በ18ኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ በቀዳሚነት የተደረገው የአዲስ አበባ ከተማ እና የመከላከያ ጨዋታ ሪችሞንድ አዶንጎ አንድ በጨዋታ እና አንድ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠረው ግብ አዲስ አበባ ከተማዎች 2 – 0 መርታት ችለዋል ።
አዲስ አበባ ከተማ በ17ኛው ሳምንት በአርባምንጭ ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 ሶስት ለውጦችን አድርገው የገቡ ሲሆን ሳሙኤል አስፈሪ ፣ ልመንህ ታደሰ እና ዘሪሁን አንሼቦን በቴዎድሮስ ሀሙ ፣ ሮቤል ግርማ እና እዮብ በቀታን ቀይረው ሲያስገቡ በመከላከያ በኩል በሰበታ ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ አንድ ለውጥ በማድረግ እስራኤል እሸቱን በባዳራ ናቢ ሲላ ተክተው ገብተዋል ።የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በአንፃራዊነት መከላከያዎች ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ብልጫውን ወስደው ያሳለፉት ቢሆንም የግብ ዕድል በመፍጠሩ ረገድ ግን ደከም ብለው ነበር ። በአዲስ አበባ ከተማ በኩል በተወሰደባቸው ብልጫ ወደ ኋላ ለማፈግፈግ ቢገደዱም አልፎ አልፎ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ፊት የሚደርሱባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው የነበረ ቢሆንም በተመሳሳይ ልክ እንደ መከላከያ ሁሉ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ነበር ።
የግብ ሙከራዎች ድርቅ በመታው ጨዋታ ላይ የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ የታየው በ17ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ። አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከግራ መስመር አቅጣጫ የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት የነበረ ቢሆንም ክሌመንት ቦዬ አድኖበታል ። አዲስ አበባ ከተማዎች ከመጀመሪያው ሙከራ በኋላ ቀጣዩን ዕድል ለመፍጠር ሁለት ያህል ደቂቃዎችን ብቻ የጠበቁ ሲሆን በዚህ ጊዜ ግን ግብ ማስቆጠር ችለዋል ። ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ በረጅም የመታውን ኳስ የመከላከያ ተጫዋቾች መያዝ ሲሳናቸው ጋናዊው አጥቂ ሪችሞንድ አዶንጎ ኳሱን ተጠቀሞ አዲስ አበባ ከተማን መሪ አድርጓል ።
በቀጣዮቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ላይ መከላከያዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ቢወስዱም የአዲስ አበባ ከተማን የተከላካይ ክፍል አልፈው የግብ ሙከራ ለማድረግ ሳይችሉ ነበር አጋማሹን ያጠናቀቁት ። በአዲስ አበባ ከተማን በኩልም አጋማሹን በጀመሩበት ወደ ኋላ አፈግፍገው በመከላአሉ ላይ በማተኮር እና ኳሱ በእግራቸው ስር በሚገባ ጊዜ በፈጣን ሽግግር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የመድረስ አጨዋወታቸውን በመተግበር የመጀመሪያው አርባአምስት ደቂቃ በመሪነት ማጠናቀቅ ችለዋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያዎች ተጠናክረው ይገባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ልክ እንደ መጀመሪያው ሁሉ በሁለተኛው አጋማሽም የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ሲያዳግታቸው ቆይቷል ።በአጋማሹ የተቀዛቀዘ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን በመመራት ላይ የነበሩት የመዲናዋ ክለብ ተጫዋቾች የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ ለማድረግ እስከ 80ኛው ደቂቃ ለመጠበቅ ተገደው ነበር ። በዚህ ደቂቃ ላይ ፍፁም አለሙ ያሻገረለትን ኳስ ቢንያም ጌታቸው በግንባር ወደ ግብ ቢልከውም ክሌመንት ቦዬ ለጥቂት ወደ ውጪ አውጥቶበታል ።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ መከላከያዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት ለመጠቀም በሚጥሩበት ሰዓት አዲስ አበባ ከተማዎች ኳሱን በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት ማለፍ የቻሉ ሲሆን ቻርለስ ሪባኑ ይዞ የሄደውን ኳስ ወደ ለቢንያም ጌታቸው ሰንጥቆለት ቢንያም በሳጥን ውስጥ ገብቶ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ሲመለስ ኳሱን ለማግኘት የጣረው ቻርለስ ሪባኑ በዳዊት ማሞ ጥፋት ተሰርቶበት የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም የመጀመሪያው ግብ ያስገኘው ሪችሞንድ አዶንጎ መቶ ሁለተኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል ። ጨዋታውም በአዲስ አበባ ከተማ የ2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።
ውጤቱን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ ነጥቡን 18 በማድረስ ወደ 13ኛ ደረጃ ከፍ ሲል መከላከያ በበኩሉ በ19 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አዲስ አበባ ከተማ በመጪው ማክሰኞ አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ ከፋሲል ከተማ ሲጫወት መከላከያ ደግሞ የፊታችን ዕሁድ የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስን ቀን 9 ሰዓት ላይ የሚገጥም ይሆናል ።