በ21ኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ በቀዳሚነት የተደረገው የአዳማ ከተማ እና የሲዳማ ቡና ጨዋታ በአንድ እኩል ውጤት ተጠናቋል ።
አዳማ ከተማዎች በ20ኛው ሳምንት ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በዳዋ ሆቴሳ ምትክ አቡበከር ወንድሙን ሲያሰልፉ በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ በሳምንቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሲረቱ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ ደግፌ አለሙ እና ይገዙ ቦጋለን በአማኑኤል እንዳለ እና ብርሃኑ አሻሞ ተከተው በማሰለፍ ጨዋታውን ጀምረዋል ።
ተመጣጣኝ ሊባል የሚችል እቅስቃሴን ባስመለከተን ጨዋታ በሁለቱም በኩል ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ከፍተኛ ትንቅንቅ ተደርጎበታል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በአዳማ ከተማም ሆን በሲዳማ ቡና በኩል ወጣ ገባ ያሉ እንቅስቃሴዎችን የተመለከትን ሲሆን አዳማ ከተማዎች ወደ ፊት መስመር የሚያደርሷቸው ኳሶች በቀላሉ አልፈው ወደ ሳጥን ለመግባት የቻሉ አልነበሩም ። በሲዳማ ቡና በኩል በተለይም በፈጣን ሸግግሮች ወደ አዳማ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የመጀመሪያውን ሙከራ በማድረጉ ረገድ ሲዳማ ቡና ቀዳሚ የነበሩ ሲሆን ፍሬው ሰለሞን ከቅጣት ያሻገረውን ኳስ ይገዙ ቦጋለ ማግኘት ችሎ የነበረ ቢሆነንም የይገዙ ኳስ ኢላማውን የጠበቀ አልነበረም ።
በ15ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ያኩቡ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ልኮት የነበረ ቢሆንም ጀማል ጣሰው ተቆጣጥሮታል ።
አዳማ ከተማዎቾ ወደ ሲዳማ ቡና የግብ ክልል ለመድረስ የሚያደርጓቸው ጥረቶች በሶስተኛው የማጥቃት ዞን ላይ ሲደርሱ ይበላሽ ነበር ።
በ37ኛው ደቂቃ ላይ ሳልሀዲን ሰይድ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ኳስ በጀማል ጣሰው ተመልሷል ።
በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት አዳማ ከተማዎች በ44ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል ። በቀኝ መስመር በኩል ራሱን ነፃ አድርጎ የነበረው አቡበከር ወንድሙ ያደረሰውን ከተቃራኒ አቅጣጫ ከደስታ ዮሀንስ የደረሰውን ኳስ ወደ ግቅ አክርሮ በመምታት በተክለማርያም ሻንቆ መረብ ላይ አሳርፏል ።ነገር ግን አዳማ ከተማዎች ደስታቸውን አጣጥመው ሳይጨርሱ ግብ አስተናግደዋል ። ከርቀት የቀኝ አቅጣጫ ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት ፍሬው ሰለሞን ሲያሻግረው ሳልሀዲን ሰይድ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ሲዳማ ቡናን አቻ አድርጓል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም በኩል በጨዋታው አሸናፊ ለመሆን ጥረቶች የተደረጉ ሲሆን በቱይም አዳማ ከተማዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ችለዋል ።
በሲዳማ ቡና በኩል አልፎ አልፎ ወደ አዳማ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት በአዳማ ተከላካዮች በተደጋጋሚ ሊከሽፍ ችሏል ።
በ57ኛው ደቂቃ ላይ ኡበበከር ወንድሙ ከቅጣት ምች በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ዮሴፍ ዮሀንስ ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
አዳማ ከተማዎች ከነዚህ ሙከራዎች በኋላም በ70ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ የግብ ዕድል ማግኘት ችለው የነበረ ሲሆን አሜ መሀመድ ከሲዳማ ቡና ተከላካዮች የነጠቀውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ በጊት ጋትኩት ሲመለስ በቅርብ የነበረው አብዲሳ ጀማል ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ኳሹ ኢላማውን የጠበቀ አልነበረም ።
በሁለቱም በኩል የተጫዋቾች ቅያሪን ማድረግ ቢችሉም ሌላ ግብ ሳይስተናገድ ጨዋታው 1 – 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን 34 በማድረስ በግብ ከፍያ በልጦ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አዳማ ከተማ ደግሞ ነጥቡን 26 በማድረስ ወደ 8ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል ።22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ( ባህርዳር ) በመጪው ግንቦት 1 ( ሰኞ ) አዳማ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲገጥም ሲዳማ ቡና ደግሞ ፋሲል ከነማን ከሁለት ቀናት በኋላ ግንቦት 3 ( ረቡዕ ) የሚገጥም ይሆናል ።