የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት መካሄድ ሲጀምሩ እየመራ ነጥብ መጋራት ልማዱ ያደረገ የሚመስለው አዲስ አበባ ከተማ 1 – 0 ሲመራ ቆይቶ 84ኛ ደቂቃ ላይ በተቆጠረበት ግብ ጨዋታውን በአቻ ውጤት አጠናቋል ።
አዲስ አበባ ከተማዎች በ23ኛው ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን በማድረግ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ፤ ዋለልኝ ገብሬን እና ቢንያም ጌታቸውን በሳሙኤል አስፈሪ ፤ ሙሉቀን አዲሱ እና ፍፁም ጥላሁን ምትክ ሲያሰልፉ በጅማ አባጅፋር በኩል ደግሞ በሳምንቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 አራት ለውጦችን በማድረግ ለይኩኝ ነጋሽ ፤ ኢዳላሚን ናስር ፤ ሙሴ ከበላ እና እዮብ አለማየሁን በአላዛር ማርቆስ ፤ ተስፋዬ መላኩ ፤ አስጨናቂ ፀጋዬ እና ቦና አሊን ተክተው ገብተዋል ።
የመጀመሪያውን አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አዲስ አበባ ከተማዎች ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ በመጀመር ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም እንደወሰዱት ብልጫ አላዛር ማርቆስን ለመፈተን ደቂቃዎችን መጠበቅ የግድ ብሏቸው ነበር ። በጅማ አባጅፋር በኩል የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በተወሰደባቸው ብልጫ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ለመድረስ ተቸግረው ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራም በ22ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ ቻርለስ ሪባኑ ከርቀት በቀጥታ ወደ ግብ የመታውን አስደናቂ ኳስ አላዛር ማርቆስ በድንቅ ብቃት ግብ ከመሆን አድኖታል ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ኤልያስ አህመድ ቻርለስ ሪባኑ ከሱራፌል አስማማው ቀምቶ ያቀበለውን ኳስ በተከላካዮች መሀል ለቢንያም ጌታቸው አቀብሎተሰ ቢንያም ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም አላዛር ከግቡ ወጥቶ ኳሱን መልሶበታል ።
ከውሀ እረፍት መልስ እስከ አጋማሹ መጠናቀቂያ ድረስ ጅማ አባጅፋሮች በተሻለ በመንቀሳቀስ በአዲስ አበባ የሜዳ ክፍል ላይ ደቂቃዎችን ማሳለፍ ቢችሉም 34ኛው ደቂቃ ላይ ዱላ ሙላቱ ከግራው የሳጥኑ አቅጣጫ ከሞከረው እና ኢላማውን መጠበቅ ካልቻለው ኳስ ሌላ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም ነበር ። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ሰባት ደቂቃዎች በኋላ አዲስ አበባ ከተማዎች ኳስ እና መረብን ማገናኘት ችለዋል ። ያብስራ ሙሉጌታ በሪችሞንድ አዶንጎ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ኤልያስ አህመድ 52ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል ።
ከግቡ በኋላ ጅማ አባጅፋሮች አንፃራዊ ብልጫን በመውሰድ መጫወት ችለው የነበረ ሲሆን ቶሎ ቶሎ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ያደረጓቸው ጥረቶችም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ጥሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር አስችሏቸው ነበር ።
በ60ኛው ደቂቃ ላይ መሀመድኑር ናስር ከበላይ ዓባይነህ የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ወደ ግብ ሞክሮ የአዲስ አበባ ከተማው ግብ ጠባቂ ዳንኤል ተሾመ በጥሩ ብቃት ግብ ከመሆን አድኖበታል ።
በመምራት ላይ የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ወደ ኋላ አፈግፍገው በመጫወት በተወሰኑ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢጥሩም ይሀሰ ነው ሊባል የሚችል የግብ ሙከራን ለማድረግ አልቻሉም ነበር ።
በ79ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ ሙሴ ከበላ ከርቀት ወደ ግብ የመታው ኳስ በልመንህ ታደሰ ሲመለስ በቅርብ የነበረው ዳዊት ፍቃዱ በቀላሉ ግብ ለማስቆጠር ያገኘውን ዕድል ሚዛኑን መጠበቅ ባለመቻሉ ወድቆ ኳሱን ሳይጠቀምበት ቀርቷል ። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ መስዑድ መሀመድ ለዳዊት ፍቃዱ በተከላካዮች መሀል የላከለተን ኳስ ሊወጣ ሲል እንደምንም ተቆጣጥሮ ለእዩብ አቀብሎት እዮብ በግቡ ትይዩ ለነበረው መሀመድኑር ናስር በአየር አድርሶት መሀመድኑር በግንባር ገጭቶ አስቆጥሮታል ።
ከግቡ በኋላ አዲስ አበባ ከተማዎች አንሰራርተው ሁለተኛ ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ጨዋታው ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ አዲስ አበባ ነጥቡን 25 ማድረስ ቢችልም በደረጃው ላዬ ለውጥ ሳያደርግ 14ኛ ላይ የተቀመጠ ሲሆን አባጅፋር ደግሞ ነጥቡን 20 አድረሶ በግብ ክፍያ ሰበታ ከተማን በመብለጥ ወደ 15ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል ።
በ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኔ 5 ( ዕሁድ ) 10:00 ላይ አዲስ አበባ ከተማ ወላይታ ድቻን ሲገጥም በተከታዩ ቀን ሰኔ 6 ( ሰኞ ) ረፋድ 4:00 ላይ ደግሞ ጅማ አባጅፋር ከሀድያ ሆሳዕና ይጫወታል ።