የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመከላከያ እና በባህርዳር ከተማ መካከል ተደርጎ ከዕረፍት መልስ በተቆጠሩ ግቦች 1 – 1 ተለያይተዋል ።
መከላከያ በ19ኛው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ አሚን ነስሩን በግሩም ሀጎስ ምትክ ሲያሰልፉ ባህርዳር ከተማ ደግሞ በሳምንቱ በአርባምንጭ ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አራት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን ሄኖክ ኢሳይያስን ፤ ሰለሞን ወዴሳን ፤ አለልኝ አዘነን እና ሳለአምላክ ተገኝን በመናፍ ዓወል ፤ አህመድ ረሺድ ፤ አብዱልከሪም ኒኪማ እና አሊ ሱሌማን ምትክ ጨዋታውን እንዲጀምሩ ማድረግ ችለዋል ።በጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ባህርዳር ከተማዎች በፈጣን እንቅስቃሴ የጀመሩት ሲሆን ይህን ሁነት ግን ለረጅም ደቂቃዎች ማስቀጠል አልቻሉም ነበር ። በመከላከያ በኩል በመጀመሪያው ደቂቃዎች ላይ ወደ ኋላ አፈግፍገው የነበሩ ሲሆን ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ የባህርዳር ከተማን የኋላ ክፍል ለማስከፈት ጥረቶችን ማድረግ ችለው ነበር ።
በጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ቀዳሚው የግብ ሙከራ 12ኛ ደቂቃ ላይ የተመለከትን ሲሆን ቢንያም በላይ ከሳጥኑ በቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ፋሲል ገብረሚካኤል አድኖበታል ።
ባህርዳር ከተማዎች በፍፁም አለሙ መከላከያ ደግሞ በቢንያም በላይ አማካኝነት ለአጥቂዎቻቸው ጥሩ ጥሩ ኳሶችን በተለያዩ አቅጣጫዎች ኳሶችን ለማድረስ ቢጥሩም ወደ ማጥቃቱ ሶስተኛ ዞን የሚገቁ ኳሶች በተጋጣሚ ተከላካዮች በቀላሉ የሚመለሱ በመሆናቸው ሌሎች የግብ ሙከራዎችን በቀላሉ ለመመልከት አልቻልንም ።የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ያስመለከተን ሲሆን የግብ ሙከራዎችን ከግቦች ጋር ጭምር የተመለከትንበት ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
መከላከያዎች ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ወደ ግብ ለመድረስ ያደረጓቸው ጥረቶች የነበሩ ቢሆንም በአጨራረስ ችግሮች ምክንያት ቀድመው ግብ ማስቆጠር አልቻሉም ። በ46ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም በላይ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ኳሱ ወደ ውጪ ወጥቷል ።
በ59ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም አለሙ በሳጥን ውሰጥ በኢብራሂም ሁሴን በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ መቶ በማስቆጠር ባህርዳር ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል ።ከግቡ በኋላ የአቻነቱን ግብ ፍለጋ ጥረቶች ያደረጉት መከላከያዎች ከአስር ደቂቃዎች በኋላ አቻ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ። ቢንያም በላይ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ በልደቱ ጌታቸው ተገጭቶ ያገኘወሰ አዲሱ አቱላ ተቀይሮ በገባ በ69ኛው ሰከንድ ላይ ግብ አስቆጥሯል ።በ76ኛው ደቂቃ ላይ ግሩም ሀጎስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ ፋሲል በግሩም ሁኔታ ያዳነው ሲሆን በመጨረሻ ተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ከቅጣት ምት በተነሳ ኳስ ኦሴ ማውሊ ከክሌመንት ቦዬ ጋር ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ የጨዋታው የመጨረሻ የግብ ዕድል ነበር ።በመጨረሻም ጨዋታው 1 – 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ባህርዳር ከተማ ነጥቡን 25 በማድረስ ወደ 8ኛ ደረጃ ከፍ ሲል መከላከያ በበኩሉ ነጥቡን 21 ማድረስ ቢችልም በነበረበት 12ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።በ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሚያዚያ 21 ( አርብ ) 9 ሰዓት ላይ ባህርዳር ከተማ ጅማ አባጅፋርን ሲገጥም በዕለተለ አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ ደግሞ መከላከያ ኢትዮጵያ ቡናን የሚገጥም ይሆናል ።