በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሁለተኛ ቀን ውሎ ከምሽት 1 ሰዓት ጀምሮ የተደረገው ጨዋታ የባህርዳር ከተማ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ልክ እንደ ዕለተለ ቀዳሚ ጨዋታ አንድ ለአንድ ተጠናቋል ።
በ14ኛው ሳምንት ከሰበታ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ባህርዳር ከተማዎች በጨዋታው ከተጠቀሙት አሰላለፍ ሶስት ቅያሪዎችን በማድረግ የገቡ ሲሆን በሰለሞን ወዴሳ ፣ አለልኝ አዘነ እና ከሪም ኒኪማ ምትክ መሳይ አገኘሁን ፣ በረከት ጥጋቡን እና ኦሴ ማውሊን ጨዋታውን እንዲጀምሩ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ከፋሲል ከተማ በተመሳሳይ አቻ የተለያዩት ኢትዮጵያ ቡናዎችም ሶሰት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በአበበ ጥላሁን ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና አማኑኤል ዮሐንስ ምትክ ቴዎድሮስ በቀለ ፣ ያብቃል ፈረጃ እና እንዳለ ደባልቄን አስገብተዋል ።በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡናዎች እንደተለመደው ከኋላ ኳስን መስመርተው በመውጣት ለመጫወት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን ኳሱን ከራሳቸው የግብ ክልል አርቀው ለመጫወት ግን ተቸግረው ነበር ። ኳሶችን ወደ መሀል ሲያደርሱ በተደጋጋሚ በባህርዳር ከተማዎች ይነጠቁ የነበረ ሲሆን የጣና ሞገዶቹ የነጠቋቸውን ኳሶች በፈጣን ይዘው በመግባት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጓቸው ጥረቶች የተሳኩ አልነበሩም ።
በጨዋታው 4ኛ ደቂቃ ላይ ፍፁም አለሙ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ሆኖ የደረሰውን ኳስ ከፍ አድርጎ ወደ ግብ ልኮት የነበረ ቢሆንም ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ ወጥቷል ። ለብዙ ደቂቃዎች በግብ ሙከራዎች ያልታጀበው ጨዋታ ቀጣዩን የግብ ዕድል ያስመለከተን 30ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ። ሀይሌ ገብረትንሳይ በቀኝ አቅጣጫ ከቅጣት ምት ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ የባህር ዳር ከተማው ግብ ጠባቂ ፋሲል ገብረሚካኤል ግቡን ለቆ ወጥቶ እንዳለ ደባልቄ በግንባር የገጨው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ሊወጣ ችሏል ።ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ የጣና ሞገዶቹ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል ። ከሳጥኑ ቅርብ በግራ አቅጣጫ ላይ ሀይሌ ገብረትንሳይ ሳለአምላክ ተገኝ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ፍፁም አለሙ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ኳስ እና መረብን 33ኛ ደቂቃ ላይ ማገናኘት ችሏል ።
ይህም ግብ ፍፁም አለሙ በውድድር አመቱ ያስቆጠራቸውን የግቦች ብዛት ወደ 6 በማሳደግ በከፍተኛ ግብ አግቢነቱ ደረጃ ላይ ከእስማኤል ኦሮ ኦጎሮ እና ይገዙ ቦጋለ ቀጥሎ 3ኛ ላይ እንዲቀመጥ አስችሎታል ። ግቡ መቆጠር በኋላ ኢትዮጵያ ቡናዎች በተሻለ ወደ ባህርዳር የሜዳ ክፍል ጠጋ ብለው መጫወት የቻሉ ቢሆንም የባህርዳር ከተማን የተከላካይ መስመር እና ግብ ጠባቂውን የፈተነ የግብ ዕድል ግን መፍጠር አልቻሉም ።
43ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር በግራ በኩል ወደ ሳጥን ለመግባት ሲሞክር በመናፍ አወል ጥፋት የተሰራበት ሲሆን በሁነቱ ሁለተኛውን የቢጫ ካርድ የተመለከተው መናፍ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በባህርዳር ከተማ መሪነት ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ቡናማዎቹ ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱበት የቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው የጣና ሞገዶቹ ደግሞ አፈግፍገው በመጫወት በመልሶ ማጥቃቶች ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ። ኢትዮጵያ ቡናዎች በተለይም በግራ መስመር በኩል የባህርዳር ከተማ ሳጥን ውሰጥ ሰብረው በመግባት የግብ ዕድሎችን ለማግኘት ሞክረዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በ47ኛው ደቂቃ ላይ አስራት ቱንጆ በግራ መስመር ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት ፋሲል ገብረሚካኤል ያዳነበት ሲሆን ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ላይ አስራት ቱንጆ ከሮቤል ተክለሚካኤል የደረሰውን ኳስ ሞክሮ ኢላማውን ሳይጠብቅለት ቀርቷል ። ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት የካሳዬ አራጌ ልጆች 68ኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶላቸዋል ። የቡድኑ አምበል አቡበከር ናስር ሮቤል ተክለሚካኤል ከመሀል ሜዳ ያሻገረለትን ኳስ ተከላካዮችን አምልጦ በማለፍ በግሩም ሁኔታ ከተቆጣጠረ በኋላ አጨራረሱን በማሳመር ቡናማዎቹን አቻ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል ።ከግቡ መቆጠር በኋላ ቡናማዎቹ ሌላ ግብ ለማከል የሚችሉበትን አጋጣሚ መፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ። ተቀይሮ የገባው አላዛር ሽመልስ በቀኝ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ ወደ ግብ ሲሞክረው ፋሲል ገብረሚካኤል ሲያድንበት በፋሲል የተመለሰውን ኳስ እንዳለ ደባልቄ አግኝቶ በድጋሚ ቢሞክረውም ኳሱ ወደ ውጪ ወጥቷል ።
በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ባህር ዳር ከተማዎችም ቀድሞ ከነበረው ተነቃቀተው ለመጫወት የቻሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናዎችም ተጨማሪ ግቦችን ለማከል ያደረጓቸው ጥረቶች ሳይሳኩ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ ከጨዋታውም በፊት በእኩል 19 ነጥብ ላይ ይገኙ የነበሩት ሁለቱ ተጋጣሚዎች ነጥባቸውን 20 በማድረስ ደረጃቸውን ከፍ ያደረጉ ሲሆን ባህርዳር ከተማ 7ኛ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 9ኛ ላይ ተቀምጠዋል ።በ16ኛው ሳምንት ( አዳማ ከተማ ) ባህርዳር ከተማ አዲስ አበባ ከተማን ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ሲዳማ ቡናን የሚገጥሙ ይሆናል ።