የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ አሰልጣኙን ካሰናበተ በኋላ በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ውጤቶችን ይዞ እየወጣ ያለውን አዲስ አበባ ከተማን በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ከሚመራው ወልቂጤ ከተማ ጋር አገናኝቶ የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ የብሄራዊ ቡድኑ አጥቂ ጌታነህ ከበደ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ወልቂጤ ከተማ 1 ለ 0 አሸንፎ ወቷል ።
አዲስ አበባ ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን ባሸነፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ አንድ ቅያሪ ብቻ በማድረግ ብዙአየሁ ሰይፉን ወደ ጨዋታው ሲያስገቡ በወልቂጤ ከተማ በኩል ደግሞ በስድስተኛው ሳምንት ከተጠቀሙት ቋሚ 11 ስድስት ያህል ቅያሪዎችን በማድረግ ሀብታሙ ሸዋለም ፤ ተስፋዬ ነጋሽ ፤ በሀይሉ ተሻገር ፤ ዮናስ በርታ ፤ ያሬድ ታደሰ እና እስራኤል እሸቱን ጨዋታውን እንዲጀምሩ አድርገዋል ።
በጨዋታው በሁለቱም በኩል ወደ በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ፊት ለመሄድ ሙከራዎችነሰ አድርገዋል ። አዲስ አበባ ከተማዎች በፈጣን ቅብብል ወደ ጎሎች ለመድረስ ሲሞክሩ በወልቂጤ ከተማ በኩል ረጃጅም ኳሶችን የመጠቀም ሁነቶች ተመልክተናል ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የመጀመሪያ ዕድል ያገኙት ወልቂጤ ከተማዎቾ የነበሩ ሲሆን ተስፋዬ ነጋሽ በረጅም የተላከለትን ኳስ ተከላካዮችን በፍጥነት አልፎ ያገኘውም ቢሆንም ፊት ለፊቱ ለመጣበትን ግብ ጠባቂን በአየር ላይ ለማሳለፍ ሲሞክር ኳሱ በመርዘሙ ወደ ውጪ ወቶበታል ። በአዲስ አበባ ከተማ በኩል 5ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ከበደ ለፍፁም ጥላሁን በሳጥን ውስጥ ጥሩ ኳስ ቢያቀብለውም ፍፁም ሳይደርስበት ቀርቷል ።
በተከታዮቹ ደቂቃዎች በብዛት ቶሎ ቶሎ የመቀማማት እና አንድ ቡድን ኳሱን ይዞ ጫና ማሳደር ያልቻለበት ነበር ። ነገር ግን የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ጨዋታው ፈጠን ብሎ የግብ ዕድሎች የታዩበት ነበር ። 41ኛ ደቂቃ ላይ ፍፁም አለሙ ከመሀል ክፍል የደረሰውን ኳስ ረመዳን የሱፍን አልፎ ከፊቱ የነበረው አበባው ቡጣቆም ወድቆለት ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም በማይታመን ሁኔታ የመታው ኳስ ወደ ውጪ ወቷል ። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ወልቂጤ ከተማዎቾ ያገኙትን የቅጣት ምት ሀብታሙ ሸዋለም ወደ ግብ ሲያሻማው በአዲስ አበባ ተከላካዮች ስህተት ነፃ የነበረው ጌታነህ ከበደ በግንባሩ ገጭቶ አስቆጠረው ።
በሁለተኛው አጋማሽ በስፋት አዲስ አበባ ከተማዎቾ ቅያሪዎችን በማድረግ ውጤቱን ለመቀልበስ የሞከሩበት ነበር ። 54ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተነሳውን ኳስ ሳሙኤል ተስፋዬ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ በሲልቭያን ግቦሆ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። አዲስ አበባ ከተማዎች ጫና አሳድረው ግብ ለማግኘት ሙከራዎቻቸወን የቀጠሉ ሲሆን በወልቂጤ ከተማ አልፎ አልፎ ወደ ፊት በመሄድ ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።
63ኛ ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከአዲስ አበባው ተከላካይ ሳሙኤል የነጠቀውን ኳስ ለአብዱልከሪም ወርቁ አቀብሎት አብዱልከሪም ጠንከር አድርጎ ሳይመታው ዳንኤት ተሾመ በቀላሉ ይዞታል ። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ጨዋታው ቀዝቀዝ ብሎ ቀጥሎ ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በወልቂጤ ከተማ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎም አዲስ አበባ ከተማ በ10 ነጥብ ባለበት 5ኛ ደረጃ ላይ የሚቆይ ሲሆን አሸናፊው ክለብ ወልቂጤ ከተማ ነጥቡን 12 በማድረስ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 2ኛ ላይ ተቀምጧል ።