በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ ከምሽት አንድ ሰዓት ጀምሮ የተደረገው የአዲስ አበባ እና በኮቪድ ውጤቶች ምክንያት ከሊግ ካምፓኒው ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባው የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በፈረሰኞቹ የ3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በ14ኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና የተረቱት አዲስ አበባ ከተማዎች በጨዋታው ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ ልመንህ ታደሰን እና ኤልያስ አህመድን በሮቤል ግርማ እና ዋለልኝ ገብሬ ምትክ ሲያስገቡ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ ከአርባ ምንጭ ከተማ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ አራት ለውጦችን በማድረግ በሄኖክ አዱኛ ፣ ምኞት ደበበ ፣ አቤል ያለው እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ምትክ ሻሂዱ ሙስጠፋን ፣ ደስታ ደሙን ፣ ናትናኤል ዘለቀን እና አዲስ ግደይን አሰልፈዋል ።በጨዋታው አዲስ አበባ ከተማዎች በመስመር በኩል በተለይም በፍፁም ጥላሁን በኩል የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ በተለይም ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ወደ አዲስ አበባ ከተማ የግብ ክልል ለመድረሰ ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።
በጨዋታው በአንፃራዊነት ኳሱን ይዘው ለመጫወት ችለው የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በ18ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል ። ፍፁም ጥላሁን በቀኝ መስመር ላይ ሆኖ ከኤልያስ አህመድ የደረሰውን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት ወደ ግብ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ሲመለስ ያገኘው እንዳለ ከበደ ኳሱን መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል ።
ከግቡ በኋላ ፈረሰኞቹ በተሻለ ወደ ፊት በመሄድ ለመጫወት የቻሉ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማዎች በራሳቸው የሜዳ ክፍል ላይ በዛ ብለው በመገኘት የተጋጣሚያቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማቋረጥ ጥረቶችን አድርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -
25ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ወልዴ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የመታውን ኳስ የአዲስ አበባ ከተማው ግብ ጠባቂ ዳንኤል ተሾመ የተቆጣጠረው ሲሆን ከአንድ ደቂቃ በኋላ በተቃራኒው ፍፁም ጥላሁን ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ ኢላማውን ስቶ ወጥቷል ። በ36ኛው ደቂቃ ላይም በድጋሚ በረከት ወልዴ ከማዕዘን የተነሳ ኳስ ሲመለስ አግኝቶ ከሳጥኑ በቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ ሊወጣ ችሏል ።
በረጃጅም ኳሶች አሁንም ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ የሞከሩት ፈረሰኞቹ በቀላሉ የአዲስ አበባን የተከላካይ መስመር አልፈው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ነበር ። የመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ጋቶች ፓኖም ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በዳንኤል ተሾመ ተመልሶ አዲስ ግደይ ቢያገኘውም የአዲስ ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
በሁለተኛው አጋማሽም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በረጃጅም ኳሶች ወደ ግብ የመድረስ ፍላጎቶችን ያሳዩ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በኩል በፈጣን እንቅስቃሴ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በተለይም በግራ መስመር ባደላ መልኩ በሚደረጉ ጫናዎች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን አድርገዋል ።
በ48ኛው ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኙትን የቅጣት ምት ሱሌማን ሀሚድ ወደ ግብ በጥሩ ሁኔታ አሻግሮት የነበረ ቢሆንም በኦጎሮ የተጨረፈውን ኳስ ናትናኤል ዘለቀ ለጥቂት ሳይደርስበት ቀርቷል። በ56ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ለበአዲስ አበባ ከተማ በኩል ፍፁም ጥላሁን በመልሶ ማጥቃት ይዘው የገቡትን ኳስ ነፃ ሆነው የሚጠብቁት ተጫዋቾች የነበሩ ቢሆንም በራሱ የሞከረው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል ።65ኛው ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ አቻ መሆን የቻሉበትን ግብ ማግኘት የቻሉ ሲሆን ሙሉቀን አዲሱ በሳጥን ውሰጥ በአዲስ ግደይ ላይ ጥፋት ሰርቷል በሚል ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ቶጓዊው አጥቂ እስማኤል ኦሮ ኦጎሮ ግብ አድርጎታል ።
በዚህም አጥቂው በውድድር አመቱ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛቶች 10 በማድረስ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በ2 ግቦች ልዩነት መምራት ጀምሯል ። ከግቡ በኋላ አዲስ አበባዎች የተሻለ ኳሱን በመያዝ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን የግብ ሙከራዎችን በማድረጉ ረገድ ግን ተቸግረው ታይተዋል ።
በ85ኛው ደቂቃ ላይ ምንም እንኳን ኳሱ ሲወጣ የመጨረሻው ንክኪ የአላዛር ሳሙኤል ቢሆንም ፈረሰኞቹ ያገኙትን የማዕዘን ምት ሱሌማን ሀሚድ አሻምቶት ናትናኤል ዘለቀ ግብ በማድረግ ፈረሰኞቹን መሪ ማድረግ ችሏል ። ከአምሰት ደቂቃዎች በኋላም በፈጣን መልሶ ማጥቃት አዲስ ግደይ ከሀይደር ሸረፋ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ እየገፋ ሄዶ በማስቆጠር የፈረሰኞቹን መሪነት ወደ 3 ለ 1 ከፍ አደረገ ይህም ለረጅም ጊዜያት በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ ለነበረው አዲስ ጥሩ ጅማሮ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ። በመጨረሻም ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 አዲስ አበባ ከተማ 1 ሆኖ ጨዋታው ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 31 በማድረስ የመጀመሪያውን ዙር ከተከታዩ በአራት ነጥብ ልዩነት ማጠናቀቁን ሲያረጋግጥ አዲስ አበባ ከተማ በበኩሉ በ14 ነጥብ በነበረበት 14ኛ ደረጃ ለመቆየት ተገዷል ።
በ16ኛው ሳምንት ( አዳማ ከተማ ) አዲስ አበባ ከመታ ባህርዳር ከተማን ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ሰበታ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል ።