በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ በቀዳሚነት በተደረገው ጨዋታ ፋሲል ከነማ በሙጂብ ቃሲም ሁለት ግቦች አዳማ ከተማን 2 ለ 0 ረቷል ።
አዳማ ከተማዎች በ26ኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ እዮብ ማቲዮስን እና ዮሴፍ ዮሀንስን በቶማስ ስምረቱ እና ፀጋአብ ዮሴፍን ምትክ ሲያሰልፉ በፋሲል ከነማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ሰበታ ከተማን 1 ለ 0 ባሸኘፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙት የመጀመሪያ አሰላለፍ ሶስት ቅያሪዎችን በማድረግ አስቻለው ታመነ ፤ ሱራፌል ዳኝቸውን እና በረከት ደስታን በከድር ኩሊባሊ ፤ በዛብህ መለዮ እና ኦኪኪ አፎላቢ ቦታ አሰልፈው ወደ ሜዳ ገብተዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ፋሲል ከነማዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን በተለይም ከመስመር በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ። በአንፃሩ በአዳማ ከተማ በኩል አፄዎቹ የግብ ዕድል መፍጠሪያ ቦታዎችን እንዳያገኙ በማድረግ እና በተወሰኑ አጋጣሚዎችም ከፊት መስመር ለተሰለፉት ሶስቱ ተጫዋቾች ኳሶችን በማድረስ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ነበር ።
በአፄዎቹ በኩል እንደፈጠሩት ጫና ጠንከር ያሉ ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ያልቻሉ ሲሆን በበረከት ደስታ እና በናትናኤል ገብረጊዮርጊስ አማካኝነት ከመስመር በሚሻገሩ የአየር ላይ ኳሶች ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች ወደ ውጪ ሊወጡ ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በአዳማ ከተማ በኩል በ22ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ ገረመው በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ላይ ለአቡበከር ወንድሙ ከፍ አድርጎ ያቀበለው ሲሆን አቡበከር ለመጠቀም ሲሞክር በአምሳሉ ጥላሁን በተፈጠረበት ጫና ኳሱን በአግባቡ ወደ ግብ እንዳይሞክረው ሆኗል ።
ፋሲል ከነማዎች በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም የነበራቸው የማጥቃቱ ሶስተኛው ዞን ላይ ሲገቡ ኳሱን በሚገባ ከመጠቀም ይልቅ በአዳማ ከተማ ተከላካዮች ሲበላሹ ቆይተዋል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሶስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት አፄዎቹ የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር ። አምሳሉ ጥላሁን ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያሬድ ባየህ አግኝቶ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሳኩባ ካማራ ሲመልሰው ያንኑ ኳስ በረከት ደስታ ከግራ መስመር ላይ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ሌላኛው የመሀል ተከላካይ አስቻለው ታመነ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ።
የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ ከመጀመሪያው በተመሳሳይ እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን አፄዎቹ አጋማሹ በተጀመረ 10ኛ ደቂቃ ላይ ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ማግኘት ችለዋል ።
ሙጂብ ቃሲም ሱራፌል ዳኛቸው በግሩም ሁኔታ ያደረሰውን ኳስ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተከትሎ በአንድ ንክኪ ወደ ግብነት ቀይሮታል ። ይህም ሙጂብ ቃሲም ከአልጄሪያው ክለብ ጄኤስ ካቢሌ ያልተሳካ ቆይታ በኋላ ወደ ፋሲል ተመልሶ ያስቆጠረው የመጀመሪያ ግብ ሆኗል ።
ግብ ያስተናገዱት አዳማ ከተማዎች በተወሰነ የመነቃቃት ሁኔታን ቢያሳዩም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ እስከ 71ኛው ደቂቃ መጠበቅ የግድ ብሏቸው ነበር ። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ አዲስ ተስፋዬ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አቡበከር ወንድሙ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በሳማኪ ሚኬል ተይዟል ። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም በአማኑኤል ጎበና እና በዮሴፍ ዮሀንስ ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች ኢላመቸውን መጠበቅ የቻሉ አልነበሩም ።
አፄዎቹ በቀጣይቹ ደቂቃዎች ላዬ በፈጣን የማጥቃት ሂደት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን አድርገዋል ።
በ77ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ጥላሁን ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ለቡድኑም ሆነ ለራሱ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል ።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አዳማ ከተማዎች ቅያሪዎችን በማድረግ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለማሻሻል ቢጥሩም ኳስ እና መረብ ሳያገናኙ ጨዋታው ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ ነጥቡን 55 በማድረስ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 3 ዝቅ ሲያደረግ አዳማ ከተማ በበኩሉ በ30 ነጥብ በነበረበት 11ኛ ደረጃ ለመቆየት ተገዷል ።
በ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 17 ( አርብ ) 7:00 ላይ ፋሲል ከነማ ከሀዋሳ ከተማ ሲጫወት 10:00 ላይ ደግሞ አዳማ ከተማ መከላከያን የሚገጥም ይሆናል ።