በአዳማ ከተማ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል የተደረገው የሰባተኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ 0 ለ 0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ።
አዳማ ከተማ በስድስተኛው ሳምንት ከሲዳማ ቡና አቻ በተለያየበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ አንድ ቅያሪ ብቻ በማድረግ ደስታ ዮሀንስን ጨዋታውን እንዲጀምር ሲያደርጉ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ሀዋሳ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ የነበረውን ቋሚ 11 ምንም ሳይቀይሩ ይዘው ገብተዋል ።
በጨዋታው አዳማ ከተማዎች የፈጠሯቸውን በርካታ ዕድሎች በአጨራረስ ድክመት ምክንያት ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል ። በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል ደግሞ የነበረው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በእጅጉ የወረደ ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ የተደረገው በ12ኛው ደቂቃ ላይ በአዳማ ከተማ በኩል ሲሆን አሜ መሀመድ ከምኞት ደበበ የነጠቀውን ኳስ መሬት ለመሬት ወደ ግብ ሞክሮት በግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ተይዞበታል ።
በመጀመሪያዎቸለ ደቂቃዎች ፈረሰኞቹ በተሻለ ወደ አዳማ ከተማ የሜዳ ክፍል አልፈው በመግባት ጫና ለመፍጠር ጥረቶችን ቢያደርጉም ቀስ በቀስ አዳማ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ወደ ፊት ለመሄድ ሞክረዋል ።
ቀደም ብሎ ስህተት ሰርቶ የነበረው የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ምኞት ደበበ በድጋሚ 28ኛ ደቂቃ ላይ ኳስ ለግብ ጠባቂው ለማቀበል ሲሞክር በመሳሳቱ ኳሱን ያገኘው አብዲሳ ጀማል ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብ ሳይሆን ቀርቷል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም ወደ ፊት በመሄድ የበላይ የነበሩት አዳማ ከተማዎች ቢሆኑም ግብን ከመረብ ሳያገናኙ እንዲሁም በተለይ በመስመር በፈጣን እንቅስቃሴ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩት ፈረሰኞቹም ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳሱን በተሻለ በመቆጣጠር እና ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ግቦችን ለማግኘት የጣሩ ሲሆን አዳማ ከተማዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት በመሄድ የቅዱስ ጊዮርጊስን የተከላካይ መስመር በተደጋጋሚ የፈተኑበት ነበር ።
በአጋማሹ የተደረገው የመጀመሪያ ሙከራ 52ኛ ደቂቃ ላይ በፈረሰኞቹ በኩል ሲሆን ያብስራ ተስፋዬ ከሀይደር ሸረፋ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን በቀኝ በኩል ሆኖ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው መልሶታል ።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም አሜ መሀመድ በፈጣን እንቅሰቃሴ ወደ ግብ ክልል የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብ ሞክሮት በቻርለስ ሉክዋጎ በቀላሉ ተይዞበታል ። ፈረሰኞቹ በ73ኛ ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተነሳን ኳስ ሊወጣ ሲል ቡልቻ እና ኦጎሮ ተቀባበለው ለሄኖክ አዱኛ የደረሰውን ኳስ ሄኖክ በሳጤን ውስጥ ሆኖ ቢመታውም በግብ ጠባቂው ተመልሶበታል ።
አዳማ ከተማዎች በተደጋጋሚ አሁንም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ሙከራዎቻቸው በሙሉ ከግቡ አናት በላይ ወደ ውጪ የሚወጡ ነበሩ ። በተለይም 85ኛ ደቂቃ ላይ አብዲሳ ጀማል ከጨረቃው አካባቢ ጠንከር አድርጎ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወቶበታል ። በስተመጨረሻም ጨዋታውም ምንም ግብ ሳያስተናግድ ሊጠናቀቅ የግድ ሆነ ።
ውጤቱን ተከትሎም አዳማ ከተማ በ8 ነጥብ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ በ11 ነጥብ ባለበት 5ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል ።