በደረጃ ሰንጠረዡ 14ኛ እና 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩትን ሁለት ክለቦች ያገናኘዉ የሀያ ዘጠነኛው ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ መርሐግብር አዳማ እና ድሬዳዋ ጨዋታቸውን በአቻ ዉጤት አጠናቀዋል።
አስቀድመዉ በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንታት ብርቱ ተፎካካሪ ይመስሉ የነበሩት አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ የሊጉ የጨዋታ ሳሞንታት እየገፉ በመጡ ቁጥር ግን በተቃራኒው እየተንሸራተቱ ለለመዉረድ የሚደረገዉን ትግል ከተቀላቀሉ ሰንበትበት ብለዋል።
አሁን ደግሞ በወራጅ ቀጠናዉ ላይ የተገኙት ሁለቱ ክለቦች ምናልባት ሶስተኛ ወራጅ ቡድን ሁነዉ ወደ ታችኛዉ ሊግ ላለመዉረድ አንድ እና አንድ ማሸንፍን ዋና ኢላማቸዉ አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
በተመሳሳይ መንገድ እጅግ በርከት ያሉ የማጥቃት ባህሪ ያላቸዉን ተጫዋቾች ይዘዉ የገቡት ሁለቱም ክለቦች የጨዋታውን የበላይነት ለመዉሰድ በየፊናቸዉ ሲታትሩ ተስተውለዋል።
- ማሰታውቂያ -
ከጨዋታዉ ጅማሮ አንስቶ ለአይን ሳቢ በነበረዉ ጨዋታ ላይም ገና በ11ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ተመልክተንበታል። በዚሁ ደቂቃ ላይም የአዳማ ከተማዉ ተከላካይ ሚሊዮን ሰለሞን ሱራፌል ጌታቸው ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘዉን ቅጣት ምት አብዱለጢፍ መሐመድ ቀጥታ ወደ ግብ ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በተለይ ግቧን ባስተናገዱት አዳማ ከተማዎች በኩል የመደናገጥ ስሜትን የተመለከትን ሲሆን ለዚህም ማሳያ በብዛት አብዲሳ ጀማል ፣ አቡበከር ወንድሙ እና ዳዋ ሁቴሳ ያገኟቸዉ የነበሩ ዕድሎችን ወደ በቀላል ስህተት ወደ ግብነት መቀየር አለመቻላቸው ነበር ፤ በአንፃሩ በብሩትካናማዎቹ በኩል ደግሞ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በይበልጥ ጥንቃቄ ላይ ያመዘነ የጨዋታ መንገድን ሲከተሉ ተስተውሏል።
የጨዋታዉ ሂደት በዚህ ሁነት ቀጥሎ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ የሶስት ደቂቃዎች እድሜ ሲቀረዉ ግን የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ዮሴፍ ዮሐንስ ከርቀት ሞክሮ ግብ ጠባቂዉ ደረጀ የመለሰበት ኳስ ለአዳማ ከተማዎች በአጋማሹ ከተደረጉ ሙከራዎቾ መካከልም ተጠቃሽ ነበረች።
በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሶስት የሚደርሱ ተጫዋቾችን ቀይረዉ ወደ ሜዳ በማስገባት ወደ ጨዋታዉ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት አዳማዎች ዉጥናቸዉ ፍሬ አፍርቶ በ52ኛዉ ደቂቃ ላይ የአቻነቷን ግብ ማግኘት ችለዋል። በዚሁ ደቂቃ ላይም ወጣቱ የመስመር ተጫዋች ቢኒያም አይተነዉ ከቀኝ መስመር በኩል ተጫዋቾችን ቀንሶ ያሻገረዉን ኳስ የድሬዳዋ ተከላካዮች በአግባቡ ማፅዳት ባለመቻላቸው ምክንያት በቅርበት የነበረዉ አብዲሳ ጀማል ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል።
ተመጣጣኝ የጨዋታ ፍክክርን እያስመለከተን በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም አልፎ አልፎ አስደንጋጭ የሚባሉ ሙከራዎችን በሁለቱ ክለብች በኩልም ለመመልከት ችለናል። ከነዚህ መካከልም በ76ኛዉ ደቂቃ ላይ መነሻዉን ከማዕዘን ያደረገዉን ኳስ የመስመር አጥቂዉ ወሰኑ አሊ አክርሮ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም በግብ ዘቡ ደረጀ ድንቅ ብቃት ከሽፏል።
በተመሳሳይ ደግሞ በ81ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ብርቱካናማዎቹ መሪ መሆን የሚችሉበትን እድል ማግኘት ችለዉ ነበር ፤ በዚሁ ደቂቃ ላይም የፊት አጥቂዉ ማማዱ ሲዲቤ ከርቀት አክርሮ ወደ ግብ የላከዉን ኳስ ግብ ጠባቂዉ ሲመልሰዉ በአቅራቢያው የነበረዉ ሱራፌል ጌታቸዉ በድጋሚ በሞክርም አሁንም የግብ ዘቡ ሳኩቡ ካማራ አዉጥቶታል።
የጨዋታዉ ሰዓት እየገፋ በሔደ ቁጥር እየተቀዛቀዘ የሄደዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።
ዉጤቱን ተከትሎም አዳማ ከተማ በ32 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በ30 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።