በሰባተኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ የመጀመሪያ ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰአት ጀምሮ ባህርዳር ከተማን ከወላይታ ድቻ አገናኝቶ በባህርዳር ከተማ የ3 ለ 1 ድል ጨዋታው ተጠናቋል ።
ባህርዳር ከተማዎች በስድስተኛው ሳምንት ጅማ አባጅፋርን ባሸነፉበት ጨዋታ የተጠቀሙትን ቋሚ አሰላለፍ በድጋሚ ይዘው ሲገቡ በወላይታ ድቻ በኩል ደግሞ ከፋሲል ከተማ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ 11 የአንድ ተጫዋች ብቻ ቅያሪ በማድረግ አበባየሁ አጪሶ ጨዋታውን እንዲጀምር አድርገዋል ።
ባህርዳር ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ ወደ ወላይታ ድቻ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች በተወሰኑ አጋጣሚዎች በፈጣን ኳሶች ወደ ፊት ለመሄድ ጥረቶችን አድርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የመጀመሪያው የግብ ሙከራ 5ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ከግርማ ዲሳሳ የደረሰውን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ሞክሮት በግብ ጠባቂው የመለሰበት ነበር ።
ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት የጣና ሞገዶቹ የሶስተኛው የማጥቃት ክፍል ላይ ሲደርሱ የሚወስኗቸው ውሳኔዎች የግብ ዕድሎችን እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል ።
በ18ኛ ደቂቃ ላይ ባህርዳር ከተማዎች ቀዳሚ መሆን የሚችሉበትን ግብ በፍፁም አለሙ አማካኝነት ማግኘት ችለዋል ። የወላይታ ድቻ ተከላካዮች መዘናጋታቸውን ተከትሎ ፍፁም አለሙ ከሳጥን ውጪ ሳይታሰብ የመታው ኳስ ፅዮን መርዕድን አልፋ ግብ ሆናለች ።
በአንዳንድ አጋጣሚዎች ወደ ፊት ለማለፍ ጥረቶችን ያደረጉት የጦና ንቦቹ 23ኛ ደቂቃ ላይ በስንታየሁ መንግስቱ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ በመምታት የመጀመሪያ ሙከራ ቢያደርጉም ስንታየሁ ኳሱን ቀል አድርጎ በመምታቱ ፋሲል ገብረሚካኤል በቀላሉ ሊይዘው ችሏል ። የጣና ሞገዶቹ በተደጋጋሚ ወደ ጦና ንቦቹ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም በተለይም በግራ እና በቀኝ መስመር ወደ ግብ ክልል የሚያሻግሯቸው ኳሶች በተከላካዮች ይመለሱባቸው ነበር ።
ነገር ግን 38ኛ ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል የወላይታ ድቻን ተከላካይ ክፍል በማለፍ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ፍፁም አለሙ በሳጥን ውስጥ ይዞት የገባውን ኳስ በማስቆጠር የጣና ሞገዶቹን መሪነት ወደ 2 ለ 0 ከፍ አደረገ ።
የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት ምንይሉ ወንድሙ በሳጥኑ መግቢያ ላይ ሆኖ በአየር ላይ የደረሰውን ኳስ በጭንቅላት ገጭቶ ሳጥን ውስጥ ከተከላካዮች ጋር እየታገለ ለነበረው ለስንታየሁ መንግስቱ በማቀበል ፈጥኖ ወደ ግብ ክልል በመሮጥ በድጋሚ የተቀበለውን ኳስ ከመረብ አሳረፈ ።
በሁለተኛው አጋማሽ በመመራት ላይ የነበሩት የጦና ንቦቹ ወደ ፊት ተጭነው በመሄድ እና በተደጋጋሚ የባህርዳር ከተማን የተከላካይ ክፍል በመፈተን ግብ ለማግኘት የጣሩበት ሲሆን በጣና ሞገዶቹ በኩል በመጀመሪያዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ጥሩ በመንቀሳቀስ ከሳጥን ውጪ ኳሶችን ወደ ግብ በመላክ ሙከራዎችን በማድረግ እና ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላም ከኋላ በሚነሱ ፈጣን ኳሶች ግቦችን ለማግኘት ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ።
56ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም ከቀኝ መስመር ለስንታየሁ መንግስቱ የላከለት ኳስ እና ስንታየሁ ጎሉን ባዶውን አግኝቶ ኳሱን መቆጣጠር ባለመቻሉ ሳንጠቀምበት ቀርቷል ። በባህርዳር ከተማ በኩል ሁለቱን ግቦች ያስቆጠረው ፍፁም አለሙ ሁለት ጊዜ ወደ ግብ የሞከራቸው ኳሶች ጠንካራ ባለመሆናቸው በቀላሉ በፅዮን መርዕድ ተይዘውበታል ።
61ኛ ደቂቃ ላይ ስንታየሁ መንግስቱ የጦና ንቦቹን አቻ የሚያደርግበትን ዕድል ማግኘት ችሎ በድጋሚ አምክኖታል በዚህ አጋጣሚ ላይ የባህርዳር ከተማው አምበል አህመድ ረሺድ ለግብ ጠባቂው ለማቀበል በሚሞክርበት ጊዜ ኳሱ በማጠሩ ቀድሞ የደረሰበት እንድሪስ ሰይድ ነፃ ለነበረው ስንታየሁ ቢያቀብለውም ስንታየሁ የመታው ኳስ ወደ ውጪ ወቷል ።
ባህርዳር ከተማ ጅማ አባጅፋርን 2 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋታ ሁለቱንም ግቦች ማስቆጠር ችሎ የነበረው ኤርትራዊው አሊ ሱሌማን 65ኛው ደቂቃ ላይ ከፍፁም አለሙ የሰነጠቀለትን ኳስ በግሩም አጨራረስ ግብ በማድረግ የጣና ሞገዶቹን ሶስተኛ ግብ አስቆጠረ ።
በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በወላይታ ድቻ በኩል ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም እና በተለይም ከመስመር በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገው ነበር ምንም እንኳን ኢላማቸውን የጠበቁ እና ግብ ጠባቂውኖ የፈተኑ ባይሆኑም ። መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ የባህርዳር ከተማ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ተቀይሮ የገባው ቢንያም ፍቅሬ ግብ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ ለጥቂት በፋሲል ገብረሚካኤል ተይዞበታል ።
ውጤቱን ተከትሎም ባህርዳር ከተማ ነጥቡን 13 በማድረስ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ቢያሸንፍ ኖሮ መሪነቱን ድጋሚ መያዝ ይችል የነበረው ወላይታ ድቻ በእኩል 13 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ወደ 3ኛ ደረጃ ተንሸራቷል ።