በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ባህርዳርን ከቅዱስ ጊዮርጊስ አገናኝቶ በአቤል ያለው እና በከነአን ማርክነህ ግቦች ፈረሰኞቹ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ መሪነታቸውን አጠናክረዋል ።
በባህርዳር ከተማ በኩል በ10ኛ ሳምንት በሲዳማ ቡና በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አስራ አንድ የአንድ ተጫዋች ቅያሪ በማድረግ መናፍ አወል ከአሰላለፈሰ ውጪ በማድረግ አለልኝ አዘነን ያሰለፉ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ፋሲል ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ የነበረውን ቋሚ አሰላለፍ ምነም አይነት ለውጥ ሳያደርጉበት ጨዋታውን ጀምረዋል ።
የዕለቱ የመሀል ዳኛ የጨዋታውን መጀመር በፊሽካቸው ሲያበስሩ ጨዋታውን መጀመስ የቻሉት ፈረሰኞቹ ገና በ40ኛው ሰከንድ ነበር ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ ያገኙት ። ከግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ የተነሳው ኳስ በአቤል ያለው በእስማኤል ኦሮ አጎሮ በከነአን ማርከነህ በኩል አልፎ አማኑኤል ገብረሚካኤል ወደ ግብ ሲሞክረው የተፋውን ኳስ ያገኘው አቤል ያለው ግቡን አስቆጥሯል ።
- ማሰታውቂያ -
ባህርዳር ከተማዎች ኳሱን ከኋላ መስመርተው የመሄድ ፍላጎት ቢያሳዩም በተጋጣሚያቸው በሚደረግባቸው ጫና እና በነሱ መፈየሜዳ ክፍል ሲገቡ በቁጥር የሚወሰድባቸው ብለጫ በፈለጉት ልክ ወደ ግብ ክልል መድረስ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ። በፈረሰኞቹ በኩል በረጃጅም ኳሶች እና ከቆሙ ኳሶቾ የግብ ዕድሎችን በተለያዩ አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው ነበር ።
13ኛ ደቂቃ ላይ በእስማኣል ኦሮ አጎሮ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት አቤል ያለው አሻምቶ አምበሉ ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ለጥቂት ወደ ውጪ ወቷል ። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ በባህርዳር ከተማ ግብ ጠባቂ የሰተራው ጥፋት ለፈረሰኞቹ ሁለተኛ ግቅ መገኘት መንስኤ ሆኗል ።
በረጅም የተመታውን ኳስ ሰለሞን ወዴሳ እና ፈቱዲን ጀማል ሳይናበቡ ለግብ ጠባቂው የደረሰው ኳስ በአግባቡ ባለመያዙ በቅርብ የነበረው ከነአን ማርክነህ አግኝቶ የፈረሰኞቹን መሪነት ወደ 2 ለ 0 ከፍ አደረገ ። ግቡን ያስቆጠረው ከነአን ማርክነህ በ31ኛው ደቂቃ ላይ ጉዳት አጋጥሞት በበረከት ወልዴ ተቀይሮ ከሜዳ ሊወጣ ችሏል ።
በቅዱር ጊዮርጊስ በኩል በ35ኛው እና 41ኛ ደቂቃ ላይ በኦሮ አጎሮ እና ፍሪምፖንግ ሜንሱ አማካኝነት ከማዕዘን በተነሱ ኳሶች በግንባር ተገጭተው ወደ ግብ የተላኩት ኳሶች በግብ ጠባቂው ሊመለሱ ችለዋል ። የጣና ሞገዶቹ በአጋማሹ ያደረጉት ለግብ የቀረበ ሙከራ 36ኛ ደቂቃ ላይ የተደረገ ሲሆን ከሪም ኒኪማ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ፍፁም አለሙ አግኝቶ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ተጨርፎ ወደ ውጪ ወቷል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ሳለ በረጅም የተላከን ኳስ የቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር ተጫዋቾች ኦሮ ኦጎሮ እና አቤል ያለው ሳይናበቡ በአቤል አማካኝነት ተሞክሮ ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ምናልባትም የፈረሰኞቹን መሪነት ከዕረፍት በፊት ከፍ ማድረግ የሚችል ነበር ።
በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ክለቦች በኩል በአንፃራዊነት ከመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ብሎ የተካሄደ ነበር ። የጣና ሞገዶቹ ኳሱን ተቆጣጥረው ወደ ፊት ለመሄድ የሚያደርጉትን ጥረት ቢቀጥሉም የፈረሰኞቹ የተቀናጀ መከላከልን ሰብረው ለመግባት የተቸገሩበት ነበር ። በዚህም በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሳጥኑ ውጪ ያደርጓቸው የነበሩት ሙከራዎች ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ወደ ውጪ ይወጡ ነበር ።
በፈረሰኞቹ በኩል በጥሩ መከላከል እና በፈጣን ሽግግር ወደ ፊት ለማለፍ ጥረቶችን ያደርጉ የነበሩ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በቸርነት ጉግሳ እና በአማኑኤል ገብረሚካኤል አማካኝነት ከተደረጉት የግብ ዕድሎች ውጪ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ አልቻሉም ነበር ።
በመጨረሻም ቅዱር ጊዮርጊስ ጨዋታውን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ ነጥቡን 23 በማደርስ መሪነቱን ያጠናከረ ሲሆን ባህርዳር ከተማ በበኩሉ በ14 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚቆይ ይሆናል ።
በ12ኛ ሳምንት ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ሀዋሳ ከተማን ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ወልቂጤ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል ።