በ25ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ተጠባቂ ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ በሜዳቸዉ እና በደጋፊዎቻቸው ፊት በሲዳማ ቡና 3ለ1 በሆነ ዉጤት ተሸንፈዋል።
ከተደጋጋሚ ዉጤት አልባ ጉዞ በኋላ ባለፈዉ በ24ኛዉ ሳምንት አዳማ ከተማን በጠባብ ዉጤት ማሸነፍ ከቻሉበት ስብስብ ፍፁም አለሙን እና ኦሴ ማዉሊን በፋአድ ፈረጃ እና አሊ ሱለይማን ቀይረዉ ወደ ሜዳ ሲገቡ በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ወላይታ ድቻን 1ለ0 ከረቱበት ስብስብ መሐሪ መናን በሰለሞን ሀብቴ ብቻ ቀይረዉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
በዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ መሪነት በጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በሁለቱም በኩል ዉጤቱን አጥብቆ ከመፈለግ አንፃር ብርቱ ፉክክርን ተመልክተንበታል።
በተለይ በጨዋታዉ የመጀመሪያ 25 ደቂቃዎች ያክል ተመጣጣኝ የኳስ ፍሰት የነበረ ቢሆንም በጥቂቱም ቢሆን በሙከራ ረገድ ባለሜዳዎቹ ባህርዳር ከተማዎች የተሻሉ ነበሩ በተለይ ደግሞ በ25ኛዉ ደቂቃ ላይ ከፊት መስመር አጥቂዉ ኦሲ ማዉሊ የተቀበለዉን ኳስ ተመስገን ደረሰ እክርሮ ወደ ግብ ቢልካትም ኢላማዋን ሳትጠብቅ ወጥታለች።
- ማሰታውቂያ -
ለ30 ደቂቃዎች ያህል በኦሲ ማዉሊ ፣ ተመስገን ደረሰ እንዲሁም ፍፁም አለሙ ተደጋጋሚ ሙከራ ያደርጉ የነበሩት ባህርዳር ከተማዎች ግብ ማስቆጠር ሳችሉ ቀርተዉ በተቃራኒው ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል።
ሰለሞን ሀብቴ ከማዕዘን ያሻማዉን ኳስ ረጅሙ ተከላካዩ ጊት ጋትኮት 31ኛዉ ደቂቃ ላይ በጭንቅላቱ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ወዲያዉኑ ወደ ባህርዳር የግብ ክልል የደረሱት ሲዳማዎች ቡድጋሚ ለግብ የቀረበ አደገኛ ሙከራን ማድረግ ችለዉ ነበር። ከአጥቂዉ ሳልሀዲን ሰይድ የተቀበለዉን ኳስ ይገዙ ቦጋለ ከሳጥን ዉጭ አክርሮ ወደ ግብ ቢልካትም በአቡበከር ኑሪ ድንቅ ብቃት ግብ መሆን ሳትችል ቀርታለች።
በ42ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ይገዙ ቦጋለ ከቀኝ መስመር በኩል ከሀብታሙ ገዛኸኝ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ በግራ ዕግሩ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡ ሲዳማ ቡና ክለቡ 2ለ0 እየመራ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመራ ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት መልስ አሊ ሱለይማንን በሰላምላክ ተገኝ ቀይረዉ ወደ ሜዳ የገቡት ባህርዳር ከተማዎች ወዲያዉኑ ወደ ጨዋታው የመለሰቻቸዉን ግብ ማግኘት ችለዉ ነበር።
በ50ኛዉ ደቂቃ ላይ አህመድ ረሽድ ተጫዋቾችን ቀንሶ ሳጥን ዉስጥ ሲገባ ተከላካዩ ጊት ጋትኮት እንደምንም ኳሷን ሲመልስ አጠገቡ የነበረዉ ፍፁም አለሙ ወደ ግብ ሲሞክር ኳሷ አንግሉን ገጭታ ስትመለስ በአቅራቢያዉ የነበረዉ አሊ ሱለይማን አስቆጥሮ ክለቡን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር 8 ደቂቃዎች በኋላ ግን ሲዳማ ቡናዎች ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ከአማካዩ ዳዊት ተፈራ የተሻገረለትን ኳስ የመስመር አጥቂዉ ሀብታሙ ገዛኸኝ በደረቱ አብርዶ ወደ ግብነት በመቀየር የክለቡን መሪነት ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ችሏል።
ሶስተኛ ግብ ካስተናገዱ በኋላ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ብልጫ በመዉሰድ ወደ ጨዋታው የሚመልሷቸዉን ግቦች ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ እንዳሰቡት ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ በሜዳቸዉ እና በደጋፊዎቻቸው ፊት በሲዳማ ቡና 3ለ1 በሆነ ዉጤት ተሸንፈዋል።
ዉጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በ40 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በአንፃሩ ባህርዳር ከተማዎች ደግሞ በ29 ነጥብ አስራአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በቀጣይ በ26ኛዉ ሳምንት ባህርዳር ከተማ ፈረሰኞቹ ጋር ሲገናኙ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ከአዳማ ከተማ ጋር የሚገናኙ ይሆናል።