በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የተገናኙት አዲስ አበባ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ተመጣጣኝ እና ጥሩ ፉክክር አድርገው ከእረፍት በፊት ባስቆጠሯቸው አንድ አንድ ግቦች አቻ ሊለያዩ ችለዋል ።
አዲስ አበባ ከተማ በሰባተኛው ሳምንት ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ ሶስት ቅያሪዎችን በማድረግ ዋኬኔ አዱኛ ፤ ዘሪሁን አንሼቦን እና ሙሉቀን አዲሱን ማሰለፍ የቻሉ ሲሆን በሀዋሳ ከተማ በኩል ሰበታ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አስራአንድ አንድ ቅያሪ ብቻ በማድረግ መድኃኔ ብርሀኔ ጨዋታውን እንዲጀምር አድርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው ጅማሮ የሀዋሳ ከተማዎች በፍጥነት ወደ ግብ የመድረስ ፍላጎት የታየበት ነበር ። ቀስ በቀስም ወደ ጨዋታው የተመለሱት አዲስ አበባ ከተማዎች ረጅም ኳሶችን እና በመስመር ላይ ባሉት እንዳለ ከበደ እና ፍፁም ጥላሁን አማካኝነት ለአጥቂው ኦዶንጎ በሚደላኩ ኳሶች ግቦችን ለማግኘት የጣሩበት ነበር ።
የሁለቱም ቡድኖች ፈጣን እንቅስቃሴ በጥሩ ፉክክር ቢቀጥልም የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ ግን እምብዛም ነበር ። ሀዋሳ ከተማ በመስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጉት ሙከራ ኢላማቸውን ሳይጠብቁላቸው ወደ ውጪ ወተዋል ።
35ኛ ደቂቃ ላይ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ከግብ ክልላቸው ኳስ ነጥቀው የወጡት አዲስ አበባ ከተማዎች በተጠቀሰው ደቂቃ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል ። በግራ መስመር ላይ የነበረው እንዳለ ከበደ ከሙሉቀን አዲሱ የደረሰውን ኳስ በሳጥን ውስጥ ሮጦ ለገባው ረችሞንድ ኦዶንጎ በአየር ላይ አድርሶት አጥቂው በግሩም ሁኔታ በግንባር በመግጨት አስቆጥሮታል ።
ግቧ ከተቆጠረች በኋላ ሀዋሳ ከተማዎች ግብ ለማግኘት የወሰደባቸው ሶስት ያህል ደቂቃዎች ብቻ ነበር ። ወንድማገኝ ሀይሉ ፤ ብሩክ በየነ እና መስፍን ታፈሰ ያደረጉት ጥሩ ቅብብል ለኤፍሬም አሻሞ ደርሶት ኤፍሩም በጥሩ አጨራረስ ሀዋሳ ከተማን አቻ ያደረገ ግብ አስቆጠረ ። በቀጣዮቹ የመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ አዲስ አበባ ከተማዎች ከቆሙ ኳሶች የፈጠሯቸው የግብ ዕድሎች በግብ ጠባቂው በመመለስ እና ወደ ውጪ በመውጣት ግብ ሳይሆኑ ቀርተዋል ።
በሁለተኛውም አጋማሽ ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ ፉክክር የታየበት ነበር ምንም እንኳን በቀላሉ የግብ ዕድሎች ያልታየበት ጨዋታ ቢሆንም ።
58ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ከክንፍ ወደ ግብ ሳጥን ውስጥ ያሻገረው ኳስ መስፍን ታፈሰ ለጥቂት አመለጠችው እንጂ ሀዋሳ ከተማ መሪ መሆን የሚችልበት ትልቅ ዕድል ነበር ። እስከ 80ዎቹ መጨረሻዎች ወደ ተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል በመድረስ የግብ ሙከራ ለማድረግ አይናፋር የሆኑት አዲስ አበባ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በተመሳሳይ መንገድ በተባረክ ሄፌሞ ( ሀዋሳ ከተማ ) እና ፍፁም ጥላሁን ( አዲስ አበባ ከተማ ) አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ዕድሎችን ማግኘት ቢችሉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል ።
ውጤቱን ተከትሎም በእኩል 10 ነጥብ ላይ የነበሩት ሁለቱ ክለቦች አንድ አንድ ነጥብ በመጨመር በእኩል 11 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 6ኛ ( ሀዋሳ ከተማ ) እና 7ኛ ( አዲስ አበባ ከተማ ) ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል ።