የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ እና ባህርዳር ከተማ አገናኝቶ የጣና ሞገዶቹ በፈቱዲን ጀማል ግብ ቀዳሚ መሆን ቢችሉም ኡበበከር ኑሪ ከሰለሞን ወዴሳ የደረሰውን ኳስ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ በተቆጠረ ግብ ጨዋታው አንድ አቻ ተጠናቋል ።
አዲስ አበባ ከተማ በ15ኛው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 አንድ ለውጥ ብቻ ያደረጉ ሲሆን በአሰጋኸኝ ጴጥሮስ ምትክ ቴዎድሮስ ሀሙ ጨዋታውን መጀመር የቻለ ሲሆን በባህርዳር ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ከኢትዮጵያ ቡና አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 አራት ለውጦችን በማድረግ በፋሲል ገብረሚካኤል ፣ መናፍ አወል ፣ ሳለአምላክ ተገኝ እና ኦሴ ማውሊ ምትክ አቡበከር ኑሪ ፣ ሰለሞን ወዴሳ ፣ ሄኖክ ኢሳይያስ እና አብዱልከሪም ኒኪማን አሰልፈዋል ።በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ አዲስ አበባ ከተማዎች የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን ቀስ በቀስ ባህር ዳር ከተማዎች ኳሱኝ ተቆጣጥረው በመጫወት ወደ ፊት ለማለፍ ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።
በሙከራዎች ባልታጀበው የመጀመሪያ አጋማሽ በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ፊት መስመር ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች የሚያገኟቸውን ኳሶች መረጋጋት ተስኗቸው በተደጋጋሚ ሲያበላሿቸው ነበር ።
በባህርዳር ከተማ በኩል ኳሱን ከሜዳቸው ይዘው ለመውጣት በተወሰነ መልኩ የተቸገሩ ሲሆን ፍፁም አለሙ ወደ ኋላ ተመልሶ የሚመሰርታቸው ኳሶች የጣና ሞገዶቹ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የሜዳ ክልል ኳሶችን ይዘው መግባት እንዲችሉ አድርጓቸው ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
የባህርዳር ከተማን ወደ ፊት የማለፍ እንቅስቃሴ በመግታት በኩል የአዲስ አበባ ከተማው የመሀል ክፍል ተጫዋች ቻርለስ ሪባኑ ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነበር ።
በአጋማሹ የታየው አንድ ጥሩ ሙከራ በባህርዳር ከተማ በኩል የተደረገ ሲሆን 35ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም አለሙ ከርቀት ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት በግብ ጠባቂው ዳንኤል እና በግቡ አግዳሚ ሊመለስ ችሏል ።
የሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ የግብ ሙከራዎች የታዩበት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ነበር ። የአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ የተሻሉ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ ወደ ግብ የቀረቡባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር የቻሉ ሲሆኖ በ53ኛው ደቂቃ ላይም ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል ። ፍፁም አለሙ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ የመሀል ተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል በግንባር በመግጨት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
ከግቡ በኋላ አዲስ አበባ ከተማዎች ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ወደ ወደ ፊት በመድረስ የባህር ዳር ከተማን የተከላካይ ክፍል ለመፈተን ችለዋል ።
በ63ኛ ደቂቃ ላይ ሳሙኤል አስፈሪ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ቻርለስ ሪባኑ እና እንዳለ ከበደ ወደ ግብ ሞክሮት የባህርዳር ከተማ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውታል ።
ባህርዳር ከተማዎች ጨዋታውን በማቀዝቀዝ ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማዎች ደግሞ ረጃጅም እና ፈጣን ኳሶችን በመጠቀም ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።
በ70ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ጥላሁን ከርቀት ላይ ወደ ግብ የሞከረው ግሩም ኳስ በኡበበከር ኑሪ ተይዟል ።
በ75ኛው ደቂቃ ላይ ከአዲስ አበባ የግብ ክልል ርቀው የነበሩት ባህርዳር ከተማዎች በጥሩ ቅበብል ወደ ሳጥን ይዘው የገቡትን ኳስ በአሊ ሱሌማን ወደ ግብ ተሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ ወቷል ።
የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ 6 ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት በባህርዳር ከተማው ግብ ጠባቂ የተሰራ ስህትት የጨዋታውን ውጤት ወደ አቻ ቀይሮታል ። ግብ ጠባቂው ኡበበከር ኑሪ ከሰለሞን ወዴሳ የደረሰውን ኳስ በሚገባ መቆጣጠር ሳይችል በእግሩ ስር አልፎ ግቡ ሊቆጠር ችሏል ።ጨዋታውም በመጨረሻ በአንድ አቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ ባህርዳር ከተማ ነጥቡን 21 በማድረስ የ7ኛ ደረጃን መልሶ ያገኘ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ ነጥቡን 15 ማድርስ ቢችልም በደረጃው ላይ ለውጥ ሳያመጣ በ14ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ17ኛ ሳመንት ጨዋታዎች በመጪው ረቡዕ ምሽት 12 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ከተማ አርባምንጭ ከተማን ሲገጥም ባህርዳር ከተማ ደግሞ በማግስቱ በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ከሀድያ ሆሳዕና የሚጫወት ይሆናል ።