ስታድየም ተደርገዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ የ2016 የውድድር ዘመንን በሁለተኝነት እና በሻምፕየንነት ያጠናቀቁት መቻል እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተገናኝተው መቻል 1 – 0 አሸንፏል።
በጨዋታው 79ኛ ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ከአማኑኤል ዮሐንስ የደረሰውን ኳስ ግብ ጠባቂውን በማለፍ ጭምር አስቆጥሮታል።
ውጤቱንም ተከትሎ መቻል በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለመሸነፍ ክብረወሰኑን ሰባተኛ ጨዋታ ላይ አድርሷል።
- ማሰታውቂያ -
በሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች መቻል ከአዳማ ከተማ እንዲሁም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወልዋሎ አዲግራት ይጫወታሉ።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች በኋላ ወደ ድል የተመለሰበትን ውጤት በመቀሌ 70 እንደርታ ላይ አስመዝግቧል።
በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና 2 – 0 ያሸነፈ ሲሆን አንተነህ ተፈራ የሁለቱም ግቦች አስቆጣሪ ነው። በ57ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ቀዳሚውን ግብ ሲያስቆጥር በ60ኛ ደቂቃ ላይ ደግሞ ሁለተኛውን በጨዋታ እንቅስቃሴ ከመረብ አሳርፏል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ መቀሌ 70 እንደርታን የረታበት ሲሆን ከወራጅ ቀጠናው በመውጣትም 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በቀጣይ ሳምንት በሚደረጉ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና ከስሁል ሽረ እንዲሁም መቀሌ 70 እንደርታ ከኢትዮጵያ መድኅን ይጫወታሉ።