በአራተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ሊጉን ከሶስት ሶስት በማሸነፍ በመምራት ላይ የነበረው ፋሲል ከነማ በመነቃቃት ላይ ባለው አዲስ አበባ ከተማ 2 ለ 1 ተሽንፏል ።
በጨዋታው ፋሲል ከተማዎች በሙሉ ደቂቃው ደክመው የተሴተዋሉ ሲሆን በአንፃሩ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ መከላከያን በማሸነፍ የተነቃቁት አዲስ አበባ ከተማዎች የተጋጣሚያቸውን አጨዋወት በመግታተ ያሰቡትን አሳክተው ለመውጣት ችለዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ማድረግ የቻሉት አዲስ አበባ ከተማዎች ሲሆኑ አምስተኛ ደቂቃ ላይ በሪችሞንድ ኦዶንግ አማካኝነት ኢላማውኔ የጠበቀ ሙከራ ቢያደርጉም በሚካኤል ሳማኪ ተመልሷል ። ፋሲል ከተማዎች ኳስን ይዘው ለመጫወት ቢሞክሩም ወደ ፊት በሚሄዱበት ጊዜ የነበራቸው ድክመት የግብ ሙከራዎች በቀላሉ እንዳያደርጉ አድርጓቸዋል ።
- ማሰታውቂያ -
አዲስ አበባ ከተማዎች በፋሲል ከተማ ተከላካዮች ስህተት ግብ የማስቆጠር አጋጣሚን ማግኘት ቢችሉም ኦዶንግ የመታው ኳስ በሳማኪ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ።
በጨዋታው 20ኛ ደቂቃ ላይ አዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር ቻሉ ። ከመስመር የተሻማውን ኳስ ሳማኪ በእግሩ ለመመለስ ሲሞክር ኳሱ አልፎት የአዲስ አበባ ከተማው አጥቂ ኦዶንጎ በግንባር በመግጨት አስቆጠረ ።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አዲስ አበባ ከተማዎች ከመስመር በተነሳ ኳስ ግብ የማስቆጠር ዕድልን በፍፁም አማካኝነት አግኝተው የነበረ ቢሆንም በድጋሚ በሳማኪ ሊመለስ ችሏል ።
አፄዎቹ የነበራቸው እንቅስቃሴ ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ክፍተቶች የነበሩት ሲሆን በዚህ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ተከላካዮች በኩል የነበረው ጥረት የሚደነቅ ነበር ።
በ39ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ አስቆጣሪው ኦዶንግ በሳጥን ውስጥ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ኤልያስ አህመድ የአዲስ አበባን ከተማን ሁለተኛ ግብ አስቆጠረ ።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽም በአዲስ አበባ ከተማ የ2 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ በአፄዎቹ በኩል ግቦችን ለማስቆጠር በተለያዩ አቅጣጫዎች ጥረቶችን ሲያደርጉ የተስተዋለ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ደግሞ በመከላከሉ ጠንክረው በመግባት ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ሞክረዋል ።
በተደጋጋሚ ወደ ግብ ቢሄዱም የአዲስ አበባ ተከላካይ መስመርን ሰብረው ለመግባት የተቸገሩት ፋሲል ከተማዎች 62ኛ ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጠሩ ። ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ፍቃዱ አለሙ በግንባር በመግጨት አስቆጠረ ።
ከግቧ መቆጠር በኋላ አፄዎቹ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም ኳሷን ከመረብ የሚያዋህድ ተጫዋች ማግኘት አልቻሉም ። አዲስ አበባ ከተማዎችም በጠንካራ መከላከል ጨዋታውን በአሸናፊነት አጠናቀው መውጣት ችለዋል ።
በዚህም አዲስ አበባ ከተማ ነጥቡን ወደ ስድስት ሲያሳድግ ፋሲል ከተማ ባለበት ዘጠኝ ነጥብ ለመቆየት ተገደዋል ።