በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ቀዳሚ ጨዋታ ሲዳማ ቡና አዲስ አበባ ከተማን 2 – 1 መርታት ችሏል ።
ጨዋታው ከጅምሩ ፈጠን ባሉ እንቅስቃሴዎች ታጅቦ በስምንት ደቂቃ ውሰጥ ሁለት ግቦችን አስተናግዷል ።
አዲስ አበባ ከተማዎች በ28ኛው ሳምንት ሰበታ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 አንድ ለውጥ በማድረግ ቢንያም ጌታቸው ሪችሞንድ አዶንጎን ተክቶ ሲገባ በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ በሳምንቱ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን በማድረግ ያኩቡ መሀመድን እና ጊት ጋትኩትን ሰለሞን ሀብቴ እና ተስፋዬ በቀለነሰ ተክተው ገብተዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በ7ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ሙሉአለም መስፍን አስቆጥሮ ሲዳማ ቡና መሪ መሆን ችሎ ነበር ። ነገር ገሰን የሲዳማ ቡና መሪነት ከሴኮንዶች ቆይታ ያለፈ አልነበረም ። ፍፁም ጥላሁን በረጅም ከአሰጋኸኝ ጴጥሮስ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በሲዳማ ቡና መረብ ላይ በማሳረፍ አዲስ አበባ ከተማን አቻ ማዳረግ ችሏል ።
ከግቦቹ መቆጠር ቀደም ብሎ በ4ኛው ደቂቃ ላይ ሮቤል ግርማ ከቅጣት ምት ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ ግብ ተመልሷል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ የጨዋታው ሂደት በብዛት በመሀል የሜዳው ክፍል የነበረ ሲሆን ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ከጨዋታው ነጥብ ማግኘት የግድ የሚላቸው የመዲናዋ ተጫዋቾች በተሻለ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ችለው ነበር ።
በ19ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር አቅጣጫ የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ መክብብ ሰለሞን ተቆጣጥሮታል ።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ ሞክሮ በዳንኤል ተሾመ ከታየዘበት በኋላ ሲዳማ ቡናዎች በአጋማሹ ሌላ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም ነበር ።
በ26ኛው ደቂቃ ላይ ቻርለስ ሪባኑ ከሳጥን ውጪ በጠንካራ ምት ወደ ግብ የላከው ኳስ ለጥቂች ዘደ ውጪ ወጥቷል ።
ከውሀ እረፍት መልስ አዲስ አበባ ከተማዎች እንቅስቃሴያቸውን በማስቀጠል በተለይም በመስመር ባደሉ የማጥቃት ሂደቶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ። በሲዳማ ቡና በኩል ወደ አዲስ አበባ ከተማ የግብ ክልል ለማድረስ የሚጥሯቸው ኳሶች በቀላሉ በተጋጣሚ ተጫዋቾች እግር ስር ይገቡ ነበር ።
በ42ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ጥላሁን ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ በመክብብ ደገፉ ግብ ከመሆን ድኗል ። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ራሱ ፍፁም ከተመሳሳይ ቦታ በተቃራኒው እግሩ ወደ ግብ የላከው ኳስ ዳግም ከመክብብ ማለፍ የቻለ አልነበረም ። የመጀመሪያው አጋማሽም በ1 – 1 ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች በተሻለ እንቅስቃሴ የጀመሩት ሲሆን በተለይም ከቆሙ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶቾን በማድረግ የቀጠሉት ነበር ። በአዲስአበባ ከተማ በኩል የሚገኙ ኳሶችን በፈጣን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ለማድረግ ቢጥሩም ያን ያህል ተፅዕኖ መፍጠር የቻቹ አልነበሩም ።
ከሙከራዎች ርቆ የቆየው ጨዋታ በ70ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግዷል ። ዳዊች ተፈራ ከሜዳ ክፍሉ ወደ አዱስ አበባ የግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ በሳልሀዲን ሰይድ በኩል አልፎ ሀብታሙ ገዛኸኝ የግብ ጠቢቂውን መውጣት ተመልክቶ ወደ ከፈሸ አድርጎ ወደ ግብ የላከው ኳስ የሲዳማ ቡና ሁለተኛ ግብ ሆኖ ተመዝግቧል ።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ አዲስ አበባ ከተማ ተጭኖ በመጫወት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢጥሩም ፍፁም ጥላሁን በ79ኛው እና 80ኛው ደቂቃ ላይ ካደረጋቸው ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በ45 ነጥብ 3ኛ ደረጃውን ሲያስጠብቅ አዲስ አበባ ከተማ በበኩሉ በ33 ነጥብ በነበረበት 12ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ( 30ኛ ) ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 23 ( ሀሙስ ) ሲዳማ ቡና ሀድያ ሆሳዕናን ሲገጥም በማግስቱ ረፋድ 4:00 ላይ አዲስ አበባ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚገጥም ይሆናል ። ( መርሀግብሮቹ ከ29ኛው ሳምንት ውጤቶች ጋር ተያይዞ ሊቀየሩ ይችላሉ )