በ17ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ አዳማ ከተማን ከጅማ አባጅፋር አገናኝቶ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል ።
አዳማ ከተማዎች በ16ኛው ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን ሚሊዮን ሰለሞን እና እዮብ ማቲያስን በደስታ ዮሀንስ እና ኡበበከር ወንድሙ ምተክ ሲያሳልፉ በሳምንቱ በሀዋሳ ከተማ የተረቱት ጅማ አባጅፋሮች በጨዋታው ከነበረው ምርጥ 11 በተመሳሳይ ሁለት ለውጦችን በማድረግ ተስፋዬ መላኩ እና ሙሴ ከበላን በቦና አሊ እና አስጨናቂ ፀጋዬ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል ።በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ አዳማ ከተማዎች በፈጣን አጀማመር የጅማ አባጅፋርን የኋላ መስመር መፈተን የቻሉ ሲሆን በጅማ አባጅፋር በኩልም ቀስ በቀስ ወደ ፊት ማለፍ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው ነበር ።
የአዳማ ከተማዎች አጨዋወት ሁለቱን የፊት መስመር ተጫዋቾች ዳዋ ሆቴሳ እና አሜ መሀመድን ኢላማ ያደረጉ ተደጋጋሚ ኳሶችን መጠቀም ቢችሉም ከጨዋታ ውጪ የሆኑ ኳሶች ይበዙበት ነበር ። በጨዋታው የመጀመሪያውን ግልፅ የግብ ዕድል የፈጠሩት ጅማ አባጅፋሮች ሲሆኑ በ14ኛ ደቂቃ ላይ መሱድ መሀመድ ለመሀመድኑር ናስር ከሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ሆኖ የቀነሰለትን ኳስ አጥቂው ተንሸራቶ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ጀማል ጣሰው መልሶበታል ።
በ15ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው አማካይ ዮሴፍ ዮሀንስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አላዛር አድኖበታል ።
- ማሰታውቂያ -
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሌላ የግብ ሙከራ ያደረጉት ጅማ አባጅፋሮች ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል ። የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ተጫዋቾች ያገኙትትን የቅጣት ምት ዲዊት እስጢፋኖስ ያሻማዋሎ ተብሎ ሳጠበቅ አድናን ረሻጅ በቀጥታ ወደ ግብ መቶ ከመረብ ላይ አሳርፎታል ።አዳማ ከተማዎች ከግቡ በኋላ ተጭነው መጫወታቸውው የቀጠሉ ሲሆን በ38ኛው ደቂቃ ላይም ለተቆጠረባቸው ግብ መልስ መስጠት ችለዋል ። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ዮሀንስ ከግራ መስመር ወደ ግብ ክልል ኳሱን ሲያሻግር የጅማ አባጅፋር ተከላካዮች ባለመናበብ ከግባቸው ማራቅ የተሳነባቸውን ኳስ አሜ መሀመድ አግኝቶ በማስቆጠር የጨዋታውን ውጤት ወደ 1 – 1 ቀይሮታል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በአንድ እኩል ውጤቶ ተጠናቋል ።
ሁለተኛው አጋማሽ አብዛኛው የጨዋታ የበላይነት በአዳማ ከተማ ስር የነበረበት ሽኩቻዎች የበዙበት በሜዳው ካለው በርካታ የአዳማ ከተማ ደጋፊ ጋር ተደምሮ ደመቅ ያለ አጋማሽ ነበር ።
በአዳማ ከተማዎች በኩል በተመሳሳይ ለሁለቱ የፊት አጥቂዎች ኳስን አመቻችቶ ለማድረስ ጥረቶች የቀጠሉ ሲሆኖ በዚህም 47ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ተከላካዮችን አምልጦ የደረሰውን ኳስ አክርሮ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ኳሱ አላዛርን ማለፍ የቻለ አልነበረም ።
በ72ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ግብ ጠባቂው መልሶበታል ።የማሸነፊያውን ግብ ፍለጋ አጠናክረው የቀጠሉት የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ልጆች በተለይም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ከፍተኛ ጫና በጅማ አባጅፋር የግብ ክልል ላይ መፍጠር ችለው ነበር ። በዚህም 89ኛው ደቂቃ ላይ ጅብሪል አህመድ ከአማኑኤል ጎበና የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ቢልከውም ለጥቂት ወደ ውጪ ወቷል ።
በመጨረሻም ሁለቱም ቡድኖች ከጨዋታው አንድ አንድ ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል ።
ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ በ23 ነጥብ 7ኛ ላይ ሲቀመጥ ከትናንት በስቲያ ሰበታ ከተማ ማሸነፉን ተከትሎ ዘደ 16ኛ ወርዶ የነበረው ጅማ አባጅፋር በ12 ነጥብ ወደ 15ኛ ደረጃ ተመልሷል ።
በ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሀሙስ 9 ሰዓት ላይ አዳማ ከተማ ወላይታ ድቻን ሲገጥም ጅማ አባጅፋር ደግሞ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በተመሳሳይ ሰዓት ፋሲል ከተማን ይገጥማል ።