በ21ኛው ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ በቀዳሚነት በተደረገው የአርባምንጭ ከተማ እና የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ ሰራተኞቹ ወልቂጤ ከተማዎች በአንጋፋዎቹ ተጫዋቾቻቸው ጌታነህ ከበደ ( 2 ) እና አበባው ቡጣቆ ግቦች 3 – 0 አሸንፈዋል ።
አርባምንጭ ከተማዎች በ20ኛው ሳምንት በፋሲል ከነማ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አራት የተጫዋቾች ቅያሪ ያደረጉ ሲሆን ኡቸና ማርቲን ፤ አንዱአለም አስናቀ ፤ ሀቢብ ከማል እና ፍቃዱ መኮንንን በበርናንድ ኦቼንጌ ፤ አሸናፊ ፊዳ ፤ ኤሪክ ካፓይቶ እና በላይ ገዛኸኝ ምትክ ሲያሰለፉ በወልቂጤ ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ በፋሲል አበባየሁ እና ጫላ ተሺታ ምትክ አበባው ቡጣቆን እና አክሊሉ ዋለልኝ በመተካት ጨዋታውን ጀምረዋል ።በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ የወልቂጤ ከተማዎች አንድ ሁለት ቅብብል በአርባምንጭ ከተማ የሜዳ ክፍል በርከት ብሎ ቢታይም ወደ አዞዎቹ ግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ተቸግረው ነበር ። አርባምንጭ ከተማዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ በተለይም ከመስመር በሚነሱ ኳሶች የሰራተኞቹን የኋላ ክፍል ለመፈተን ጥረቶችን አድርገዋል ።
በሁለቱም በኩል የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች በግብ ሙከራዎች ያልታጀቡ መሆናቸው ጨዋታውን በተወሰነም ቢሆን አቀዝቅዞታል ።
ከውሀ እረፍት መልስ የጨዋታ ብልጫውን መልሰው የወሰዱት ሰራተኞቹ በ37ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ አስቆጥረዋል ።ጌታነህ ከበደ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የመታውን ኳስ የአርባምንጩ ተከላካይ ኡቸና ማርቲን በሳጥን ውስጥ ሆኖ በእጁ በመመለሱ ወልቂጤ ከተማዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ጌታነህ አስቆጥሮ መሪ መሆን ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
ከግቡ በኋላ አዞዎቹ ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ወደ ግብ ለመድረስ የሚያደርጓቸው የነበሩ ጥረቶች የታለሙበት ቦታ ሳይደርሱ በወልቂጤ ከተማው ግብ ጠባቂ በሮበትርት ኦዶንካራ ይያዙ ነበር ።
የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩ ሶስት ደቂቃዎች ላይ ሳምሶን አሰፋ ከሳጥን ውጪ ኳስ በእጅ ነክተካል በሚል ወልቂጤ ከተማዎች በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ የተሰጣቸውን የቅጣት አበባው ቡጣቆ ወደ ግብ ልኮት በወርቅይታደስ አበበ ግንባር ተጨርፎ በአርባምንጭ ከተማ መረብ ላይ አርፏል ።የመጀመሪያው አጋማሽም በወልቂጤ 2 – 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።
ወልቂጤ ከተማዎች ከእረፍት መልስ መሪነታቸውን ከፍ ያደረጉበትን ሶስተኛ ግብ ለማስቆጠር ስድስት ያህል ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጁባቸው ። በ51ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ ከግራ መስመር ወደ መሀል ያሻገረለትን ኳስ ኡቸና ማርቲን በአግባቡ ማራቅ ሲሳነው ያገኘው የመጀመሪያው ግብ አስቆጣሪ ጌታነህ ከበደ ኳሱን በቀኝ እግሩ ተቆጣጥሮ በግራ እግሩ በሳምሶን አሰፋ መረብ ላይ በማሳረፍ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሶስተኛ ግብ አስቆጥሯል ።በጨዋታው በሶስት ግቦች እየተመሩ የነበሩት አዞዎቹ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በተለያዩ አማራጮች ወደ ወልቂጤ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ እና የግብ ዕድሎችን ለማግኘት ጥረቶችን አድርገዋል ።
በ65ኛው ደቂቃ ላይ ወልቂጤ ከተማዎች በሶስት ተጫዋቾቻቸው አከታትለው አራት የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር ። ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ በቅድሚያ ጌታነህ ከበደ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ሞክሮ በኡቸና ማርቲን ሲመለስ በድጋሚ አግኝቶ ጌታነህ የመታውን ሳምሶን አሰፋ ሲመልሰው ጫላ ተሺታ ዳግም ወደ ግብ የላከውን ኳስ ደግሞ ወርቅይታደስ አበበ ግብ ከመሆን ሲያድነው በመጨረሻም ዋሁብ አዳምስ ያደረገው የግብ ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ ወጥቷል ።አዞዎቹ በጨዋታው የመጀመሪያ አላማውን የጠበቀ ሙከራ በ79ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጉ ሲሆን አንዱአለም አሰናቅ ከርቀት በአስደናቂ ሁኔታ ወደ ግብ የላከውን ኳስ የወልቂጤ ከተማው ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ በድንቅ ብቃት ኳስ እና መረብ እንዳይገናኙ ማድረግ ችሏል ።
የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች በተቃረቡበት 88ኛ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው በላይ ገዛኸኝ በረጅም የተሻገረለትን ኳስ ደረቱ ላይ አብርዶ አስቆጠረው ተብሎ የተጠበቀው ኳስ የግቡን የቀኝ ቋሚ ለትሞ ወደ ውጫ ወጥቷል ።በመጨረሻም የተመስገን ዳና ልጆች ከጨዋታው ሶስት ጎል እና ሶሰት ነጥብ ይዘው ወጥተዋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ ነጥቡን 28 በማድረስ ከ11ኛ ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አርባምንጭ ከተማ ደግሞ በ26 ነጥብ ወደ 10ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል ።በ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ( ባህርዳር ) በመጪው ሚያዝያ 29 ( ቅዳሜ ) ረፋድ 4 ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማ ጅማ አባጅፋርን ሲገጥም ወልቂጤ ከተማ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማን ከሁለት ቀናት በኋላ ግንቦት 1 ( ሰኞ ) ቀን 10 ሰዓት ጀምሮ የሚገጥም ይሆናል ።