በ29ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባምንጭ ከተማን በከንዓን ማርክነህ ብቸኛ ግብ ማሸነፍ ችሏል።
ቀን 10:00 ሰዓት ሲል በባህርዳር ስታዲየም በዝናብ ታጅቦ በተካሄደው ጨዋታ ምንም እንኳን በጨዋታዉ የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ግብ ቢስተናገድበትም በሁለቱም ክለቦች በኩል እጅግ ለእይታ ማራኪ የነበረ እንቅስቃሴን ተመልክተንበታል። በተለይ በአዞዎቹ በኩል በሜዳዉ የመሐል ክፍል ላይ እና በመስመር በኩል ረጃጅም ኳሶችን ለፊት መስመር አጥቂዉ አህመድ ሁሴን ለማድረስ ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋለ ሲሆን ምንም እንኳን ይህ ጥረታቸዉ ፍሬ አፍርቶ በአጋማሹ ግብ ማስቆጠር ባይችሉም ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን ግን መፍጠር ችለዉ ነበር።
በአንፃሩ በፈረሰኞቹ በኩል ደግሞ ያላቸዉን የነጥብ የበላይነት አስጠብቀዉ ለመዉጣት በሚመስል መልኩ በአመዛኙ ጥንቃቄ የታከለበት የጨዋታ መንገድን ቢከተሉም ነገር ግን ለተጋጣሚያቸዉ አርባምንጭ ቀላል አልነበሩም። በተመሳሳይ በመሐል ሜዳዉ ላይ ያመዘነ እና በተጨማሪም በሜዳዉ ዳር እና ዳር ከአማኑኤል እና ቸርነት በሚነሱ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ሲታትሩ ተስተውሏል። ለዚህም ማሳያ ጨዋታዉ በተጀመረ ገና በ9ኛዉ ደቂቃ ላይ ከከንአን ማርክነህ የተቀበለዉን ኳስ የፊት አጥቂዉ ኦሮ አጎሮ ወደ ግብ ሲሞክር ግብ ጠባቂዉ ይስሀቅ በሚመልስበት ሰዓት በአቅራቢያው የነበረዉ ከንአን ኳሷን አግኝቶ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ከግቧ መቆጠር በኋላ በተደጋጋሚ ለቁመተ መለሎዉ አጥቂያቸው በሚጣሉ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ሙከራቸዉን የቀጠሉት አዞዎቹ በ 32ኛዉ ደቂቃ ላይ ድንቅ ሙከራን ማድረግ ችለዉ ነበር በዚሁ ደቂቃ ላይም መላኩ ኤልያስ ከቀኝ መስመር በኩል ያሻገረዉን ኳስ አጥቂዉ አህመድ ሁሴን ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ለጥቂት ወጥታለች።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ግብ አስቆጥረዉ መሪ መሆን ከቻሉ በኋላ የበልጥኑ ጥንቃቄ የታከለበት ጨዋታ ሲከተሉ የነበሩት ፈረሰኞቹ በ40ኛዉ ደቂቃ ላይ ሙከራን ማድረግ ችለዉ ነበር። በዚሁ ደቂቃም ከማዕዘን የተሻገረዉን ኳስ ቸርነት ጉግሳ በግንባሩ በመግጨት ለግብ የቀረበ ሙከራን ማድረግ ችሎ ነበር።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ የ3 ደቂቃዎች እድሜ ሲቀሩት ደግሞ አዞዎቹ በ አማካኝት ለግብ የቀረበ ድንቅ ሙከራን ማድረግ ችለዉ ነበር ፤ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ አህመድ ሁሴን ተቆጣጥሮ ግብ ጠባቂዉን ካለፈ በኋላ ለሱራፌል ዳንኤል አቀብሎት የነበረ ቢሆንም የተጫዋቹን ሙከራ ተከላካዮቹ ደርሰዉ አዉጥተዉበታል።
ከዕረፍት መልስ በተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ የቀጠለ የሚመስለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በተለይ ከበድ ባለ ዝናብ ታጅቦ ደቂቃዎች እየገፉ በመጡ ቁጥር ግን ፈረሰኞቹ ጨዋታዉን በማረጋጋት እና አልፎ አልፎ በሚገኙ የመልሶ ማጥቃት እድሎች ተጨማሪ ግብን ለማስቆጠር ሲሞክሩ ተስተዉሏል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በ69ኛዉ ደዊቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ ከመስመር ተጫዋቹ አማኑኤል የተቀበለዉን ኳስ ቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም የግብ ዘቡ ይስሀቅ የመለሰበት አጋጣሚ በፈረሰኞቹ በኩል እጅግ አስቆጭ ሙከራ ነበር ፤ ከደቂቃዎች በኋላ በ82ኛዉ ደቂቃ ላይ በድጋሚ ከመልሶ ማጥቃት የተገኘዉን ድንቅ ኳስ ቸርነት አሁንም ቢሞክርም ግብ መሆን ሳይችል ቀርቷል።
በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ መጣል በጀመረዉ ከባድ ዝናብ የተፈተኑ የሚመስሉት አዞዎቹ በተደጋጋሚ ለአጥቂዉ አህመድ ይላኩ ከነበሩት ኳሶች ዉጭ ይህ ነዉ ሊባል የሚችል ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዉ ጨዋታዉ በፈረሰኞቹ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ዉጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ62 ነጥብ 1ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አርባምንጭ ከተማ በአንፃሩ በ40 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።