የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሁለት ሳምንት መቋረጥ በኋላ በዛሬው ዕለት ወደ ውድድር ተመልሷል ። ሊጉ ቀደም ብሎ የሶስት ሳምንታት ጨዋታዎችን ያካሄደ ሲሆን የአራተኛ ሳምንት መርሀ ግብሮችም በአርባምንጭ ከተማ እና በባህርዳር ከተማ መካከል በተደረገ ጨዋታ ተጀምሯል ።
ቀን 9 ሰዓት ጀምሮ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታድየም በተካሄደው ጨዋታ በሶስተኛው ሳምንት አዲስ አበባ ከተማን ከመመራት ተነሰቶ 2 ለ 1 ያሸነፈው አርባምንጭ ከተማ ዛሬም በተመሳሳይ ሁኔት ባህርዳር ከተማን ከመመራት ተነስቶ 2 ለ 1 አሸንፏል ።
በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመራው አርባምንጭ ከተማ በሶስተኛ ሳምንት ከተጠቀመው ቋሚ 11 አንድ ቅያሪ ብቻ በማድረግ አንድነት አዳነን ወደ ቋሚ አሰላለፍ ያስገባ ሲሆን በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሚመራው ባህርዳር ከተማ ደግሞ አራት ቅያሪዎችን በማድረግ ጨዋታውን የጀመረ ሲሆን ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑሪን ፤ መሳይ አገኘው ፤ ሳለአምላክ ተገኝ እና ዜናው ፈረደ በቋሚ አሰላለፉ አካቷል ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው ባህርዳር ከተማ በተደጋጋሚ ኳስን ከኋላ መስርተው በመውጣት ለመጫወት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በአርባምንጭ ከተማ በኩል በተቃራኒ ሜዳ በዝተው በመግባት እና ባህርዳር ከተማዎች ኳስን በቀላሉ ይዘው መውጣት እንዳይችሉ ሲያደርጉ ተስተውሏል ።
በመጀመሪያው አጋማሽ በባህርዳር ከተማ በኩል በአንዳንድ አጋጣሚዎች በሁለቱ ክንፎች በኩል በመሄድ ወደ ግብ ክልል ለመድረስ ሞክረው የነበረ ሲሆን በዚህ አይነት እንቅስቃሴ በቀኝ መስመር ላይ ፍፁም አለሙ ከመሳይ አገኘው የደረሰውን ኳስ የአርባምንጭ ተከላካይን በግሩም ሁኔታ በማለፍ ወደ ግብ ይዞ የሄደውን ኳስ አክርሮ በመምታት ባህርዳር ከተማን መሪ ማድረግ ቻለ ።
ከግቧ መቆጠር በኋላ አርባምንጭ ከተማዎች ወደፊት በተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም ወደ ግብ በመድረስ እና የተሳኩ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ በኩል ግን እምብዛም ነበሩ ። የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ 44 ደቂቃ መጠበቅ የተገደዱት አዞዎቹ በተጠቀሰው ደቂቃ ሀቢብ ከማል ከጨርቃዋ አካባቢ ወደ ግብ የመታው ኳስ በባህርዳር ከተማ ግብ ጠባቂ አበቡበከር ኑሪ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሊሆን ችሏል ። ከአንድ ደቂቃ በኋላም አዞዎቹ በአጥቂያቸው ኤሪክ ካፒያቶ አማካይነት ድንቅ የግብ ሙከራ ቢያደርጉም በአቡበከር ተመለሷል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ የባህርዳር ከተማ ግብ ጠባቂ ኳስ ይዞ በረጅም ለመምታት በሚሞክርበት ሰዓት ከሳጥን ውጪ ይዞ ወቷል በሚል በረዳት ዳኛው ጠቋሚነት አዞዎቹ ከሳጥኑ ጫፍ ላይ የቅጣት ምት አገኙ ። የቅጣት ምቱንም 23 ቁጥር ለባሹ ሀቢብ ከማል በግራ እግሩ በግሩም ሁኔታ አስቆጠረ ። የመጀመሪያ አጋማሽም በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ በተለይም በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ክፍት የነበረ እና በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ ችለዋል ። አርባምንጭ ከተማዎች በተሻለ ወደ ግብ በመድረስ እና በተደጋጋሚ ወደ ባህርዳር ከተማ ሳጥን አካባቢ በመድረስ እና አልፈውም በመግባት የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ቢሞክሩም ኢላማቸውን ግን የጠበቁ አልነበሩም ። ባህርዳር ከተማዎች ከኋላ መስርተው ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት ተጭነው በሚጫወቱት የአርባምንጭ ከተማ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ሲነጠቁ እና በራሳቸው ላይ ጫና እንዲፈጠርባቸው አድርጎ ነበር ። በጨዋታው 67ኛ ደቂቃ ላይ በዝውውር መስኮቱ ባህርዳር ከተማን የተቀላቀለው እና ጉዳት ላይ የነበረው አሊ ሱሌማን ተቀይሮ በመግባት የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል ።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ወደ ስምንት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት የአርባምንጭ ከተማው አጥቂ ኤሪክ ኪፕያቶ በሳጥን ውስጥ ተከላካዮችን አልፎ ግብ ለማስቆጠር በሚጥርበት ጊዜ ተቀይሮ በገባው አህመድ ረሺድ ጥፋት ተሰርቶበት አዞዎቹ የፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ቻሉ ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም አምበሉ ወርቅይታደስ አበበ 83ኛ ደቂቃ ላይ በማስቆጠር አርባምንጭ ከተማን 2 ለ 1 እንዲመራ አስቻለ ።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ባህርዳር ከተማዎች ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ወደ ፊት በመሄድ ግብ ለማግኘት ቢጥሩም ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል ። ጨዋታውም በአርባምንጭ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።
በዚህም አርባምንጭ ከተማ ነጥቡን ወደ 7 ሲያሳድግ ባህርዳር ከተማ ደሞ ባለበት 7 ነጥብ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።