በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ መከላከያን ከኢትዮጵያ ቡና አገናኝቶ በምክትል አሰልጣኙ ዮርዳኖስ ዓባይ እየተመራ የገባው መከላከያ ከእረፍት በፊት በተቆጠሩ ግቦች 3 ግቦች እና በተጨማሪ ደቂቃ ላይ በተቆጠረ አንድ ግብ ታግዞ 4 – 0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል ።
መከላከያዎች በ20ኛው ሳምንት ከባህርዳር ከተማ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሶስት ለውጦችን በማድረግ ግሩም ሀጎስ ፤ አዲሱ አቱላን እና እስራኤል እሸቱ በዳዊት ማሞ ፤ ልደቱ ጌታቸው እና ባዳራ ናቢ ሲላን ምትክ ሲያሰልፉ በሳምንቱ ከጅማ አባጅፋር በተመሳሳይ ነጥብ የተጋሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በጨዋታው ከተጠቀሙት የመጀመሪያ አሰላለፍ ሁለት ቅያሪዎችን በማድረግ ገዛኸኝ ደሳለኝን እና ተመስገን ገብረኪዳንን በሀይሌ ገብረትንሳይ እና ዊልያም ሰለሞን ምትክ በማሰለፍ ጨዋታውን መጀመር ችለዋል ።አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ በጀመረው የመከላከያ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ላይ መከላከያ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ጫና ፈጥረው በመጫወት ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉበት ነበር ።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ኳሱን ከኋላ መስርተው ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት በመከላከያ ተጫዋቾች በአጭሩ ሲጨናገፍ እና የሚነጠቋቸውም ኳሶች በራሳቸው ላይ ጫና ሊፈጥርባቸው ችሏል ።
መከላከያዎች በ10 እና 12ኛ ደቂቃ ላይ በተሾመ በላቸው እና ግሩም ሀጎስ ባደረጓቸወሰ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች የግብ ዕድሎችን መፍጠር የጀመሩ ሲሆን በ14ኛው ደቂቃ ላይ ተሾመ በላቸው ከምንተስኖት አዳነ በተከላካዮች መሀል ተሰንጥቆ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም የግቡ አግዳሚ መልሶበታል ።
በ20ኛው ደቂቃ ላይ ኢሚኑኤል ላርዬ ከአማኑኤል ዮሀንስ የነጠቀውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ በረከት አማረ የመለሰው ሲሆን ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ግብ የተላከው ኳስ ከመረብ ላይ አርፏል ።
ተሾመ በላቸው በተከላካዮች መሀል አልፎ የደረሰውን ኳስ ግብ ጠባቂውን በረከት አማረን በማለፍ ጭምር መከላከያን መሪ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል ።
- ማሰታውቂያ -
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ቢንያም በላይ በቡናማዎቹ የተከላካይ መስመር ክፍተት የደረሰውን ኳስ በበረከት አማረ መረብ ላይ በማሳረፍ የጦሩን መሪነት ወደ 2 – 0 ከፍ አደረገ ።ኢትዮጵያ ቡናዎች ከግቦቹ በኋላ በተወሰነ መልኩ ወደ መከላከያ የሜዳ ክፍል ለመድረስ ቢሞክሩም ይህ ነው ላባል የሚችል ጠንካራ የግብ ሙከራ ለማድረግ በፍፁም አልቻሉም ። ወደ መከላከያ ሳጥን ለመግባት እንኳን 27 ያህል ደቂቃዎች መጠበቅ የግድ ብሏቸው ነበር ።
በ40ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ በመንቀሳቀስ የኢትዮጵያ ቡናን የኋላ ክፍል ሲረብሽ የነበረው ተሾመ በላየቸው በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ላይ ሆኖ ወደ መሀል የቀነሰውን ኳስ ነፃ የነበረው አዲሱ አቱላ አግኝቶ ማስቆጠር ችሏል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በመከላከያ 3 – 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።
ሁለተኛውን አጋማሽ ቡናማዎቹ ተነቃቅተው የጀመሩ ቢመስሉም ወደ ተጋጣሚ የግቅ ክልል መድረስ ከብዷቸው ቀጥሏል ። ምንም እንኳን ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የመከላከያ የሜዳ ክፍል ላይ ለመድረስ ቢችሉም የመከላከያዎች ንቁ ሆነው መከላከል ነገሮችን አክብዶባቸዋል ።በ62ኛው ደቂቃ ላዬ የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ እና የኢትዮጵያ ቡና በጨዋታው ቀዳሚ የግብ ሙከራ የተደረገ ሲሆን ታፈሰ ሰለሞን በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ላይ የደረሰውን ኳስ አክርሮ ወደ ግቅ መሞከር ቢችልም ግብ ጠባቂው ክሌመንት ቦዬ አድኖታል ።
ኢትዮጵያ ቡናዎች የተጫዋቸ ቅያሪዎችን እንዲሁም የተጫዋች ሚና ለውጥን ማድረግ ቢችልም ፍሬያማ ሊሆኑ አልተቻላቸውም ።
በመከላከያ በኩል ከቆሙ ኳሶች እና በኢትዮጵያ ቡና የኋላ ክፍል ከጨዋታ ውጪ አጠባበቅ ላይ የሚፈጠሩ ከፍተቶችን በመጠቀም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን አድርገዋል ። በዚህም በ83ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት አዳነ ከቢንያም በላይ በግሩም ሁኔታ የደረሰውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ሙከራው ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ።መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ብቻ ሲቀረው ቢንያም በላይ በግራ መስመር በፍጥነት ይዞ የገባውን ኳስ ለምንተስኖት አዳነ ቀንሶለት የነበረ ቢሆንም የምንተስኖትን ኳሽ ቴዎድሮስ በቀለ ተንሸራቶ በመመለስ ግብ ከመሆን አድኖታል ።
በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ በረከት አማረ በፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውሰጥ በኤርሚያስ ኃይሉ ላይ በሰራው ጥፋት መከላከያዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት አሚኑ ነስሩ አስቆጥሯል ።በመጨረሻም መከላከያ 4 ኢትዮጵያ ቡና 0 ሆኖ ጨዋታው ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ ነጥቡን 24 ማድረስ የቻለ ቢሆንም በደረጃው ላይ ግን ለውጥ ሳያደርግ 12ኛ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በነበረበት 28 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።በ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ( ባህርዳር ) በመጪው ግንቦት 2 ( ማክሰኞ ) መከላከያ ሀድያ ሆሳዕናን ሲገጥም ሚያዝያ 30 ( ዕሁድ ) ኢትዮጵያ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ ይጫወታል ።