በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሁለተኛ ቀን ውሎ ከቀን 10 ሰዓት ጀምሮ የተካሄደው የአርባ ምንጭ ከተማ እና የሰበታ ከተማ ጨዋታ በመጀመሪያው እና በሁለተኛው አጋማሽ ላይ በተቆጠሩ ግቦች 1 ለ 1 ተጠናቋል ።
በ14ኛው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ምንም ግብ የተለያዩት አርባምንጭ ከተማዎች በጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ሙና በቀለን በአሸናፊ ኤልያስ ተክተወው የገቡ ሲሆን በሳምንቱ ከባህርዳር ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ሰበታ ከተማዎች ደግሞ በጨዋታው ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ በረከት ሳሙኤልን በወልደአማኑኤል ጌቱ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል ።በድሬዳዋ ዛሬ በጣለው ዝናብ ምክንያት ሜዳው በተወሰነ መልኩ ጭቃማ እንዲሁም በአንዳንድ የሜዳው ክፍሎች ላይ ውሀ ቋጥሮ የነበረ ሲሆን የቋጠርረውን ውሀ በተወሰነ ለመቀነስ ጥረቶች ከተደረጉ በኋላ ነበር የአርባ ምንጭ ከተማ እና የሰበታ ከተማ ጨዋታ ጅማሮውን ያደረገው ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች ኳሱን ይዘው በመጫወት ወደ ፊት ለመድረስ ሲጥሩ በአንፃሩ አርባምንጭ ከተማዎች በፈጣን ሽግግሮች እና ረጃጅም ኳሶች የሰበታ ከተማን የኋላ መስመር ለመፈተን ሞክረዋል ።በጨዋታው 14ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ኤልያስ ከተቃራኒ አቅጣጫ ከፀጋዬ አበራ የደረሰውን ኳስ በቀኝ መስመር በኩል ሃይለሚካኤል አደፍርስን አልፎ ወደ ሳጥን በፍጥነት ይዞ በመግባት ለእንዳልካቸው መስፍን የቀነሰለት ኳስ እንዳልካቸው ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
ከደቂቃዎች በኋላም በላይ ገዛኸኝ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ይዘው የሄዱትን ኳስ በላይ ገዛኸኝ ለአሸናፊ ኤልያስ አቀብሎት ወደ ሳጥን በመግባት መልሶ የደረሰውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠብቅ ኳሱን ወደ ውጪ ልኮታል ። በ24ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ በላይ ገዛኸኝ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ሞክሮት የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂውን እና የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወጥቷል ።
የግብ ዕድሎችን በቀላሉ ለመፍጠር ተቸግረው ነበሩት ሞግሌዎቹ 29ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር ። በአጋጣሚው ሃይለሚካኤል አደፍርስ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ያሻማውን ኳስ ያገኘው ሳሙኤል ሳሊሶ አረጋግቶ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል ። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሰበታ ከተማዎች ኳሱን ይዘው ወደ ፊት ለማለፍ የሚያደርጓቸው ጥረቶች ወደ ግብ ክልል ደርሰው ሙከራ ሳይደረግባቸው ይመለሱ የነበረ ሲሆን የሚመለሱትን ኳሶች አዞዎቹ በፈጣን ይዘው በማለፍ የግብ ዕድሎችን ለማግኘት ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ከማዕዘን በተነሳ ኳስ ወልደአማኑኤል ጌቱ ግብ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወቷል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በአርባ ምይጭ ከተማ የ1 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ በአርባምንጭ ከተማም ሆነ በሰበታ ከተማ በኩል ኳሱን ይዘው በመጫወት ለመጀመር ፍላጎቶች ያሳዩ ሲሆን አጋማሹ ከተጀመረ ከሶሰት ደቂቃዎች በኋላ ሰበታ ከተማዎች ግብ ማግኘት ችለዋል ። ግብ አስቆጣሪው ሳሙኤል ሳሊሶ ሲሆን ከበሀይሉ ግርማ በረጅም የደረሰውን የአየር ላይ ኳስ በግንባር በመግጨት 48ኛው ደቂቃ ላይ ሞግሌዎቹን አቻ አድርጓል ።አርባምንጭ ከተማዎች በተወሰነ ብልጫውን መውሰድ ቢችሉም የሰበታ ከተማን የኋላ መስመር አልፈው የግብ ዕድሎችን መፍጠር አልቻሉም ። በአንፃራዊነት ሰበታ ከተማዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
67ኛ ደቂቃ ላይ በአብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ሳሙኤል ሳሊሶ በቀጥታ ወደ ግብ ልኮት በግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። ከውሀ እረፍት መልስ ሰበታ ከተማዎች መሉ ለመሉ ብልጫ ወስደው በመጫወት የመጨረሻዎቹን 20 ደቂቃዎች በአርባ ምንጭ ከተማ የሜዳ ክፍል ላይ ማሳለፍ ችለዋል ።
በ75ኛው ደቂቃ ላይ በሰበታ ከተማ በኩል ከማዕዘን የተነሳ ኳስ በግንባር ተገጭቶ ሲመለስ ያገኘው ተከላካዩ አንተነህ ተስፋዬ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል ። የሰበታ ከተማዎች እንቅስቃሴ በአመዛኙ በግራ መስመር በኩል ያደላ ሲሆን በዚሁ አቅጣጫ 79ኛ ደቂቃ ላይ ዱሬሳ ሹቢሳ እየገፋ ይዞ የሄደውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት ለጥቂት ኢላማውን ስቷል። ከአምሰት ደቂቃዎች በኋላም በማዕዘን መምቻው አቅራቢያ ያገኙትን የቅጣት ምች ሳሙኤል ሳሊሶ በቀጥታ ወደ ግብ መቶት በግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋ ተመልሷል ። በመጨረሻም ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤቶ ተጠናቋል ።ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ ነጥቡን 18 ያደረሰ ሲሆን በደረጃው ላይ ጌይ ለውጥ ሳያደርግ 10ኛ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ሰበታ ከተማ ደግሞ በ9 ነጥብ የመጀመሪያውን ዙር የሊጉን ግርጌ በመያዝ ማጠናቀቁን አረጋግጧል ።
በ16ኛው ሳምንት ( አዳማ ከተማ ) አርባምንጭ ከተማ መከላከያን ሰበታ ከተማ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚገጥሙ ይሆናል ።