በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ በቀዳሚነት ጨዋታቸውን ያደረጉት አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና 0 ለ 0 በሆነ ውጤት ተለያይተዋል ።
አዳማ ከተማ በ10ኛ ሳምንት ጨዋታ ሰበታ ከተማን ከመመራት ተነስተው ባሸነፉት ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ የሁለት ተጫዋች ቅያሪ በማድረግ በአሜ መሀመድ እና ዮሴፍ ዮሐንስ ምትክ አብዲሳ ጀማልን እና ታደለ መንገሻን ሲያስገቡ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በሀዋሳ ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ሮቤል ተክለሚካኤልን በዊልያም ሰለሞን ቀይረው አስገብተዋል ።
ቀዝቃዛ የሜዳ ላይ አንቅስቃሴ የነበረው ጨዋታ በብዛት በመሀል የሜዳው ክፍል ላይ ቆይታ የበዛበት ነበር ። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ከኋላ መስርተው ወደ ፊት ለማለፍ የሚያደርጉት ጥረት በመሀል ላይ የቁጥር ብልጫ በነበራቸው የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች አማካኝነት ሲበላሽባቸው ነበር ። በአዳማ ከተማ በኩል የሚነጠቁ ኳሶችን በፍጥነት ወደ ፊት በመላክ በተለይም በቀኝ መስመር በኩል ወደ ግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ቢያደርጉም የቡናን የተከላካይ መስመር አልፈው ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረዋል ።
- ማሰታውቂያ -
ሁለቱም ክለቦች ከነበራቸው ደካማ የፊት መስመር እንቅስቃሴ የተነሳ የግብ ሙከራዎች ማድረግ ተስኗቸው ነበር የመጀመሪያውን አጋማሽ ያጠናቀቁት ።
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተወሰነ መልኩ ጨዋታ የተነቃቃ ይመስል ነበር ። ኢትዮጵያ ቡናዎች ቀደም ብሎ ከነበረው በተሻለ ወደ አዳማ ከተማ የግብ ክልል የመድረስ ዕድሎችን ቢያገኙም በአጨራረስ ላይ የነበራቸው ክፍተት እነዚህን ዕድሎች ወደ ግብ እንዳይቀይሩ አግዷቸዋል ።
57ኛ ደቂቃ ላይ አቤል እንዳለ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ከእንዳለ ደባልቄ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት በግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ተጨርፎ የማዕዘን ምት ሆኗል ። እንዲሁም በ66ኛ ደቂቃ ላይ እንዳለ ደባልቄ በረጅም የደረሰውን ኳስ አረጋግቶ ለታፈሰ ሰለሞን ያቀበለው ቢሆንም የታፈሰ ኳስ ኢላማውን የጠበቀ አልነበረም ።
በአዳማ ከተማ በኩል በራሳቸው የሜዳ ክፍል በቁጥር በዝተው የሚነጠቁ እና ከኋላ የሚጀመሩ ኳሶችን በረጃጅም ከፊት መስመር ላይ ተነጥሎ ለነበረው ዳዋ ሆጤሳ በማድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ውጤታማ መሆን አልቻለም ።
83ኛ ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማዎች ከኋላ መስርተው ለመውጣት በሚሞክሩበት ጊዜ ሚሊዮን ሰለሞን ለማቀበል የሞከረው ኳስ በእንዳለ ደባልቄ ተነጥቆ ለታፈሰ ሰለሞን ቢደርሰውም በታፈሰ የተመታው ኳስ በቶማስ ስምረቱ ሊመለስ ችሏል ።
ከተጨማሪ ሶስት ደቂቃዎች በኋላ ጨዋታው ፍፃሜውን ሲያገኝ ያለ ግብ የተለያዩት ሁለቱ ክለቦች አንድ አንድ ነጥብ ተጋርተዋል ።
ውጤቱን ተከትሎም አዳማ ከተማ ነጥቡን 16 በማድረስ 5ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በ15 ነጥብ ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል ።
በ12ኛ ሳምንት ጨዋታ አዳማ ከተማ ፋሲል ከተማን ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ አዲስ አበባ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል ።