በ20ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ ቀዳሚ ጨዋታ ውድድሩ ወደ ከተማው ከመጣ በኋላ ድል ማድረግ ያልቻለውን አዳማ ከተማን ከአዲስ አበባ ከተማ አገናኝቶ ግብ ሳያስተናግድ ተጠናቋል ።
አዲስ አበባ ከተማዎች በ20ኛው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 አንድ ለውጥ ብቻ አድርገው የገቡ ሲሆን በፍፁም ጥላሁን ምትክ መሀመድ አበራን ያሰለፉ ሲሆን በአዳማ ከተማ በኩል በሳምንቱ በሀድያ ሆሳዕና በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን አድርገው ሲገቡ ዮናስ ገረመው ፤ ዮሴፍ ዮሀንስን እና አሜ መሀመድን በጀሚል ያዕቆብ ፤ ዘካርያስ ከበደ እና ፀጋአብ ዮሴፍ እና ምትክ በጨዋታው ላይ ተሰልፈዋል ።ጨዋታው በፈጣን እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን በተለይም አዳማ ከተማዎች አንፃራዊ የበላይነት በመውሰድ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ደግሞ በአብዛኛው ከሪችሞንድ አዶንጎ በስተቀር በራሳቸው የሜዳ ክፍል ሆነው በሚነጠቁ ኳሶች የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረት በማድረግ የጀመሩበት ነበር ።
በጨዋታው የነበረው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ 3ኛው ደቂቃ ላይ የተደረገ ሲሆን ዳዋ ሆቴሳ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የመታውን ምርጥ ኳስ የአዲስ አበባ ከተማው ግብ ጠባቂ ዳንኤል ተሾመ በድንቅ ብቃት ግብ ከመሆን አድኖታል ።
በመዲናዋ ክለብ በኩል ደግሞ በ7ኛው ደቂቃ ላይ ሪችሞንድ አዶንጎ የዮሴፍ ዮሀንስን ስህት ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ ቸኩሎ ሞክሮት ኳሱ ከግቡ አናት በላይ ወጥቶል ።
- ማሰታውቂያ -
አዳማ ከተማ በተለይም በቀኝ መስመር በኩል በማድላት የአዲስ አበባ ከተማን የመከላከል አጥር ለመስበር ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በተወሰኑ አጋጣሚዎች ወደ ሳጥኑ ዘልቀው መግባት ችለው የነበረ ቢሆንም ጠንካራ የግብ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ቆይተዋል ።ከውሀ እረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል 28ኛው ደቂቃ ላይ ሮቤል ግርማ ከቅጣት ምት ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ በጀማል ጣሰው ተይዟል ።
በ35ኛው ደቂቃ ላይም እንዳለ ከበደ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ሪችሞንድ አዶንጎ በቀጥታ ወደ ግቦ መምታት የቻለ ቢሆንም ኳሱ ከጀማል ጣሰው ማለፍ የቻለ አልነበረም ።
በጨዋታ ሂደት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተሳናቸው አዳማ ከተማዎች ከቆሙ ኳሶች ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ያደረጓቸው ጥረቶች ውጤታማ ሳይሆኑ አዲስ አበባ ከተማዎችም ከሮቤል እና አዶንጎ የግብ ሙከራዎች ሌላ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይቸሉ የመጀመሪያውን አጋማሽ ያለ ግብ አጠናቀዋል ።
በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በአዳማ ከተማ በኩል የተመለከትነውን እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ተመልክተነው ነበር ። ፍፁም ጥላሁንን በመሀመድ አበራ በመቀየር ጨዋታውን የጀመሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በአዳማ ከተማ ላይ ጫን ማሳደርም ችለው ነበር ።47ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ፍፁም ጥላሁን በሪችሞንድ አዶንጎ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ጀማል ጣሰው ተቆጣጥሮታል ። በ50ኛው ደቂቃ ላይም የእንዳለ ከበደ እና የሙሉቀን አዲሱ ቅብብል ወደ ሳጥን ገብቶ ነፃ ለነበረው ፍፁም ጥላሁን ተልኮለት የነበረ ቢሆንም ሚሊዮን ሰለሞን ደርሶ አውጥቶታል ።
አዳማ ከተማዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ በመመለስ የአዲስ አበባ ከተማን የኋላ ክፍል አልፈው ለመግባት ያደረጓቸው ሙከራዎች በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ በመሆን ይበላሹ ነበር ።
ቡድኑ በአጋማሹ ያዳረገው ብቸኛ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በ53ኛው ደቂቃ ላይ በደስታ ዮሀንስ አማካኝነት ከቅጣት ምት ያደረጉት ሙከራ ሲሆን በዳንኤል ተሾመ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ።ቀጣዮቹ ደቂቃዎች የአዳማ ከተማ ጫና አይሎ የታየበት ሲሆን በሁለቱ መስመሮች በኩል የማጥቃት እድሎችን ለመፍጠር ያደረጓቸው የነበሩ ሙከራዎች እምብዛም በአዲስ አበባ ከተማ ተከላካዮች ላይ ጫና ያልፈጠሩ ሲሆን በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ግብ ለመድረስ የሚያደርጓቸው ጥረቶችም ከራሳቸው የፊት መስመር ድክመት ጋር ተደሞሮ በተጋጣሚ የኋላ መስመር ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ሲጨናገፉ ቆይተዋል ።
በአዲስ አበባ ከተማ በኩል በተፈጠረባቸው ጫና ወደኋላ አፈግፍገው በመጫወት የሚነጥቋቸውን ኳሶች በረጅም ወደ አዳማ ከተማ የሜዳ ክፍል በማሻገር በእንዳለ ከበደ ፤ በፍጹም ጥላሁን እና ሪችሞንድ አዶንጎ አማካኝነት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገው የነበረ ቢሆንም ኳስ በእነ ቶማስ ስምረቱ የሚመራውን የአዳማ ከተማ የተካላካይ ክፍል ማለፍ አልቻሉም ። በመጨረሻም ጨዋታው ያለ ግብ ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ ነጥቡን 25 በማድረስ ወደ 8ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አዲስ አበባ ከተማ በበኩሉ በ20 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ መቀጥ ችሏል ።
በ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሚያዝያ 24 ( ሰኞ ) ቀን 9 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን ሲገጥም ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ሚያዝያ 22 ( ቅዳሜ ) በተመሳሳይ ሰዓት አዳማ ከተማ ሲዳማ ቡናን ያስተናግዳል ።