በስምንተኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ በቀዳሚነት የተገናኙት አርባምንጭ ከተማ እና አዳማ ከተማ ሲሆኑ ለ80 ያህል ደቂቃዎች 1 ለ 0 ሲመሩ የቆዩት አዞዎቹ በተጨማሪ ሰዓት በተቆጠረባቸው ግብ አቻ ተለያይተው ለመውጣት ተገደዋል ።
አርባምንጭ ከተማ በሰባተኛው ሳምንት ከጅማ አባጅፋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አስራአንድ የአራት ተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ወርቅይታደስ አበበ ፤ አንድነት አዳነ ፤ መላኩ ኤልያስን እና ኤሪክ ካፓይቶን ወደ አሰላለፍ ሲመልሱ በአዳማ ከተማ በኩል ደግሞ አዳማ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ሁለት ቅያሪ በማድረግ ኤልያስ ማሞን እና ጅብሪል አህመድን በቋሚ አሰላለፉ ማካተት ችለዋል ።
ለአይን ሳቢ በሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተጀመረው ጨዋታ በተለይም በአዞዎቹ የማጥቃት አጨዋወት የታጀበ ነበር ። በከባድ የማጥቃች አጨዋወት የቀጠሉት አርባ ምንጭ ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር 10 ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጀባቸው ። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ሙና በቀለ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ኬንያዊው ኤሪክ ካፓይቶ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር አዞዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ ። መሪዎቹ አርባምንጭ ከተማዎች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ፊት የሚያደርጉት ጥረት ለአዳማ ከተማ ተከላካዮች ከባድ ፈተና ሆኖባቸው ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
አዳማ ከተማዎች በጥቂት አጋጣሚዎች ወደ ፊት ሄደው ጫና ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት በአርባምንጭ ተከላካዮች የከሸፈ ሲሆን 36ኛ ደቂቃ ላይ ግን በአሜ መሀመድ አማካኝነት ከቅጣት ምት በተነሳ ኳስ ያደረጉት የግብ ሙከራ በግብ ጠባቂው ተመልሷል ። በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ አዳማ ከተማዎች ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ መሆን ችለው ነበር ። በዚህም 38ኛ ደቂቃ ላይ አበዲሳ ጀማል በሳጥን ውስጥ ሆኖ ከአሜ መሀመድ የደረሰውን ከግብ ጠባቂው የተተፋ ኳስ ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ በአጨራረስ ድክመት ሳያስቆጥረው ቀርቷል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በአርባምንጭ ከተማ መሪነት ተጠናቀቀ ።
የሁለተኛው አጋማሽ አዳማ ከተማዎች በተወሸነ መልኩ የበላይ ሆነው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩበት ነበር ። 53ኛ ደቂቃ ላይ ሀቢብ ከማል ከቅጣት ምት ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው መልሶ የማዕዘን ምት አድርጎታል ። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ተቀይሮ የገባው አቡበከር ወንድሙ ከመስመር የተሻገረለተን ኳስ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት በግብ ጠባቂው ይስሀቅ ተመልሶበታል ።
አርባምንጭ ከተማዎች በአመዛኙ በራሳቸው ሜዳ ላይ ሆነው በመጫወት ያገኟትን ግብ አስጠብቀው ለመውጣት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን 77ኛ ደቂቃ ላይ ተበይሮ የገባው አቡበከር ሻሚል ግብ ጠባቂውን አልፎ ያመከነው ኳስ ለአዞዎቹ አስቆጪ ነበር ። የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ከፍተኛ ጫና በማድረግ ላይ የነበሩት የፋሲል ተካልኝ ልጆች ድካማቸው ባለቀ ሰዓት ፍሬ አፍርቶላቸዋል ። ከቅጣት ምት የተመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ይስሀቅ ተገኝ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ኳሱ የደረሰው ዳዋ ሆቴሳ አስቆጥሮ አዳማ ከተማዎችን ከሽንፈት ታድጓል ።
ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ ነጥቡን 11 በማድረስ በግብ ክፍያ ተበልጦ 8ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አዳማ ከተማ ደግሞ በ9 ነጥብ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል ።