የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በባህርዳር አስገብተዋል በሀዋሳ ከተማ መካከል ተደርጎ ጣና ሞገዶቹ ከሪም ኒኪማ እና ፉአድ ፈረጃ ባስቆጠሯቸው ግቦች 2 ለ 0 በማሸነፍ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ሙሉ ሶስት ነጥበ ይዘው መውጣት ችለዋል ።
ባህርዳር ከተማ በ11ኛ ሳምንት ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ቅያሪ ያደረጉ ሲሆን በአቡበከር ኑሪን እና በተመስገን ደረሰ ምትክ ፋሲል ገብረሚካኤልን እና ፉአድ ፈረጃን ጨዋታውን ያስጀመሩ ሲሆን በሀዋሳ ከተማ በኩል ድሬደዋ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ አስራአንድ አንድ ቅያሪ ብቻ በማድረግ ጨዋታውን የጀመሩ ሲሆን አብዱልባሲጥ ከማልን በዳዊት ታደሰ ቀይረው አስገብተዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ጅማሮ ባህርዳር ከተማዎች ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ወደ ፊት ለመሄድ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በሀዋሳ ከተማ በኩል በፈጣን ሽግግሮች የባህር ዳር የተከለካይ መሰመርን ለመፈተን ሙከራዎች አድርገዋል ። ይህ ሂደት በተለይም ከውሀ እረፈት በኋላ በተገላቢጦሽ ሆኖ የተመለከትንበት ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
2ኛ ደቂቃ ላይ ከእጅ ውርወራ የተነሳን ፍፁም አለሙ ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ ለከሪም ኒኪማ ቀንሶለት የነበረ ቢሆንም ኒኪማ ወደ ግብ የላከው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወቷል ። 25ኛው ደቂቃ ላይ ሳለአምላክ ተገኝ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ዳንኤል ደርቤ ለማውጣት ሲሞክር እዛው ሳጥን ውሰጥ ኳሱ አየር ላይ ሳለ ላውረንስ ላርቴ እና መድኃኔ ብርሀኔ ባለመናበባቸው ምክንያት ኳሱ ለከሪም ኒኪማ ደርሶ የመጀመሪያው ግቡ ተቆጥሯል ።
በጨዋታው የባህርዳር ከተማው አማካይ አለልኝ አዘነ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ወዲያውኑ በቀጥታ ከሜዳ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል ። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በባህርዳር ከተማ 1 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ በአመዛኙ ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ፊት ሄደው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በሚደረጉ ሂደቶች ከተጋጣሚያቸው ተሽለው የታዩበት ነበር ። ነገር ግን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በሚደርሱበት ጊዜ የነበራቸው የኳስ ቅበብል እና የውሳኔ ድክመት ሀዋሳ ከተማዎች በቀላሉ የፋሲል ገብረሚካኤልን መረብ እንዳይደፍሩ አድርጓቸዋል ።
በ47ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም አለሙ ከአሊ ሱሌማን የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት በመሀመድ ሙንታሪ የተያዘበት ኳስ በአጋማሹ ቀዳሚው የግብ ሙከራ ነበር ። በተደጋጋሚ ወደ ባህርዳር ከተማ የግብ ክልል መድረስ ችለው የግብ ሙከራ ለማድረግ የተቸገሩት ሀዋሳ ከተማዎች 61ኛ ደቂቃ ላይ በመስፍን ታፈሰ የጭንቅላት ኳስ ጥሩ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር ።
በተፈጠረባቸው ጫና ወደ ኋላ አፈግፍገው የነበሩት የጣና ሞገዶቹ ቀስ በቀስ ወደ ፊት የመሄድ አጋጣሚዎችን መፍጠር በቻሉበት አጋጣሚ ሁለተኛ ግብ አስቆጥረዋል ። ፍፁም አለሙ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ፉአድ ፈረጃ በመድኃኔ ብርሀኔ እግሮች መሀል በማሳለፍ የባህርዳር ከተማን መሪነት ከፍ አደረገ ። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ በፈጣን መልሶ ማጥቃት አሊ ሱሌማን ሁለት ተጫዋቾችን በማለፍ ጭምር ይዞት የሄደውን ኳስ ብዙ አማራጮች ቢኖርቱም የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ወደ ግብ የመታው ኳስ ከግቡ አናት ባለይ ወጥቷል ።
መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ሊጠናቀቅ አራት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት ተቀይሮ የገባው አቤኔዘር ዮሐንስ ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ የመታው ኳስ በፋሲል ግበረሚካኤል ተመልሶ ሊወጣ የቻለ ሲሆን በመጨረሻም የዕለቱ ዳኛ የጨመሩት የባከነ አራት ደቂቃ ከተጠናቀቀ በኋላ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ ባህርዳር ከተማ ነጥቡን 17 በማድረስ ወደ 6ኛ ደረጃ ሲያሻሽል ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ ባለበት 20 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚቆይ ይሆናል ።
በ13ኛ ሳምንት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ፋሲል ከተማን ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል ።